በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ጽናትንና መንፈሰ ጠንካራነትን አስተምሮናል

ይሖዋ ጽናትንና መንፈሰ ጠንካራነትን አስተምሮናል

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ጽናትንና መንፈሰ ጠንካራነትን አስተምሮናል

አሪስቶተሊስ አፖስቶሊዲስ እንደተናገረው

ፒያቲጎርስክ የተባለው በማዕድን ውኃውና በአስደሳች የአየር ጠባዩ የሚታወቀው የሩሲያ ከተማ በካውካሰስ ተራሮች ሰሜናዊ ግርጌ ይገኛል። በ1929 የግሪክ ስደተኛ ከሆኑ ወላጆች በዚህች ከተማ ተወለድኩ። አሥር ዓመት ከፈጀው የስታሊናዊ የምንጠራ፣ የሽብርና የዘር ማጥፋት ዘመቻ በኋላ ወደ ግሪክ መሄዳችን ግድ ስለነበር እንደገና ለስደት ኑሮ ተዳረግን።

ወደ ፓይሪየስ ግሪክ ከተዛወርን በኋላ “ስደተኛ” መሆን ከጠበቅነው ፈጽሞ የተለየ ነበር። ባይተዋርነት ተሰማን። እኔና ወንድሜ አርስቶትልና ሶቅራጥስ የተባሉትን የሁለት ታዋቂ የግሪክ ፈላስፎች ስም ብንይዝም ሰዎች ብዙውን ጊዜ በስማችን አይጠሩንም ነበር። ሁሉም ሰው ትንንሾቹ ሩሲያውያን እያለ ይጠራን ነበር።

ውዷ እናቴ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሞተች። የቤቱ ምሰሶ ስለነበረች እሷን ማጣታችን በጣም ጎዳን። ታማ በነበረችባቸው ጊዜያት በርካታ የቤት ውስጥ ሥራዎችን አስተምራኛለች። ያኔ ያገኘሁት ሥልጠና በኋለኛው ሕይወቴ ጠቅሞኛል።

ጦርነትና ነጻነት

ጦርነቱ፣ አገሪቱ በናዚ ቁጥጥር ሥር መውደቋና የኅብረ ብሔራቱ ኃይሎች ያለማቋረጥ የሚያወርዱት የቦንብ ናዳ ቀን አልፎ ቀን በተተካ ቁጥር ሕይወታችን አበቃለት ብለን እንድናስብ ያደርገን ነበር። ድህነትና ረሃብ ተስፋፍቶ ነበር። ብዙ ሰዎችም አልቀዋል። ከ11 ዓመቴ ጀምሮ ሦስታችንን ለመደገፍ ስል ከአባቴ ጋር ጠንክሬ መሥራት ነበረብኝ። በግሪክኛ ቋንቋ ችሎታዬ ውስንነት እንዲሁም በጦርነቱና ከጦርነቱ ጋር ተያይዘው በመጡት ችግሮች ምክንያት ሰብዓዊ ትምህርቴን ለማቋረጥ ተገደድኩ።

ጥቅምት 1944 ግሪክ ከጀርመን ቁጥጥር ነፃ ወጣች። ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። ሁኔታው አስቸጋሪና ተስፋ አስቆራጭ በነበረበት በዚያ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣው ብሩህ ጊዜ የሚናገረው ተስፋ ልቤን ነካው። (መዝሙር 37:​29) አምላክ ሰላም በሰፈነበት ምድር ላይ መጨረሻ የሌለው ሕይወት እንደሚሰጠን የሚናገረው ተስፋ ለቁስሌ እውነተኛ ፈውስ ሆነልኝ። (ኢሳይያስ 9:​7) በ1946 እኔና አባቴ ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን በውኃ ጥምቀት አሳየን።

በቀጣዩ ዓመት በፓይሪየስ በተቋቋመው ሁለተኛ ጉባኤ ውስጥ የማስታወቂያ አገልጋይ (በኋላ የመጽሔት አገልጋይ በሚለው ተተክቷል) በመሆን የመጀመሪያ ምድቤን ስቀበል ደስታ ተሰማኝ። ክልላችን ከፓይሪየስ እስከ ኢሉሲስ ያለውን የ50 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ነበር። በዚያን ወቅት በጉባኤው ውስጥ የሚያገለግሉ በመንፈስ የተቀቡ በርካታ ክርስቲያኖች ነበሩ። ከእነርሱ ጋር የመሥራትና ከእነርሱ የመማር መብት አግኝቻለሁ። የስብከቱ ሥራ ይጠይቅባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጥረት የሚገልጹ በርካታ ተሞክሮዎች ስለነበሯቸው ከእነርሱ ጋር መሆን ያስደስተኝ ነበር። እነርሱ ካሳለፉት ሕይወት ማየት እንደሚቻለው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል ከፍተኛ ትዕግሥትና ጽናት ይጠይቃል። (ሥራ 14:​22) በዛሬው ጊዜ በዚህ ቦታ ከ50 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በመኖራቸው ምንኛ ደስተኛ ነኝ!

ያልታሰበ ፈተና

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በፓትራስ ከተማ ከምትኖር አንዲት እሌኒ ከምትባል የደስ ደስ ያላት ቀናተኛ ወጣት ክርስቲያን ጋር ተዋወቅሁ። በ1952 መጨረሻ ተጫጨን። ሆኖም ከጥቂት ወራት በኋላ እሌኒ በጠና ታመመች። ሐኪሞች የአንጎል እብጠት (brain tumor) እንዳለባት ተረዱ። ሁኔታዋ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ወዲያው ቀዶ ሕክምና ማድረግ ነበረባት። የተሟላ ሁኔታ ባልነበረበት በዚያ ወቅት ከብዙ ጥረት በኋላ አቴንስ ውስጥ ከእምነታችን ጋር በመስማማት ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ሐኪም ተገኘ። (ዘሌዋውያን 17:​10-14፤ ሥራ 15:​28, 29) ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሕመሙ ሊያገረሽ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ ቢሆንም ሐኪሞቹ ስለ እጮኛዬ የወደፊት ሁኔታ አዎንታዊ አመለካከት አድሮባቸው ነበር።

በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ነበረብኝ? ሁኔታዎች በመለዋወጣቸው የገባሁትን ቃል ማፍረስና ራሴን ከማንኛውም ግዴታ ነፃ ማድረግ ይኖርብኛል? በፍጹም! እንደማገባት ቃል ገብቻለሁ። ቃሌን ማጠፍ ደግሞ አልፈለግሁም። (ማቴዎስ 5:​37) ከዚህ የተለየ ነገር ለደቂቃ እንኳ ለማሰብ አልዳዳኝም። በታላቅ እህቷ አስታማሚነት ትንሽ ስላገገመች ታኅሣሥ 1954 ተጋባን።

ይሁን እንጂ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሕመሟ እንደገና አገረሸ። ስለዚህ ያው ሐኪም ሌላ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ነበረበት። በዚህ ጊዜ ዕብጠቱን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ሲል አንጎሏ ውስጥ ጥልቀት ያለው ቀዶ ሕክምና ማካሄድ አስፈልጎት ነበር። ይህም ባለቤቴን በከፊል ሽባ ያደረጋት ሲሆን የንግግር ችሎታዋን የሚቆጣጠረው የአንጎሏ ክፍል ክፉኛ ተጎዳ። በዚህ ጊዜ በሁለታችንም ፊት በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ውስብስብ ችግሮች ተደቀኑብን። ውዷ ባለቤቴ ቀላሉን ሥራ እንኳ ማከናወን አቃታት። እያደር እየባሰ የሚሄደው ሁኔታዋ በተለመደው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ጠይቆብናል። ከሁሉም በላይ ግን ከፍተኛ ጽናትና መንፈሰ ጠንካራነትን ጠይቆብናል።

ከእናቴ ያገኘሁት ሥልጠና የጠቀመኝ በዚህ ጊዜ ነበር። በየዕለቱ ጠዋት ተነስቼ ምግብ ውስጥ የሚጨመሩትን ነገሮች ሳዘገጃጅ እሌኒ ደግሞ ታበስል ነበር። ብዙውን ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችንንና በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ችግረኛ ክርስቲያኖችን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶችን ቤታችን እንጋብዝ ነበር። ሁሉም ምግቡን ያደንቁ ነበር! እሌኒና እኔ ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችንም ተጋግዘን ስለምንሠራ ቤታችን ንጹሕና ሥርዓታማ ነው። ይህ እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ለ30 ዓመታት ቀጥሏል።

የአቅም ገደብ ቢኖርም ቅንዓት ማሳየት

ባለቤቴ ለይሖዋ ያላትን ፍቅርና ለአገልግሎቱ የምታሳየውን ቅንዓት ምንም ነገር ሊያቀዘቅዘው እንዳልቻለ መመልከቱ እኔንም ሆነ ሌሎችን እጅግ አበረታትቷል። ከብዙ ጥረት በኋላ ጥቂት ቃላት ተጠቅማ ሐሳቧን መግለጽ ቻለች። እሌኒ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች በመንገድ ላይ ለምታገኛቸው ሰዎች መስበክ ያስደስታታል። ለሥራ በምንቀሳቀስበት ወቅት ከእኔ ጋር ይዣት እሄድና መኪናዬን ሰዎች በሚበዙበት ቦታ አቆማታለሁ። እርሷም የመኪናውን መስኮት ትከፍትና የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎችን እንዲወስዱ መንገደኞቹን ትጋብዛቸዋለች። በአንድ ወቅት በ2 ሰዓት ውስጥ ብቻ 80 መጽሔቶችን አበርክታለች። አብዛኛውን ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን የቆዩ መጽሔቶች ትጠቀምባቸዋለች። እሌኒ በሌሎች የስብከት ዘርፎችም አዘውታሪ ነበረች።

ባለቤቴ የአካል ጉዳተኛ በነበረችባቸው ዓመታት ሁሉ በስብሰባዎች ላይ ከእኔ ተለይታ አታውቅም። በግሪክ በነበረው ስደት ምክንያት ወደ ውጭ አገር ለመሄድ በተገደድንበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር የአውራጃም ሆነ የወረዳ ስብሰባ ፈጽሞ አምልጧት አያውቅም። የአቅም ገደብ ቢኖርባትም በኦስትሪያ፣ በጀርመን፣ በቆጵሮስና በሌሎች አገሮች በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተገኝታለች። እሌኒ በይሖዋ አገልግሎት ያሉኝ ኃላፊነቶች መጨመራቸው አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ቢያደርጉባትም አማርራም ሆነ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠኝ ይገባል የሚል መንፈስ አሳይታ አታውቅም።

በእኔ በኩል ሁኔታው ጽናትንና መንፈሰ ጠንካራነትን ለዘለቄታው አስተምሮኛል። ብዙውን ጊዜ ይሖዋ የእርዳታ እጁን ሲዘረጋልን ተመልክቻለሁ። ወንድሞችና እህቶች እኛን ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ሐኪሞችም በደግነት ደግፈውናል። በእነዚያ አስቸጋሪ ዓመታት ሁኔታው ሙሉ ቀን ለመሥራት ባይፈቅድልኝም ለሕይወት የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች አጥተን አናውቅም። ለይሖዋ አገልግሎትና ፍላጎት ሁልጊዜ ቅድሚያውን እንሰጥ ነበር።​—⁠ማቴዎስ 6:​33

ብዙዎች በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ለመጽናት የቻልነው እንዴት እንደሆነ ይጠይቁናል። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጋችን፣ ልባዊ ጸሎት ማቅረባችን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችንና በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መሳተፋችን ጽናትንና መንፈሰ ጠንካራነትን እንደጨመረልን ይሰማኛል። “በእግዚአብሔር ታመን፣ መልካምንም አድርግ . . . በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ . . . መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን፣ እርሱም ያደርግልሃል” የሚሉትን የመዝሙር 37:​3-5 አበረታች ቃላት ዘወትር እናስታውሳለን። ሌላው በጣም የረዳን ደግሞ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል” የሚለው የመዝሙር 55:​22 ጥቅስ ነው። በአባቱ ላይ ሙሉ ትምክህቱን የጣለ ሕፃን እንደሚያደርገው ሁሉ እኛም ሸክማችንን በይሖዋ ላይ መጣል ብቻ ሳይሆን ለእርሱ እንተወው ነበር።​—⁠ያዕቆብ 1:​6

ሚያዝያ 12, 1987 ባለቤቴ ከቤታችን ፊት ለፊት በመስበክ ላይ እንዳለች አንድ ከባድ የብረት በር ከኋላዋ ተወርውሮ ሲገፈትራት ተንከባልላ በእግረኛው መንገድ ላይ ወደቀች። በጣም በመጎዳቷ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ስልምታ (coma) ውስጥ ገባች። ከዚያም በ1990 መጀመሪያ ላይ በሞት አንቀላፋች።

በሙሉ አቅሜና ችሎታዬ ይሖዋን ማገልገል

በ1960 በኒኬያ ፓይሪየስ የጉባኤ አገልጋይ (በዚያን ጊዜ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች የሚጠራበት ስያሜ ነው) ሆኜ እንዳገለግል ተሹሜ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በፓይሪየስ በሚገኙ በሌሎች ጉባኤዎች የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። የራሴ የሆኑ ልጆች ባይኖሩኝም ብዙ መንፈሳዊ ልጆቼ በእውነት ውስጥ ጸንተው እንዲቆሙ የመርዳት መብት አግኝቻለሁ። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶቹ የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮች፣ አቅኚዎችና የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆነው ያገለግላሉ።

በ1975 ግሪክ ውስጥ ዲሞክራሲ በመስፈኑ የይሖዋ ምሥክሮች በየጫካው መሹለክለክ ሳያስፈልጋቸው በነፃነት የአውራጃ ስብሰባዎችን ማድረግ ቻሉ። አንዳንዶቻችን በውጭ አገር የተካሄዱ የአውራጃ ስብሰባዎችን በማደራጀት በኩል ያገኘነው ልምድ በዚህ ጊዜ ጠቀመን። በዚህም ምክንያት ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የአውራጃ ስብሰባ ኮሚቴዎች ውስጥ የመሥራት መብትና ደስታ አግኝቻለሁ።

በ1979 ከአቴንስ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ቦታ ላይ በግሪክ የመጀመሪያውን ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመሥራት ታቀደ። ይህንን ትልቅ የግንባታ ፕሮጀክት እንዳስተባብርና ሥራውን እንድከታተል ተመደብኩ። ይህም ሥራ ቢሆን ከፍተኛ ጽናትና መንፈሰ ጠንካራነትን የሚጠይቅ ነበር። የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ካላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ለሦስት ዓመታት ያህል መሥራቱ በመካከላችን ጠንካራ የፍቅርና የአንድነት መንፈስ እንዲሰፍን አድርጓል። ይህ ፕሮጀክት ጥሎብኝ ያለፈው ትዝታ በልቤ ውስጥ በማይፋቅ ሁኔታ ተጽፏል።

የእስረኞችን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት

ከጥቂት ዓመታት በኋላ አዲስ የአገልግሎት መስክ ተከፈተልኝ። ከግሪክ ትልልቅ እስር ቤቶች መካከል አንደኛው የሚገኘው በኮሪዳሎስ ባለው የጉባኤያችን ክልል አጠገብ ሲሆን ከሚያዝያ 1991 ጀምሮ በየሳምንቱ ወደዚህ እስር ቤት እየሄድኩ እንድጎበኝ ተመደብኩ። እዚያም ፍላጎት ያላቸውን እስረኞች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስጠና እና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን እንዳካሂድ ተፈቀደልኝ። ብዙዎቹ የአምላክ ቃል ያለውን የመለወጥ ኃይል የሚያረጋግጡ ከፍተኛ ለውጦች አድርገዋል። (ዕብራውያን 4:​12) ይህ የእስር ቤቱን ሠራተኞችም ሆነ ሌሎች እስረኞችን አስደንቋል። መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኋቸው አንዳንዶቹ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የምሥራቹ አስፋፊዎች ሆነው ያገለግላሉ።

ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሦስት አገር ያሰለቹ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠና ነበር። መንፈሳዊ እድገት በማድረጋቸው ወደ ጥናታቸው ሲመጡ ጺማቸውን ተላጭተው፣ ፀጉራቸውን አበጥረውና በግሪክ በጣም በሚወብቀው የነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ሸሚዝና ከረባት አስረው ነበር! የእስር ቤቱ ኃላፊ፣ ዋናው ተቆጣጣሪና አንዳንድ ሠራተኞች ይህንን ክስተት ለመመልከት ከየቢሯቸው እየሮጡ ወጥተዋል። ዓይናቸውን ማመን አልቻሉም!

ሌላው አበረታች ተሞክሮ የተገኘው ደግሞ በሴቶቹ የእስረኛ ካምፕ ውስጥ ነበር። በካምፑ ውስጥ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከስሳ የእድሜ ልክ እስራት ከተፈረደባት አንዲት ሴት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ተጀመረ። ይህች ሴት የምትታወቀው በዓመፀኝነቷ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ትማረው የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ግልጽ የሆኑ ለውጦች እንድታደርግ ገፋፍቷት ስለነበር ብዙዎች ያደረገችው ለውጥ ከአንበሳ መሰል ባሕርይ ወደ በግ መሰል ባሕርይ የመለወጥ ያህል እንደሆነ ተናግረዋል! (ኢሳይያስ 11:​6, 7) ብዙም ሳትቆይ የእስር ቤቱን ኃላፊ አክብሮትና አመኔታ አተረፈች። ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርጋ ራሷን ለይሖዋ ስትወስን በማየቴ ተደሰትኩ።

የአካል ጉዳተኞችንና በእድሜ የገፉትን መርዳት

ባለቤቴ ከሕመም ጋር ያደረገችውን የረጅም ዓመታት ትግል መመልከቴ በመካከላችን ለሚገኙት የታመሙና በእድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ እንዳስብ አድርጎኛል። ጽሑፎቻችን ሁልጊዜ እንደነዚህ ላሉት ግለሰቦች ፍቅራዊ ድጋፍ እንድናደርግ የሚያበረታቱ ሐሳቦችን ይዘው ስለሚወጡ ፍላጎቴ ተነሳሳ። እንደነዚህ ያሉትን ጽሑፎች ውድ አድርጌ ስለምመለከታቸው ማሰባሰብ ጀመርኩ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ “በእድሜ የገፉትንና መከራ የደረሰባቸውን መርዳት” ከሚለው የሐምሌ 15, 1962 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እትም ጀምሮ በአንድ ማኅደር ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ገፆች አጠራቀምኩ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ እያንዳንዱ ጉባኤ የታመሙትንና በእድሜ የገፉትን ለመርዳት የተቀናጀ ጥረት ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማሉ።​—⁠1 ዮሐንስ 3:​17, 18

የጉባኤያችን ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ያሉትን የታመሙና በእድሜ የገፉ ወንድሞች ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞችና እህቶችን አሰባሰቡ። ፈቃደኛ ሠራተኞቹን ቀን ቀን መርዳት የሚችሉ፣ ማታ ማታ መርዳት የሚችሉ፣ ትራንስፖርት ማቅረብ የሚችሉና በማንኛውም ሰዓት እርዳታ መስጠት የሚችሉ በማለት በቡድን በቡድን ከፋፈልናቸው። መጨረሻ ላይ የተገለጸው ቡድን እንደ ፈጥኖ ደራሽ ጓድ ነበር።

እነዚህ ጥረቶች ያስገኙት ውጤት አበረታች ነበር። ለምሳሌ ያህል በየቀኑ ጉብኝት የሚደረግላት አንዲት ለብቻዋ የምትኖር እህት በአንድ የጉብኝት ወቅት ራሷን ስታ ወለሉ ላይ ወድቃ ተገኘች። ወዲያው ሁኔታውን በአቅራቢያዋ ለምትኖር መኪና ላላት አንዲት እህት ገለጽንላት። እህት በ10 ደቂቃ ውስጥ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ሆስፒታል ወሰደቻት! ሐኪሞቹ ይህ ሕይወቷን እንዳተረፈው ተናግረዋል።

የታመሙትና በእድሜ የገፉትም ለቡድኑ አባላት የሚያሳዩት የአመስጋኝነት ስሜት በጣም ያበረታታል። ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ጋር በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ከአሁኑ ፍጹም በተለየ ሁኔታ የመኖር ተስፋ ያለን መሆኑ በእጅጉ ያስደስታል። እነዚህ ወንድሞች በመከራቸው ወቅት ለመጽናት የሚያስችላቸው እርዳታ ተደርጎላቸው እንደነበረም ማወቁ ሌላው ሽልማት ነው።

ጽናት በረከት አስገኘ

በአሁኑ ጊዜ በፓይሪየስ ከሚገኙት ጉባኤዎች ውስጥ በአንዱ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ። የእድሜ መግፋትና የጤና ችግሮች ቢኖሩብኝም በጉባኤው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።

ባለፉት ዓመታት የገጠሙኝ አስቸጋሪ፣ ፈታኝና ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ከፍተኛ ጥንካሬንና ጽናትን ጠይቀውብኛል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁልጊዜ እነዚህን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችል ኃይል ይሰጠኛል። “እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፣ አቤቱ፣ ምሕረትህ ረዳኝ። አቤቱ፣ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት” የሚሉትን የመዝሙራዊ ቃላት እውነተኝነት በተደጋጋሚ አረጋግጫለሁ።​—⁠መዝሙር 94:​18, 19

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከእሌኒ ጋር በ1957 ሁለተኛው ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1969 ኑረንበርግ ጀርመን ውስጥ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታመሙትንና በእድሜ የገፉትን የረዱ ወንድሞችና እህቶች ቡድን