በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከኒቆዲሞስ ተማሩ

ከኒቆዲሞስ ተማሩ

ከኒቆዲሞስ ተማሩ

“በኋላዬ ሊመጣ የሚ​ወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም [“የመከራውንም እንጨት፣” NW ] ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።” (ሉቃስ 9:​23) ይህን ግብዣ ያለ አንዳች ማንገራገር የተቀበሉት ተራ ዓሣ አጥማጆችና አንድ የተናቀ ቀረጥ ሰብሳቢ ነበሩ። ሁሉን ትተው ኢየሱስን ተከተሉ።​—⁠ማቴዎስ 4:​18-22፤ ሉቃስ 5:​27, 28

ኢየሱስ ያቀረበው ይህ ጥሪ ዛሬም በማስተጋባት ላይ ሲሆን ብዙዎች ለዚህ ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ደስ የሚላቸው አንዳንድ ሰዎች ‘ራሳቸውን ለመካድና የመከራ እንጨታቸውን ለመሸከም’ ያቅማማሉ። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት መሸከምና የሚያስገኘውን ልዩ መብት መቀበል አይፈልጉም።

አንዳንዶች የኢየሱስን ግብዣ ተቀብለው ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ ከመወሰን ወደ ኋላ የሚሉት ለምንድን ነው? በአንድ አምላክ በሚያምኑት የአይሁድና የክርስትና እምነቶች ውስጥ ያላደጉ ሰዎች ሁሉን ቻይ የሆነውን ፈጣሪ ሕልውና ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድባቸው አይካድም። አንዳንዶቹ ግን አምላክ እውን አካል መሆኑን ካመኑ በኋላም የኢየሱስን ፈለግ ከመከተል ወደኋላ ይላሉ። የይሖዋ ምሥክር ብሆን ዘመዶቼና ወዳጆቼ ምን ይሉኛል ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ የምንኖርበት ጊዜ አጣዳፊነት ስለማይታያቸው ዝናንና ሀብትን ወደማሳደድ ዘወር ይላሉ። (ማቴዎስ 24:​36-42፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​9, 10) የኢየሱስ ተከታዮች ለመሆን ዛሬ ነገ የሚሉ ሰዎች ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን በኢየሱስ ዘመን ከኖረው ባለጠጋ የአይሁድ አለቃ ከኒቆዲሞስ ታሪክ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።

ግሩም አጋጣሚዎች የነበሩት ሰው

ኒቆዲሞስ፣ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ከጀመረ ከስድስት ወር ገደማ በኋላ ‘ከአምላክ ዘንድ ተልኮ የመጣ መምህር መሆኑን’ ተገነዘበ። ኒቆዲሞስ፣ ኢየሱስ በ30 እዘአ በተከበረው የማለፍ በዓል ዕለት በኢየሩሳሌም ባደረጋቸው ተአምራት በጣም በመገረሙ በኢየሱስ እንደሚያምን ለመናገርና ስለዚህ መምህር ይበልጥ ለመማር በጨለማ ተደብቆ መጣ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ‘ዳግም መወለድ’ አስፈላጊ መሆኑን ስለሚገልጸው ጥልቅ እውነት ለኒቆዲሞስ ነገረው። ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” የሚሉትን ቃላት የተናገረው በዚህ ጊዜ ነበር።​—⁠ዮሐንስ 3:​1-16

ኒቆዲሞስ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶለታል! የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት የተለያዩ ገጽታዎች በቀጥታ በመመልከት የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ መሆን ይችል ነበር። ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃና በእስራኤል ውስጥ መምህር እንደመሆኑ መጠን ጥሩ የአምላክ ቃል እውቀት ነበረው። በተጨማሪም ኢየሱስ ከአምላክ ዘንድ የመጣ መምህር መሆኑን መለየት መቻሉ ግሩም ማስተዋል እንደነበረው የሚያሳይ ነው። ኒቆዲሞስ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ትሑት ሰው ነበር። የአይሁድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አባል የሆነ አንድ ሰው አንድን ተራ የአናጢ ልጅ ከአምላክ ዘንድ የተላከ ሰው አድርጎ መቀበል ምንኛ የሚከብድ ነው! እነዚህ ሁሉ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከሚሆን ሰው የሚፈለጉ ባሕርያት ናቸው።

ኒቆዲሞስ በዚህ በናዝሬት ሰው ላይ ያለው እምነት እያደር የሚቀንስ አይመስልም። ከሁለት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ የዳስ በዓል በዋለበት ዕለት ኒቆዲሞስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ስብሰባ ላይ ተገኘ። በዚህ ወቅት ኒቆዲሞስ ራሱ “ከእነርሱ አንዱ” ነበር። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማስያዝ ሎሌዎችን ላኩ። ሎሌዎቹ ተመልሰው “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” በማለት አስረዱ። ፈሪሳውያን “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” በማለት ያጣጥሏቸው ጀመር። ኒቆዲሞስ በዚህ ጊዜ ዝም ማለት አላስቻለውም። “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ተናገረ። በዚህ ጊዜ ሌሎች ፈሪሳውያን “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ” በማለት ተቹት።​—⁠ዮሐንስ 7:​1, 10, 32, 45-52

ኒቆዲሞስ ስድስት ወር ከሚያክል ጊዜ በኋላ በ33 እዘአ በተከበረው የማለፍ በዓል ዕለት የኢየሱስ አስከሬን ከመከራው እንጨት ላይ ሲወርድ ተመልክቷል። የአርማትያሱ ዮሴፍ ከሚባል ሌላ የሳንሄድሪን አባል ጋር በመሆን የኢየሱስን አስከሬን ገነዘ። ኒቆዲሞስ ለዚሁ ዓላማ 33 ኪሎ ግራም የሚያክል “የከርቤና የእሬት ቅልቅል” አመጣ። ይህ ቅልቅል ከፍተኛ ዋጋ ያወጣል። ከዚህም በላይ ሌሎቹ ፈሪሳውያን “አሳች” ብለው የሚጠሩት የኢየሱስ ደጋፊ መሆኑን ማሳወቅ ድፍረት የሚጠይቅ ነው። ሁለቱ ሰዎች የኢየሱስን አስከሬን በፍጥነት በመገነዝ በአቅራቢያው በሚገኝ አዲስ መቃብር ውስጥ አስቀመጡት። ይሁን እንጂ ኒቆዲሞስ በዚህ ጊዜም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር አልሆነም!​—⁠ዮሐንስ 19:​38-42፤ ማቴዎስ 27:​63፤ ማርቆስ 15:​43

እርምጃ ያልወሰደበት ምክንያት

ኒቆዲሞስ ‘የመከራውን እንጨት ተሸክሞ’ ኢየሱስን ያልተከተለበት ምክንያት ዮሐንስ በጻፈው ታሪክ ውስጥ አልተጠቀሰም። ይሁን እንጂ ይህ ፈሪሳዊ ቁርጥ ያለ አቋም ያልወሰደበትን ምክንያት የሚጠቁሙ አንዳንድ ፍንጮች ሰጥቷል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ዮሐንስ ይህ የአይሁድ አለቃ “በሌሊት ወደ ኢየሱስ” መምጣቱን ጠቅሷል። (ዮሐንስ 3:​2) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “ኒቆዲሞስ በሌሊት የመጣው ፈርቶ ሳይሆን ከኢየሱስ ጋር ውይይት በሚያደርግበት ጊዜ ሕዝቡ ጣልቃ እንዳይገባበት አስቦ ነው” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ኒቆዲሞስን “አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ” ሲል ገልጾታል። ይህን ያለው የአርማቲያሱ ዮሴፍን በተመለከተ “አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ” በማለት ከሰጠው መግለጫ ጋር አያይዞ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዮሐንስ 19:​38, 39) ስለሆነም በዘመኑ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ስለ ኢየሱስ መናገር ይፈሩ እንደነበረ ሁሉ ኒቆዲሞስም በጨለማ ተደብቆ ወደ ኢየሱስ የመጣው “አይሁድን ስለ ፈራ” እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።​—⁠ዮሐንስ 7:​13

አንተስ ዘመዶችህ፣ ወዳጆችህ ወይም አብረሃቸው የምትውላቸው ሰዎች ምን ይሉኛል ብለህ በመፍራት የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ዛሬ ነገ ትላለህ? አንድ ምሳሌ “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል” ይላል። እንዲህ ዓይነቱን ፍርሃት ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌው በመቀጠል “በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል” ይላል። (ምሳሌ 29:​25) በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ ትምክህት ለማሳደር ከባድ ችግር በሚያጋጥምህ ጊዜ አምላክ እንደሚደግፍህ ማረጋገጫ ማግኘት ያስፈልግሃል። ወደ ይሖዋ በመጸለይ አምልኮትህን የሚመለከቱ ጥቃቅን የሚመስሉ ውሳኔዎችን እንኳ ለማድረግ ድፍረት እንዲሰጥህ ጠይቀው። እያደር በይሖዋ ላይ ያለህ እምነትና ትምክህት አድጎ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ከባድ ውሳኔዎችን እስከማድረግ ትደርሳለህ።

በተጨማሪም ኒቆዲሞስ በገዢው መደብ አባልነቱ የነበረው ሥልጣንና ክብር ራሱን የመካድ አስፈላጊ እርምጃ እንዳይወስድ እንቅፋት ሆኖበት ሊሆን ይችላል። በዚያን ጊዜ በሳንሄድሪን አባልነት ለነበረው ቦታ ከፍተኛ ግምት ኖሮት መሆን አለበት። አንተስ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለህን ከፍ ያለ ቦታ አጣለሁ ብለህ በመፍራት ወይም ወደፊት እድገት ላላገኝ እችላለሁ ብለህ በመስጋት የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ታመነታለህ? ከእነዚህ መካከል የትኛውም ቢሆን እንደ ፈቃዱ የምትለምነውን ለማሟላት ፈቃደኛ የሆነውን የአጽናፈ ዓለም ልዑል ማገልገልን ከመሰለው ታላቅ መብት ጋር ሊስተካከል አይችልም።​—⁠መዝሙር 10:​17፤ 83:​18፤ 145:​18

ኒቆዲሞስ ቁርጥ ያለ አቋም እንዳይወስድ እንቅፋት የሆነበት ሌላው ምክንያት ሀብቱ ሊሆን ይችላል። ፈሪሳዊ እንደመሆኑ መጠን “ገንዘብንም ይወድዱ” የነበሩ ሌሎች ፈሪሳውያን ተጽዕኖ አሳድረውበት ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 16:​14) በጣም ውድ የሆነ የከርቤና የእሬት ቅልቅል መስጠት መቻሉ ባለጠጋ እንደነበረ ያሳያል። ዛሬም አንዳንዶች ስለ ቁሳዊ ንብረቶቻቸው በመጨነቅ ክርስቲያን መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመቀበል ውሳኔ ከማድረግ ይዘገያሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ . . . ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” በማለት ተከታዮቹን አጥብቆ አሳስቧቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 6:​25-33

ብዙ ነገር አምልጦታል

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብቻ በሚገኘው የኒቆዲሞስ ታሪክ ውስጥ ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ተከታይ ስለመሆኑ ምንም አለመናገሩ ትኩረትን የሚስብ ነው። አንድ አፈ ታሪክ ኒቆዲሞስ የኢየሱስ ተከታይ እንደሆነ፣ እንደተጠመቀ፣ ከአይሁድ ስደት እንደደረሰበት፣ ከሥልጣኑ እንደተባረረ እንዲሁም በመጨረሻ ከኢየሩሳሌም እንደተባረረ ይገልጻል። ያም ሆነ ይህ ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች ነን። ይኸውም ኢየሱስ እዚህ ምድር ላይ ሳለ ኒቆዲሞስ ቁርጥ ያለ እርምጃ ባለመውሰዱ ብዙ ነገር አምልጦታል።

ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር መጀመሪያ በተገናኘበት ጊዜ ኢየሱስን መከተል ጀምሮ ቢሆን ኖሮ የኢየሱስ የቅርብ ደቀ መዝሙር መሆን በቻለ ነበር። ኒቆዲሞስ እንደነበረው እውቀት፣ ማስተዋል፣ ትሕትናና ለመንፈሳዊ ፍላጎቱ ንቁ እንደመሆኑ ቢሆን ኖሮ ግሩም ደቀ መዝሙር መሆን በቻለ ነበር። አዎን፣ የታላቁን አስተማሪ አስደናቂ ንግግሮች መስማት፣ ከኢየሱስ ምሳሌዎች ጠቃሚ ትምህርት መቅሰም፣ ኢየሱስ ያከናወናቸውን አስደናቂ ተአምራት መመልከትና ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጠው የስንብት ማበረታቻ ብርታት ማግኘት በቻለ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ይህ ሁሉ አምልጦታል።

ኒቆዲሞስ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ባለማድረጉ ብዙ ነገር አምልጦታል። ከዚህ ውስጥ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” የሚለው የኢየሱስ ሞቅ ያለ ግብዣ ይገኝበታል። (ማቴዎስ 11:​28-30) ኒቆዲሞስ በቀጥታ ከኢየሱስ ማግኘት የሚችለው ይህ እረፍት አምልጦታል!

አንተስ?

ከ1914 ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ተሾሟል። በእርሱ መገኘት ወቅት ይከናወናሉ ብሎ ከተናገራቸው ነገሮች መካከል “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” የሚለው ትንቢት ይገኝበታል። (ማቴዎስ 24:​14) መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ይህ ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ መከናወን ይገባዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ሥራ ሲካፈሉ ማየት ያስደስተዋል። አንተም በዚህ ሥራ መካፈል ትችላለህ።

ኒቆዲሞስ ኢየሱስ ከአምላክ ዘንድ እንደመጣ ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐንስ 3:​2) አንተም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰህ ሊሆን ይችላል። አኗኗርህን ከመጽሐፍ ቅዱስ መስፈርቶች ጋር ለማስማማት ለውጥ አድርገህ ሊሆን ይችላል። ሌላው ቀርቶ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ትገኝ ይሆናል። በዚህ ረገድ የምታደርገው ጥረት የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም ኒቆዲሞስ ኢየሱስ በአምላክ ተልኮ የመጣ መሆኑን ከማመን አልፎ የሚሄድ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገው ነበር። ‘ራሱን መካድና የመከራውን እንጨት ዕለት ዕለት ተሸክሞ’ ኢየሱስን መከተል ያስፈልገው ነበር።​—⁠ሉቃስ 9:​23

እስቲ ሐዋርያው ጳውሎስ ያለውን ልብ በል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፣ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​1, 2

ለተግባር የሚያንቀሳቅስህን እምነት የምትገነባበት ጊዜ አሁን ነው። ለዚህ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘኸው እውቀት ላይ አሰላስል። ወደ ይሖዋ በመጸለይ እንዲህ ያለ እምነት እንድታሳይ እንዲረዳህ ጠይቀው። የእርሱን እርዳታ ባገኘህ መጠን የሚያድርብህ አድናቆትና ፍቅር ‘ራስህን እንድትክድና የመከራህን እንጨት ተሸክመህ ዕለት ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስን እንድትከተል’ ይገፋፋሃል። ለምን አሁኑኑ እርምጃ አትወስድም?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒቆዲሞስ መጀመሪያ ላይ በቆራጥነት ኢየሱስን በመደገፍ ተናግሯል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒቆዲሞስ ተቃውሞ ቢያጋጥመውም የኢየሱስን አስከሬን በመገነዝ ተባብሯል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግል ጥናትና ጸሎት እርምጃ እንድትወስድ ያበረታሃል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር ሆነህ ለመሥራት ያገኘኸውን መብት ትቀበላለህ?