በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትምህርት ቤት ይሖዋን ማወደስ

በትምህርት ቤት ይሖዋን ማወደስ

በትምህርት ቤት ይሖዋን ማወደስ

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በትምህርት ቤት ውስጥ በንግግራቸውም ሆነ በጠባያቸው አምላክን የሚያወድሱባቸውን አጋጣሚዎች ይፈልጋሉ። የእነዚህን ወጣቶች ቅንዓት የሚያሳዩ አንዳንድ ተሞክሮዎችን እንመልከት።

በግሪክ አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር የምድር ከባቢ አየር ብክለትን አስመልክቶ በጽሑፍ ሪፖርት እንድታቀርብ ታዘዘች። የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) በመጠቀም ከንቁ! መጽሔት ላይ ጠቃሚ የሆነ ሐሳብ አገኘች፤ ከዚያም በጽሑፏ መጨረሻ ላይ ሐሳቡን ያገኘችው ከንቁ! መጽሔት እንደሆነ ጠቀሰች። አስተማሪዋም እስከዛሬ ካነበበቻቸው ሁሉ የሚበልጥ ጽሑፍ እንደሆነ ነገረቻት። ከጊዜ በኋላ አስተማሪዋ ይህንን መረጃ በአንድ ሴሚናር ላይ ተጠቅማበት ጥሩ ውጤት አግኝታበታለች። ወጣቷ እህት ይህንን ስትመለከት፣ “መምህራን ባይኖሩ ኖሮ እንዴት እንሆን ነበር?” የሚለውን ጨምሮ በርካታ ንቁ! መጽሔቶችን ለአስተማሪዋ ለማበርከት ወሰነች። አስተማሪዋ በክፍሉ ውስጥ ለንቁ! መጽሔት ያላትን አድናቆት የገለጸች ሲሆን ሌሎች ተማሪዎችም መጽሔቶቹን ማግኘት ይችሉ እንደሆነ ጠየቁ። እህት ሌሎች ርዕሶችንም እንዲያነብቡ ለተማሪዎቹ በርከት ያሉ ንቁ! መጽሔቶችን አመጣችላቸው።

አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በቤኒን አንዲት ወጣት ክርስቲያን ያልተለመደ ዓይነት ፈተና አጋጠማት። በትምህርት ቤቷ የሚገኙ የበርካታ ተማሪዎች ወላጆች ተሰባስበው ልጆቻቸውን ለፈተና ለማዘጋጀት ከበድ ያሉ የትምህርት ዓይነቶችን የሚያስተምሩላቸው አስጠኚዎች የመቅጠር ልማድ አላቸው። ሆኖም አስተማሪዎቹ የመረጡት ቀን ቅዳሜ ጠዋት ነበር። ወጣቷ ምሥክር “ቅዳሜ ጠዋት ጉባኤው በሙሉ ተሰባስቦ ለስብከት የሚወጣበት ቀን ነው። በሳምንቱ ውስጥ በጣም የምደሰትበት ቀን ስለሆነ በምንም ነገር አልለውጠውም!” በማለት ተቃውሞዋን ገለጸች። ያለ እናት የሚያሳድጋትና የይሖዋ ምሥክር የሆነው አባቷ በሐሳቧ የተስማማ ሲሆን በአንድ ቡድን ውስጥ ያሉትን አስጠኚዎችና ወላጆች አሰባስቦ ፕሮግራሙ እንዲቀየር ለማግባባት ሞከረ። ሆኖም ሁሉም ሐሳቡን ሳይቀበሉት ቀሩ። ስለዚህ ወጣቷ ልጅ ጥናቱ እንዲቀርባት ወስና ከጉባኤዋ አባላት ጋር በመሆን መስበኳን ቀጠለች። የክፍሏ ልጆች ያሾፉባት ሲሆን ስብከቷንም ሆነ አምላኳን እንድትተው ይጎተጉቷት ነበር። ፈተናዎቹን እንደምትወድቅ እርግጠኞች ነበሩ። ሆኖም ውጤቱን ሲሰሙ እነዚያ በቡድን ሆነው አስጠኚ የተቀጠረላቸው ተማሪዎች ሲወድቁ ወጣቷ እህታችን ግን ፈተናውን አለፈች። አሁን ተማሪዎቹም ማፌዛቸውን አቁመው “አምላክሽን ማገልገል መቀጠል አለብሽ” ማለት ጀምረዋል።

በቼክ ሪፑብሊክ አንዲት የ12 ዓመት ልጅ በአንድ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ የቃል ሪፖርት እንድታዘጋጅ ታዘዘች። እናቷ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ እንድትጠቀም አበረታታቻት። ሪፖርቷን “እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ሰው ማን ይመስላችኋል?” በሚል ጥያቄ ጀመረች። ስለ ኢየሱስ፣ በምድር ላይ ስላሳለፈው ሕይወትና ስለ ትምህርቶቹ በደንብ አድርጋ ገለጸችላቸው። ከዚያም “ስለ ይቅር ባይነት የተሰጠ ትምህርት” የሚለውን ምዕራፍ አብራራችላቸው። አስተማሪዋም “እስከ ዛሬ ካቀረብሽው ሁሉ የሚበልጥ ሪፖርት ነው!” በማለት በአድናቆት የተናገረች ሲሆን ልጅቷ መጽሐፉን ስትሰጣት አመስግና ወሰደች። አንዳንድ ተማሪዎችም መጽሐፉን ስለፈለጉት በሚቀጥለው ቀን 18 ቅጂዎችን በደስታ ለማበርከት ችላለች።

እንደነዚህ ያሉ ወጣቶች ይሖዋን በትምህርት ቤት በማወደሳቸው ትልቅ ደስታ አግኝተዋል። ሁላችንም ብንሆን እነዚህ ወጣቶች ያሳዩትን ቅንዓት ልንኮርጅ ይገባል።