በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለእንግዳ ድምፅ’ ጆሯችሁን እንዳትሰጡ ተጠንቀቁ

‘ለእንግዳ ድምፅ’ ጆሯችሁን እንዳትሰጡ ተጠንቀቁ

‘ለእንግዳ ድምፅ’ ጆሯችሁን እንዳትሰጡ ተጠንቀቁ

“እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።”—ዮሐንስ 10:5

1, 2. (ሀ) ማርያም፣ ኢየሱስ በስሟ ሲጠራት ምን ምላሽ ሰጠች? ኢየሱስ ከዚህ በፊት ይህን ሁኔታ የሚያሳይ ምን ነገር ተናግሯል? (ለ) ኢየሱስን በቅርብ እንድንከተል የሚያስችለን ምንድን ነው?

 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ፣ ባዶ የሆነው መቃብሩ አጠገብ የቆመችውን ሴት ተመለከታት። ሴቲቱን በቅርብ የሚያውቃት ሲሆን እርሷም መግደላዊት ማርያም ነች። ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ካደረባት ጋኔን ፈውሷታል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከኢየሱስና ከሐዋርያቱ ሳትለይ ስታገለግላቸው ቆይታለች። (ሉቃስ 8:1-3) ዛሬ ግን ማርያም፣ ኢየሱስ ሲገደል በማየቷና አሁን ደግሞ ሥጋው በመጥፋቱ በሐዘን ተውጣ እያለቀሰች ናት! ስለዚህ ኢየሱስ “አንቺ ሴት፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” ሲል ጠየቃት። ይህ ሰው አትክልተኛው ስለመሰላት “ጌታዬ፤ አንተ ወስደኸው ከሆነ፣ እባክህ እንድወስደው፣ የት እንዳኖርኸው ንገረኝ” ስትል መለሰችለት። ከዚያም ኢየሱስ “ማርያም” አላት። ከአጠራሩ ማን መሆኑን ወዲያው አወቀች። “መምህር ሆይ” ብላ በደስታ በመጮህ ተጠመጠመችበት።—ዮሐንስ 20:11-18

2 ይህ ስሜት የሚነካ ዘገባ ኢየሱስ ከተወሰነ ጊዜ በፊት የተናገረውን ነገር ያስታውሰናል። ኢየሱስ ራሱን እረኛ፣ ተከታዮቹን ደግሞ በጎች አድርጎ በመግለጽ እረኛው በጎቹን በየስማቸው እንደሚጠራቸውና እነርሱም ድምፁን እንደሚያውቁ ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:3, 4, 14, 27, 28) በእርግጥም አንድ በግ እረኛውን ለይቶ እንደሚያውቀው ሁሉ ማርያምም እረኛዋ የሆነውን የክርስቶስን ድምፅ አስታውሳለች። በዛሬው ጊዜ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮችም እረኛቸው አይጠፋቸውም። (ዮሐንስ 10:16) አንድ በግ የእረኛውን ድምፅ ለይቶ አውቆ ወደ እርሱ እንደሚሄድ ሁሉ እኛም መንፈሳዊ ማስተዋላችን የመልካሙን እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በቅርብ ተከትለን እንድንሄድ ያስችለናል።—ዮሐንስ 13:15፤ 1 ዮሐንስ 2:6፤ 5:20

3. ኢየሱስ ስለ በጎች ጉረኖ ከተናገረው ምሳሌ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

3 ይሁን እንጂ ይሄው ምሳሌ እንደሚያሳየው አንድ በግ የሰውን ድምፅ ለይቶ የማወቅ ችሎታው ወዳጁን ብቻ ሳይሆን ጠላቱንም እንዲያውቅ ያስችለዋል። እኛም መሠሪ ጠላቶች ስላሉን ይህ ችሎታ በጣም ይጠቅመናል። ጠላቶቻችን እነማን ናቸው? የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው? ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ኢየሱስ ስለ በጎች ጉረኖ በተናገረው ምሳሌ ላይ የጠቀሳቸውን ሌሎች ነገሮች እስቲ እንመልከት።

‘በበሩ የማይገባ’

4. ስለ እረኛ በሚናገረው ምሳሌ መሠረት በጎቹ የሚከተሉት ማንን ነው? ከማንስ ይርቃሉ?

4 ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በበሩ የሚገባ . . . እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤ በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።” (ዮሐንስ 10:2-5) ኢየሱስ “ድምፁን” የሚለውን ቃል ሦስት ጊዜ መጠቀሙን ልብ በል። ሁለት ጊዜ ስለ እረኛው ድምፅ የተናገረ ሲሆን በሦስተኛው ጊዜ ግን የተናገረው ስለ ‘እንግዳ ድምፅ’ ነው። ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ ምን ዓይነት እንግዳ ነው?

5. ዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ የተጠቀሰውን ዓይነት እንግዳ የማናስተናግደው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ቤታችን ለማስተናገድ ስለምንቀበለው ዓይነት እንግዳ መናገሩ አልነበረም። በእንግድነት መቀበል የሚለው ሐረግ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “እንግዶችን ማፍቀር” የሚል ትርጉም ነበረው። (ዕብራውያን 13:2) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው እንግዳ ተጋብዞ የመጣ አይደለም። ግለሰቡ “ወደ በጎች ጉረኖ [የገባው] በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘሎ” ነው። ደግሞም “ሌባና ነጣቂ ነው።” (ዮሐንስ 10:1) በአምላክ ቃል ላይ ሌባና ነጣቂ ተብሎ የተጠቀሰው የመጀመሪያው አካል ማን ነበር? ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። የዘፍጥረት መጽሐፍ ማስረጃውን ይዞልናል።

የእንግዳ ድምፅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማበት ወቅት

6, 7. ሰይጣን እንግዳና ሌባ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

6 ዘፍጥረት 3:1-5 በምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የእንግዳ ድምፅ የተሰማበትን ሁኔታ ይገልጻል። ዘገባው ሰይጣን የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን በእባብ አማካኝነት እንደቀረባትና አሳሳች በሆነ መንገድ እንዳናገራት ይገልጻል። እርግጥ፣ በዚህ ዘገባ ላይ ሰይጣን ቃል በቃል “እንግዳ” ተብሎ አልተጠራም። ይሁን እንጂ አድራጎቱ በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ከተገለጸው እንግዳ ጋር በብዙ መንገድ ይመሳሰላል። ሁለቱን የሚያመሳስላቸውን አንዳንድ ነገሮች ተመልከት።

7 ኢየሱስ እንግዳው ጉረኖው ውስጥ ወዳሉት በጎች የሚመጣው በዙሪያ ጥምጥም እንደሆነ ተናግሯል። በተመሳሳይም ሰይጣን ሔዋንን ለማነጋገር የመጣው በተዘዋዋሪ መንገድ በእባብ በመጠቀም ነበር። ይህ ተንኮል ያዘለ አቀራረቡ ሰይጣን በእርግጥ አደገኛ ሌባ መሆኑን ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ወደ ጉረኖው የገባው እንግዳ ዓላማ በጎቹን ከባለቤቱ መስረቅ ነው። እንዲያውም ‘የመግደልና የማጥፋት’ ዓላማም ስላለው ከሌባም የከፋ ነው። (ዮሐንስ 10:10) በተመሳሳይ ሰይጣንም ሌባ ነው። ሔዋንን በማታለል ለአምላክ የነበራትን ታማኝነት ሰርቋል። ከዚህም በላይ ሰይጣን በሰዎች ላይ ሞት አምጥቷል። በመሆኑም ነፍሰ ገዳይ ነው።

8. ሰይጣን የይሖዋን ቃልና ዓላማ አጣምሞ ያቀረበው እንዴት ነው?

8 ሰይጣን የይሖዋን ቃልና ሐሳብ አጣምሞ ካቀረበበት መንገድ አታላይ መሆኑ በግልጽ ይታያል። ሔዋንን “በእርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” ሲል ጠየቃት። ሰይጣን ነገሩን ማመን ያቃተው በመምሰል ‘አምላክ እንዴት ይህን ያህል ምክንያታዊነት ይጎድለዋል?’ ያለ ያህል ነበር። አክሎም ‘ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈት እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው’ አላት። “እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” የሚለው አባባሉን ልብ በል። በሌላ አነጋገር ሰይጣን ‘እርሱ የሚያውቀውን እኔም አውቃለሁ። ዓላማው መች ጠፋኝ፤ እናንተን ማሰቃየት ነው’ ማለቱ ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1, 5) ሔዋንና አዳም ከዚህ እንግዳ ድምፅ ዞር አለማለታቸው በጣም ያሳዝናል። ከዚያ ይልቅ ቃሉን አምነው በመቀበላቸው በራሳቸውና በዘሮቻቸው ላይ መከራ አመጡ።—ሮሜ 5:12, 14

9. በዛሬው ጊዜ የእንግዳ ድምፅ ልንሰማ እንደምንችል መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?

9 ሰይጣን በዛሬው ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች ለማሳሳት ተመሳሳይ ዘዴዎች ይጠቀማል። (ራእይ 12:9) እርሱ ‘የሐሰት አባት’ ሲሆን እንደ እርሱ የአምላክን ሕዝቦች ለማሳሳት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ልጆቹ ናቸው። (ዮሐንስ 8:44) በዛሬው ጊዜ የእነዚህ እንግዳ ሰዎች ድምፅ የሚሰማባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

በዛሬው ጊዜ የእንግዳ ድምፅ የሚመጣባቸው አቅጣጫዎች

10. የእንግዳ ድምፅ የሚሰማበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?

10 አሳሳች ትምህርቶች። ሐዋርያው ጳውሎስ “በልዩ ልዩ ዐይነት እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ” ሲል ተናግሯል። (ዕብራውያን 13:9) ምን ዓይነት ትምህርቶች? እነዚህ ትምህርቶች ‘እንድንወሰድ’ የሚያደርጉ በመሆናቸው ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው መንፈሳዊ አቋማችንን ስለሚያዳክሙብን ትምህርቶች እንደሆነ ግልጽ ነው። እንደዚህ ያሉ እንግዳ ትምህርቶች የሚመጡት ከየት ነው? ጳውሎስ ለተወሰኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች “ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ” ብሏቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:30) በእርግጥም፣ እንደ ጳውሎስ ዘመን ሁሉ ዛሬም ከዚህ በፊት የክርስቲያን ጉባኤ አባል የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች በጎቹን ለማታላል ውሸት በመቀላቀል ብሎም ዓይን ያወጣ ውሸት በመናገር ‘እውነትን ያጣምማሉ።’ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደገለጸው እውነት የሚመስል ሆኖም ምንም እርባና የሌለው ነገር ማለትም ‘የፈጠራ ታሪክ’ ያወራሉ።—2 ጴጥሮስ 2:3

11. በ2 ጴጥሮስ 2:1, 3 ላይ የሚገኙት ቃላት የከሃዲዎችን ዘዴና ዓላማ የሚያጋልጡት እንዴት ነው?

11 ጴጥሮስ “የስሕተት ትምህርት በስውር ያስገባሉ” በማለት ከሃዲዎች የሚጠቀሙባቸውን ሌሎች ዘዴዎችም አጋልጧል። (2 ጴጥሮስ 2:1, 3) ኢየሱስ ስለ በጎች ጉረኖ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሌባ የሚገባው “በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘሎ” እንደሆነ ሁሉ ከሃዲዎችም የሚቀርቡን በረቀቀ ዘዴ ነው። (ገላትያ 2:4፤ ይሁዳ 4) ዓላማቸው ምንድን ነው? ጴጥሮስ በማከል “ይበዘብዙዋችኋል” ብሏል። በእርግጥም ከሃዲዎች ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን በተመለከተ የፈለጉትን ነገር ቢሉም ዋነኛ ዓላማቸው ግን ‘መስረቅ፣ መግደልና ማጥፋት’ ነው። (ዮሐንስ 10:10) እንደዚህ ካሉ እንግዶች ተጠበቁ!

12. (ሀ) ጓደኛ አድርገን የምንቀርባቸው ሰዎች ለእንግዳ ድምፆች ሊያጋልጡን የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ሰይጣን በሚጠቀምባቸውና እንግዳ የሆኑ ሰዎች በሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

12 መጥፎ ባልንጀሮች። ጓደኛ አድርገን በምንቀርባቸው ሰዎች አማካኝነት የእንግዳ ድምፅ ልንሰማ እንችላለን። መጥፎ ባልንጀርነት በተለይ ወጣቶችን ይጎዳል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ሰይጣን ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች መካከል ዒላማ ያደረገው በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ አነስተኛ የነበረችውን ሔዋንን ነው። ሰይጣን፣ ይሖዋ ከልክ በላይ ነፃነቷን እንደገደበባት አሳመናት፤ ሐቁ ግን ተቃራኒው ነበር። ይሖዋ ሰብዓዊ ፍጡራኑን ያፈቅራቸው እንዲሁም ስለ ደኅንነታቸው ያስብላቸው ነበር። (ኢሳይያስ 48:17) በተመሳሳይ ዛሬ፣ እንግዳ የሆኑ ሰዎች ወላጆቻችሁ ነፃነታችሁን ከልክ በላይ እንደገደቡባችሁ ሊያሳምኑ የሚሞክሩት ወጣት የሆናችሁትን ነው። እነዚህ እንግዳ የሆኑ ሰዎች ምን ተጽዕኖ ሊያሳድሩባችሁ ይችላሉ? አንዲት ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ስትል በግልጽ ተናግራለች፦ “ለተወሰነ ጊዜ የክፍል ጓደኞቼ እምነቴን አዳክመውብኝ ነበር። ሃይማኖቴ ጨቋኝና የማያፈናፍን እንደሆነ ብዙ ጊዜ ነግረውኛል።” እውነታውን ከተመለከትን ግን ወላጆቻችሁ በጣም ይወዷችኋል። ስለዚህ የክፍል ጓደኞቻችሁ ወላጆቻችሁን እንድትጠረጥሯቸው ለማሳመን ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ እንደ ሔዋን አትታለሉ።

13. ዳዊት የተከተለው የጥበብ ጎዳና ምንድን ነው? እርሱን መምሰል የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?

13 መዝሙራዊው ዳዊት መጥፎ ባልንጀርነትን በተመለከተ “ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም” ብሏል። (መዝሙር 26:4) እዚህም ላይ ቢሆን እንግዳ የሆኑ ሰዎች የሚታይባቸውን ዓይነተኛ ባሕርይ አስተዋላችሁ? ሰይጣን በእባብ በመጠቀም ማንነቱን እንደደበቀ ሁሉ እነርሱም ማንነታቸውን ይሰውራሉ። በዛሬው ጊዜ አንዳንድ በሥነ ምግባር የረከሱ ሰዎች በኢንተርኔት ሲጠቀሙ ማንነታቸውንና ትክክለኛ ዓላማቸውን ይደብቃሉ። መጥፎ ዓላማ ያላቸው አዋቂዎችን በኢንተርኔት ካገኛችኋቸው እናንተን ለማጥመድ ሲሉ ወጣት መስለው ሊቀርቡም ይችላሉ። ወጣቶች፣ መንፈሳዊ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ እባካችሁ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ።—መዝሙር 119:101፤ ምሳሌ 22:3

14. አንዳንድ ጊዜ መገናኛ ብዙኃን የእንግዶችን ድምፅ የሚያሰሙት እንዴት ነው?

14 የሐሰት ክሶች። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚቀርቡ አንዳንድ የዜና ዘገባዎች ትክክለኛ ቢሆኑም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ግን መገናኛ ብዙኃን እንግዶች የሚያሰሙትን የተዛባ አመለካከት ለማሰራጨት መጠቀሚያ ሆነው ያገለግላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ አገር ውስጥ የቀረበ የዜና ሪፖርት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች የሂትለርን አገዛዝ ደግፈዋል ብሎ በሐሰት ተናግሯል። በሌላ አገር የቀረበ ሪፖርት ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተ ክርስቲያኖችን አፍርሰዋል ሲል ወንጅሏቸዋል። በበርካታ አገሮች ውስጥ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው ሕክምና እንዳያገኙ ይከለክላሉ እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች የሚፈጽሟቸውን ከባድ ኃጢአቶች አይተው እንዳላዩ ሆነው ያልፋሉ ብለው ወንጅለዋቸዋል። (ማቴዎስ 10:22) ይሁንና እኛን በቅርብ የሚያውቁን ልበ ቅን ሰዎች እነዚህ ክሶች ውሸት መሆናቸውን ያውቃሉ።

15. በመገናኛ ብዙኃን የቀረበውን ሁሉ ማመናችን ጥበብ የማይሆነው ለምንድን ነው?

15 እንግዳ የሆኑ ሰዎች የሚያሰሙት ክስ ቢሰነዘርብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ምሳሌ 14:15 ላይ የሚገኘውን “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” የሚለውን ምክር መከተል ይኖርብናል። በመገናኛ ብዙኃን እውነት ተደርጎ የሚቀርበውን ሁሉ ማመኑ ጥበብ አይደለም። ከዓለማዊ ምንጮች የሚገኙትን መረጃዎች በሙሉ መጠራጠር ባይኖርብንም ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደ ሆነ’ መዘንጋት አይኖርብንም።—1 ዮሐንስ 5:19

የምትሰሟቸው ነገሮች “ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ”

16. (ሀ) ኢየሱስ ዮሐንስ 10:4 ላይ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን የበጎች ባሕርይ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንድናደርግ ያበረታታናል?

16 የምንሰማው ድምፅ የወዳጅ ይሁን የጠላት በእርግጠኝነት ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በጎቹ እረኛውን የሚከተሉት “ድምፁን ስለሚያውቁ” መሆኑን ተናግሯል። (ዮሐንስ 10:4) በጎቹ እርሱን እንዲከተሉት የሚያደርጋቸው አለባበሱ ሳይሆን የሚያሰማው ድምፅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተጠቀሱ ቦታዎች የሚዘግብ አንድ መጽሐፍ በጎች እረኛቸውን የሚያውቁት በድምፁ ሳይሆን በልብሱ ነው ብሎ አንድ አገር ጎብኚ እንደተከራከረ ይገልጻል። አንድ እረኛ በጎቹ የሚያውቁት ድምፁን ነው ብሎ መለሰለት። ይህን በተጨባጭ ለማሳየት እረኛውና እንግዳው ልብስ ተቀያየሩ። እንግዳው የእረኛውን ልበስ ለብሶ በጎቹን ቢጠራቸውም ድምፁን ስለማያውቁ ወደ እርሱ አልሄዱም። ይሁንና እረኛው ልብሱን ቢቀይርም እንኳ ሲጠራቸው ወዲያው ወደ እርሱ ሄዱ። ስለዚህ አንድ ሰው እረኛ መስሎ ቢቀርብም እንኳ በጎቹን ማታለል አይችልም። በሌላ አባባል በጎች የሰሙትን ድምፅ ከእረኛው ድምፅ ጋር በማወዳደር ያጣራሉ ማለት ነው። የአምላክ ቃል “መናፍስት ከእግዚአብሔር መሆናቸውን መርምሩ” በማለት እኛም ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ይመክረናል። (1 ዮሐንስ 4:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:13) እንዲህ እንድናደርግ የሚረዳን ምንድን ነው?

17. (ሀ) የይሖዋን ድምፅ በሚገባ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ከይሖዋ የምናገኘው እውቀት ምን እንድናደርግ ያስችለናል?

17 የይሖዋን ድምፅ ወይም ቃል በትክክል ባወቅን መጠን የእንግዳን ድምፅ በተሻለ ሁኔታ መለየት እንደምንችል የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ችሎታ እንዴት ማዳበር እንደምንችል ይናገራል። “ጆሮህ ከኋላህ፣ ‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’ የሚል ድምፅ ይሰማል” ይላል። (ኢሳይያስ 30:21) ከኋላችን የምንሰማው “ድምፅ” የሚመጣው ከአምላክ ቃል ነው። የአምላክን ቃል ባነበብን ቁጥር በምሳሌያዊ አነጋገር የታላቁ እረኛችንን የይሖዋን ድምፅ የሰማን ያህል ነው። (መዝሙር 23:1) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ባጠናን መጠን የአምላክንም ድምፅ የዚያኑ ያህል እያወቅን እንሄዳለን። እንዲህ ዓይነት ጥልቅ እውቀት ማግኘታችን ደግሞ የእንግዶችን ድምፅ ወዲያውኑ ለይተን እንድናውቅ ያስችለናል።—ገላትያ 1:8

18. (ሀ) የይሖዋን ድምፅ ማወቅ ምን ነገር ይጨምራል? (ለ) በማቴዎስ 17:5 መሠረት የኢየሱስን ድምፅ መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?

18 የይሖዋን ድምፅ ማወቅ ምን ማድረግን ይጨምራል? ከመስማት በተጨማሪ መታዘዝንም ይጨምራል። ኢሳይያስ 30:21ን በድጋሚ ተመልከት። የአምላክ ቃል “መንገዱ ይህ ነው” ይላል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይሖዋ የሚሰጠንን መመሪያ እንሰማለን። ቀጥሎ ደግሞ “በእርሱ ሂድ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶናል። ይሖዋ የሰማነውን ነገር በሥራ እንድናውል ይፈልጋል። ስለዚህ የተማርነውን ነገር በሥራ በማዋል የይሖዋን ድምፅ መስማት ብቻ ሳይሆን ድምፁን እንደታዘዝንም እናሳያለን። (ዘዳግም 28:1) የይሖዋን ድምፅ መታዘዝ የኢየሱስን ድምፅ መታዘዝ ማለትም ነው። ምክንያቱም እንዲህ እንድናደርግ ያዘዘን ይሖዋ ራሱ በመሆኑ ነው። (ማቴዎስ 17:5) መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ምን እንድናደርግ ነግሮናል? ደቀ መዛሙርት እንድናደርግና ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ ላይ እምነት እንድንጥል አዝዞናል። (ማቴዎስ 24:45፤ 28:18-20) የእርሱን ድምፅ መታዘዝ ማለት የዘላለም ሕይወት ማግኘት ማለት ነው።—የሐዋርያት ሥራ 3:23

“ከእርሱ ይሸሻሉ”

19. የእንግዳ ድምፅ ስንሰማ ልንወስደው የሚገባ እርምጃ ምንድን ነው?

19 ታዲያ የእንግዳ ድምፅ ብንሰማ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በጎች እንደሚያደርጉት ማድረግ አለብን። ኢየሱስ “ከእርሱ [ከእንግዳው] ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም” ብሏል። (ዮሐንስ 10:5) ምላሻችን ሁለት ነገሮች ያካተተ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አንድን እንግዳ ‘ፈጽሞ አንከተልም።’ አዎን፣ እንግዳ አጠገባችን እንዲደርስ አንፈቅድም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ግሪክኛ ቋንቋ “ፈጽሞ” የሚለው ቃል ፊት መንሳትን ለማመልከት የተሠራበት ጠንካራ አገላለጽ ነው። (ማቴዎስ 24:35፤ ዕብራውያን 13:5) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ‘ከእርሱ እንሸሻለን’ ወይም እንርቃለን። የመልካሙን እረኛ ድምፅ የሚቃረን ትምህርት ለሚያስተምሩ ሰዎች የምንሰጠው ትክክለኛው ምላሽ ይህ ብቻ ነው።

20. (ሀ) አታላይ ከሃዲዎች ሲያጋጥሙን፣ (ለ) መጥፎ ባልንጀሮች ሲያጋጥሙን እና (ሐ) በመገናኛ ብዙኃን የቀረቡ የተዛቡ ሪፖርቶች ስንሰማ ምን ምላሽ እንሰጣለን?

20 ስለዚህ የክህደት ትምህርት የሚያስፋፉ ሰዎች ሲያጋጥሙን “መለያየትን ከሚፈጥሩትና የተማራችሁትን ትምህርት በመቃወም በጉዞአችሁ መሰናክል ከሚያደርጉት እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነርሱም ራቁ” በማለት የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር መከተል ያስፈልገናል። (ሮሜ 16:17፤ ቲቶ 3:10) በተመሳሳይም፣ መጥፎ ባልንጀሮች ለሚያደርሱባቸው አደጋ የተጋለጡ ወጣት ክርስቲያኖች ጳውሎስ “ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ” በማለት ለወጣቱ ጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋሉ። እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን የሐሰት ክሶች ሲሰነዝሩብን ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ተጨማሪ ምክር እናስታውሳለን፦ “[የእንግዳ ድምፅ የሚሰሙ ክርስቲያኖች] . . . ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ። አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን።” (2 ጢሞቴዎስ 2:22፤ 4:3-5) የእንግዳ ሰዎች ድምፅ ምንም ያህል ለስላሳ ሊመስል ቢችልም እምነታችንን ከሚያዳክምብን ነገር ሁሉ እንሸሻለን።—መዝሙር 26:5፤ ምሳሌ 7:5, 21፤ ራእይ 18:2, 4

21. የእንግዶችን ድምፅ ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ምን ሽልማት ያገኛሉ?

21 በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች የእንግዶችን ድምፅ ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆን ሉቃስ 12:32 ላይ ለሚገኙት የመልካሙ እረኛ ቃላት ምላሽ ይሰጣሉ። እዚያ ላይ ኢየሱስ “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ” ብሏቸዋል። “ሌሎች በጎች” ደግሞ “እናንት አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ለመስማት በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:34) ‘የእንግዶችን ድምፅ’ ከመስማት የምንርቅ ከሆነ እጅግ አስደሳች ሽልማት ይጠብቀናል!

ታስታውሳለህ?

• ኢየሱስ ስለ በጎች ጉረኖ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው እንግዳ ለሰይጣን ትክክለኛ መግለጫ የሆነው እንዴት ነው?

• በዛሬው ጊዜ የእንግዶች ድምፅ የሚሰማው እንዴት ነው?

• የእንግዶችን ድምፅ ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• የእንግዳ ድምፅ ስንሰማ ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርያም ክርስቶስን በድምፁ አውቃዋለች

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንግዳው ወደ በጎቹ የሚመጣው ፊት ለፊት አይደለም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንግዶች ለሚያሰሙት ድምፅ ምን ምላሽ እንሰጣለን?