የሉቃስ ወንጌል 16:1-31

  • የዓመፀኛው መጋቢ ምሳሌ (1-13)

    • ‘በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በብዙ ነገርም ታማኝ ነው’ (10)

  • ሕጉና የአምላክ መንግሥት (14-18)

  • የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ምሳሌ (19-31)

16  ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ሀብታም ሰው አንድ መጋቢ* ነበረው፤ ይህ ሰው፣ መጋቢው ንብረቱን እያባከነበት እንዳለ የሚገልጽ ክስ ደረሰው።  ስለዚህ መጋቢውን ጠራውና ‘ይህ ስለ አንተ የምሰማው ነገር ምንድን ነው? ከዚህ በኋላ ቤቱን ማስተዳደር ስለማትችል በመጋቢነት ስትሠራበት የነበረውን የሒሳብ መዝገብ አስረክበኝ’ አለው።  በዚህ ጊዜ መጋቢው በልቡ እንዲህ አለ፦ ‘ጌታዬ የመጋቢነት ኃላፊነቴን ሊወስድብኝ ነው፤ ታዲያ ምን ባደርግ ይሻላል? እንዳልቆፍር አቅም የለኝም፤ እንዳልለምን ያሳፍረኛል።  ቆይ፣ ምን እንደማደርግ አውቃለሁ! ከመጋቢነት ኃላፊነቴ ስነሳ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ አንድ ነገር አደርጋለሁ።’  ከዚያም ከጌታው የተበደሩትን ሰዎች አንድ በአንድ በመጥራት የመጀመሪያውን ‘ከጌታዬ የተበደርከው ምን ያህል ነው?’ አለው።  እሱም ‘አንድ መቶ የባዶስ መስፈሪያ* የወይራ ዘይት’ ሲል መለሰለት። መጋቢውም ‘የውል ሰነድህ ይኸውልህ፤ ቁጭ በልና ቶሎ ብለህ 50 ብለህ ጻፍ’ አለው።  ቀጥሎም ሌላውን ‘አንተስ፣ የተበደርከው ምን ያህል ነው?’ አለው። እሱም ‘አንድ መቶ የቆሮስ መስፈሪያ* ስንዴ’ አለው። መጋቢውም ‘የውል ሰነድህ ይኸውልህ፤ 80 ብለህ ጻፍ’ አለው።  ጌታውም መጋቢው ዓመፀኛ ቢሆንም እንኳ አርቆ በማሰብ* ባደረገው ነገር አደነቀው፤ ምክንያቱም የዚህ ሥርዓት* ልጆች በእነሱ ትውልድ ካሉት ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ከብርሃን ልጆች+ ይበልጥ ብልሆች ናቸው።  “ደግሞም እላችኋለሁ፦ በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ፤+ እነሱም የዓመፅ ሀብት ሲያልቅ በዘላለማዊ መኖሪያ ይቀበሏችኋል።+ 10  በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ ሰው በብዙ ነገርም ታማኝ ነው፤ በትንሽ ነገር ታማኝ ያልሆነ ሰው ደግሞ በብዙ ነገርም ታማኝ አይሆንም። 11  ስለዚህ በዓመፅ ሀብት ታማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ እውነተኛውን ሀብት ማን በአደራ ይሰጣችኋል? 12  የሌላ ሰው በሆነው ነገር ታማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ ለእናንተ የታሰበውን ማን ይሰጣችኋል?+ 13  ለሁለት ጌቶች ባሪያ መሆን የሚችል አገልጋይ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድ ጊዜ ባሪያ መሆን አትችሉም።”+ 14  ገንዘብ ወዳድ የሆኑት ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሲናገር ሰምተው ያፌዙበት ጀመር።+ 15  በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ በሰዎች ፊት ጻድቅ መስላችሁ ትቀርባላችሁ፤+ አምላክ ግን ልባችሁን ያውቃል።+ በሰዎች ፊት ከፍ ተደርጎ የሚታየው ነገር በአምላክ ፊት አስጸያፊ ነውና።+ 16  “ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል እስከ ዮሐንስ ድረስ ሲነገሩ ቆይተዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአምላክ መንግሥት ምሥራች እየታወጀ ነው፤ የተለያዩ ዓይነት ሰዎችም ወደዚያ ለመግባት ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው።+ 17  እንደ እውነቱ ከሆነ ከሕጉ የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም ከምትቀር ሰማይና ምድር ቢያልፉ ይቀላል።+ 18  “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ ባሏ የፈታትንም ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።+ 19  “አንድ ሀብታም ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ሐምራዊ* ልብስና በፍታ ይለብስ የነበረ ከመሆኑም በላይ ዕለት ተዕለት በደስታና በቅንጦት ይኖር ነበር። 20  ይሁን እንጂ እዚህ ሰው ደጃፍ ላይ እያመጡ የሚያስቀምጡት መላ ሰውነቱን ቁስል የወረሰው አልዓዛር የሚባል አንድ ለማኝ ነበር፤ 21  እሱም ከሀብታሙ ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ በልቶ ለመጥገብ ይመኝ ነበር። ውሾችም* ሳይቀር እየመጡ ቁስሉን ይልሱ ነበር። 22  ከጊዜ በኋላ ለማኙ ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ* ወሰዱት። “ሀብታሙም ሰው ሞተና ተቀበረ። 23  በመቃብርም* ሆኖ እየተሠቃየ ሳለ አሻቅቦ ሲመለከት ከሩቅ አብርሃምንና በእቅፉ ያለውን አልዓዛርን አየ። 24  በዚህ ጊዜ ድምፁን ከፍ አድርጎ ‘አብርሃም አባት ሆይ፣ በዚህ የሚንቀለቀል እሳት እየተሠቃየሁ ስለሆነ እባክህ ራራልኝና አልዓዛር የጣቱን ጫፍ ውኃ ውስጥ ነክሮ ምላሴን እንዲያቀዘቅዝልኝ ላከው’ አለ። 25  አብርሃም ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ፣ አንተ በሕይወት ዘመንህ መልካም ነገሮችን ሁሉ እንደተቀበልክ፣ አልዓዛር ግን መጥፎ ነገሮች እንደደረሱበት አስታውስ። አሁን ግን እሱ እዚህ ሲጽናና አንተ ትሠቃያለህ። 26  ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ከእኛ ወደ እናንተ መሻገር የሚፈልጉ መሻገር እንዳይችሉ እንዲሁም ሰዎች ከእናንተ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ትልቅ ገደል ተደርጓል።’ 27  በዚህ ጊዜ ሀብታሙ ሰው እንዲህ አለ፦ ‘አባት ሆይ፣ እንደዚያ ከሆነ አልዓዛርን ወደ አባቴ ቤት እንድትልከው እለምንሃለሁ፤ 28  አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ እነሱም ወደዚህ የሥቃይ ስፍራ እንዳይገቡ በሚገባ ይመሥክርላቸው።’ 29  አብርሃም ግን ‘ሙሴና ነቢያት አሉላቸው፤ እነሱን ይስሙ’ አለው።+ 30  እሱም ‘አይ፣ እንደሱ አይደለም፤ አብርሃም አባት ሆይ፣ አንድ ሰው ከሞት ተነስቶ ወደ እነሱ ቢሄድ ንስሐ ይገባሉ’ አለ። 31  አብርሃም ግን ‘ሙሴንና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ+ አንድ ሰው ከሞት ቢነሳም አምነው አይቀበሉም’ አለው።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የቤት አስተዳዳሪ።”
አንድ የባዶስ መስፈሪያ 22 ሊትር ነው። ለ14ን ተመልከት።
አንድ የቆሮስ መስፈሪያ 220 ሊትር (170 ኪሎ ግራም ገደማ ስንዴ) ነው። ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በብልሃት፤ በልባምነት።”
ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
እንዲህ ዓይነት ቀለም ያለው ልብስ ከሀብት፣ ከክብርና ከሥልጣን ጋር የተያያዘ ነበር።
በአይሁዳውያን ዘንድ ውሻ ርኩስ እንስሳ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።
ልዩ ሞገስ ማግኘትን ያመለክታል።
ወይም “በሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።