ዘዳግም 30:1-20
30 “ይህ ቃል ሁሉ ይኸውም በፊትህ ያስቀመጥኩት በረከትና እርግማን+ በአንተ ላይ በሚመጣበትና አምላክህ ይሖዋ በመካከላቸው እንድትበተን ባደረገህ ብሔራት ምድር+ ሆነህ ይህን ቃል ሁሉ በምታስታውስበት* ጊዜ+
2 እንዲሁም አንተም ሆንክ ልጆችህ እኔ ዛሬ በማዝህ ትእዛዝ ሁሉ መሠረት በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ*+ ወደ አምላካችሁ ወደ ይሖዋ በምትመለሱበትና ቃሉን በምትሰሙበት ጊዜ+
3 አምላክህ ይሖዋ ተማርከው የተወሰዱብህን ይመልስልሃል፤+ ምሕረትም ያሳይሃል፤+ እንዲሁም አምላክህ ይሖዋ በመካከላቸው እንድትበተን ካደረገህ ሕዝቦች ምድር ሁሉ መልሶ ይሰበስብሃል።+
4 ሕዝብህ እስከ ሰማያት ዳርቻ ድረስ ቢበተን እንኳ አምላክህ ይሖዋ ከዚያ ይሰበስብሃል፤ ከዚያም መልሶ ያመጣሃል።+
5 አምላክህ ይሖዋ አባቶችህ ወርሰዋት ወደነበሩት ምድር ያስገባሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ፤ እሱም ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ እንዲሁም ያበዛሃል።+
6 በሕይወትም ትኖር ዘንድ አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ* እንድትወደው+ አምላክህ ይሖዋ ልብህን እንዲሁም የልጆችህን ልብ ያነጻል።*+
7 ከዚያም አምላክህ ይሖዋ እነዚህን እርግማኖች ሁሉ በሚጠሉህና በሚያሳድዱህ ጠላቶችህ ላይ ያመጣል።+
8 “አንተም ተመልሰህ የይሖዋን ቃል ትሰማለህ፤ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዛቱን ሁሉ ትፈጽማለህ።
9 አምላክህ ይሖዋ በአባቶችህ ደስ እንደተሰኘ+ ሁሉ ይሖዋ አንተንም በማበልጸግ ስለሚደሰት የሆድህን ፍሬ፣ እንስሶችህንና የምድርህን ፍሬ በማብዛት በእጅህ ሥራ ሁሉ እጅግ እንድትበለጽግ ያደርግሃል።+
10 ይህም የሚሆነው የአምላክህን የይሖዋን ቃል ስለምትሰማ፣ በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዛቱንና ደንቦቹን ስለምትጠብቅ እንዲሁም በሙሉ ልብህና በሙሉ ነፍስህ* ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ስለምትመለስ ነው።+
11 “እኔ ዛሬ የማዝህ ይህ ትእዛዝ ለአንተ ያን ያህል ከባድ አይደለም፤ ከአንተም የራቀ አይደለም።+
12 ‘ሰምተን እንድንፈጽመው ወደ ሰማይ ወጥቶ ማን ያምጣልን?’ እንዳትል ትእዛዙ ያለው በሰማይ አይደለም።+
13 ደግሞም ‘ሰምተን እንድንፈጽመው ባሕሩን ተሻግሮ ማን ያምጣልን?’ እንዳትል ትእዛዙ ያለው ከባሕሩ ማዶ አይደለም።
14 ቃሉ ትፈጽመው ዘንድ+ ለአንተ በጣም ቅርብ ነውና፤ ደግሞም በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው።+
15 “እንግዲህ እኔ ዛሬ ሕይወትንና መልካም ነገርን እንዲሁም ሞትንና መጥፎ ነገርን በፊትህ አስቀምጫለሁ።+
16 አምላክህን ይሖዋን በመውደድ፣+ በመንገዶቹ በመሄድ እንዲሁም ትእዛዛቱን፣ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን በመጠበቅ እኔ ዛሬ የማዝህን የአምላክህን የይሖዋን ትእዛዛት ብትሰማ በሕይወት ትኖራለህ፤+ ደግሞም ትበዛለህ፤ አምላክህ ይሖዋም በምትወርሳት ምድር ውስጥ ይባርክሃል።+
17 “ሆኖም ልብህ ቢሸፍትና+ ለመስማት ፈቃደኛ ባትሆን እንዲሁም ተታለህ ለሌሎች አማልክት ብትሰግድና ብታገለግላቸው+
18 በእርግጥ እንደምትጠፉ+ በዛሬው ዕለት እነግራችኋለሁ። ደግሞም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር ላይ ዕድሜያችሁ ያጥራል።
19 ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና እርግማንን በፊታችሁ እንዳስቀመጥኩ+ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምሥክሮች አድርጌ እጠራባችኋለሁ፤ እንግዲህ አንተም ሆንክ ዘሮችህ+ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤+
20 ይህን የምታደርገው አምላክህን ይሖዋን በመውደድ፣+ ቃሉን በመስማትና ከእሱ ጋር በመጣበቅ ነው፤+ ምክንያቱም እሱ ሕይወትህ ነው፤ ይሖዋ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት በማለላቸው ምድር ረጅም ዕድሜ የምትኖረውም በእሱ ነው።”+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “ወደ ልብህ መልሰህ በምታመጣበት።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “ይገርዛል።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።