በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፉ!

የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፉ!

“ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11

መዝሙሮች፦ 12, 150

1, 2. እያንዳንዳችን የትኛውን እውነታ አምነን መቀበል አለብን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ዲያብሎስ ‘ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት የለውም እንዲሁም የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላሉ’ የሚል ክስ ሰንዝሯል። ታዲያ ሰይጣን የተናገረው ነገር ትክክል ነው? ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የመረጡ ሰዎች ለዘላለም መኖር ቢችሉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስቲ አስብ። ከይሖዋ አገዛዝ ነፃ ሆነው የተሻለ ሕይወት መምራት ይችሉ ነበር? አንተስ ብትሆን ሙሉ በሙሉ ከአምላክ አገዛዝ ነፃ ሆነህ ለዘላለም መኖር ብትችል ይበልጥ ደስተኛ እንደምትሆን ይሰማሃል?

2 እነዚህን ጥያቄዎች ማንም ሊመልስልህ አይችልም። እያንዳንዳችን ይህን ጉዳይ በሚገባ ልናስብበት ይገባል። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት እንዳለው እንድንገነዘብ ያደርገናል። ከሁሉ የተሻለው አገዛዝ የእሱ አገዛዝ ነው። በመሆኑም የእሱን ሉዓላዊነት በሙሉ ልባችን መደገፍ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብለን እንድናምን የሚያደርጉ ምክንያቶችን ይጠቅሳል። እስቲ በመጀመሪያ ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት አለው እንድንል የሚያደርጉንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች እንመልከት።

ይሖዋ የመግዛት መብት አለው

3. ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክና ፈጣሪ በመሆኑ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። (1 ዜና 29:11፤ ሥራ 4:24) ዮሐንስ በራእይ ያያቸው ከክርስቶስ ጋር በሰማይ አብረው የሚገዙት 144,000 ሰዎች እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።” (ራእይ 4:11) አዎ፣ ይሖዋ ሁሉንም ነገር ስለፈጠረ የሰው ልጆችንም ሆነ መንፈሳዊ ፍጡራንን የመግዛት ሙሉ መብት አለው።

4. የአምላክን ሉዓላዊነት መቃወም የመምረጥ ነፃነትን አላግባብ መጠቀም ነው የምንለው ለምንድን ነው?

4 ሰይጣን የፈጠረው ምንም ነገር የለም። በመሆኑም ጽንፈ ዓለምን የመግዛት መብት ሊኖረው አይችልም። እሱም ሆነ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በይሖዋ ላይ ማመፃቸው ትዕቢተኞች እንደሆኑ ያሳያል። (ኤር. 10:23) የሰው ልጆች ነፃ ምርጫ ያላቸው ፍጥረታት ናቸው ሲባል በአምላክ አገዛዝ ላይ የማመፅ መብት አላቸው ማለት ነው? አይደለም። እርግጥ ነው፣ ሰዎች የመምረጥ ነፃነት ያላቸው መሆኑ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ብዙ ምርጫዎች ለማድረግ ያስችላቸዋል። ሆኖም ፈጣሪያቸውና ሕይወት ሰጪያቸው በሆነው አምላክ ላይ የማመፅ ነፃነት አይሰጣቸውም። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በይሖዋ ላይ ማመፅ የመምረጥ ነፃነትን አላግባብ መጠቀም ነው። ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋ አመራር ያስፈልገናል።

5. የይሖዋ ውሳኔዎች ፍትሕ የሚንጸባረቅባቸው እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት አለው የምንልበት ሌላም ምክንያት አለ። ሥልጣኑን የሚጠቀምበት ፍጹም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው። ይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በምድር ላይ ታማኝ ፍቅር የማሳየው፣ ደግሞም ፍትሕና ጽድቅ የማሰፍነው እኔ ይሖዋ [ነኝ፤] . . . በእነዚህ ነገሮች ደስ እሰኛለሁና።” (ኤር. 9:24) ይሖዋ ትክክልና ፍትሐዊ የሆነውን ነገር ለመለየት ሰዎች ያወጡትን ሕግ መመልከት አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር ለማወቅ የሚያስችል መሥፈርት ያወጣው እሱ ራሱ ነው። በመሆኑም ፍጹም በሆነው የፍትሕ መሥፈርቱ ላይ የተመሠረተ ሕግ ለሰው ልጆች ሰጥቷል። “ጽድቅና ፍትሕ [የዙፋኑ] መሠረት ናቸው፤” ስለሆነም ሕጎቹ፣ መሠረታዊ ሥርዓቶቹና ውሳኔዎቹ በሙሉ ትክክል እንደሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 89:14፤ 119:128) ሰይጣን ‘የይሖዋ አገዛዝ ፍትሐዊ አይደለም’ የሚል ክስ ቢሰነዝርም እሱ ራሱ በዓለም ላይ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ አልቻለም።

6. ይሖዋ ዓለምን የማስተዳደር መብት አለው እንድንል የሚያደርገን አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

6 ከዚህም ሌላ፣ ይሖዋ ጽንፈ ዓለሙን ለማስተዳደር የሚያስችል እውቀትና ጥበብ ስላለው ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት አለው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ልጁ ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ሐኪሞች ሊያድኗቸው ያልቻሏቸውን ሕመምተኞች እንዲፈውስ አስችሎታል። (ማቴ. 4:23, 24፤ ማር. 5:25-29) ይህ ለእኛ ተአምር ቢሆንም ለይሖዋ ግን ተአምር አይደለም። የሰውነታችንን አሠራር በሚገባ ያውቃል፤ እንዲሁም የደረሰብንን ማንኛውንም ዓይነት ጉዳት መፈወስ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የሞቱትን የማስነሳትና የተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይደርሱ የመከላከል ችሎታ አለው።

7. የይሖዋ ጥበብ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ካለው ጥበብ በጣም የላቀ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

7 በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም የእርስ በርስ ግጭቶችንም ሆነ በብሔራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ማስወገድ አልቻለም። ዓለም አቀፍ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ጥበብ ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ኢሳ. 2:3, 4፤ 54:13) እኛም ስለ ይሖዋ እውቀትና ጥበብ ይበልጥ ባወቅን መጠን በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ብሎ እንደጻፈው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ይሰማናል፦ “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!”—ሮም 11:33

የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ ነው

8. ይሖዋ ስለሚገዛበት መንገድ ስታስብ ምን ይሰማሃል?

8 እስካሁን እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ የመግዛት መብት እንዳለው ይናገራል። በተጨማሪም የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ ነው የምንለው ለምን እንደሆነ ይገልጻል። አንዱ ምክንያት የይሖዋ አገዛዝ በፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው። ይሖዋ “መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ እንደሆነ ስናስብ ይበልጥ ወደ እሱ ለመቅረብ እንነሳሳለን። (ዘፀ. 34:6) አምላክ አገልጋዮቹን የሚይዛቸው በአክብሮት ነው። እኛ ለራሳችን ከምናስበው በላይ አምላክ ለእኛ ያስብልናል። ዲያብሎስ፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን መልካም ነገር ይነፍጋቸዋል የሚል ክስ ቢሰነዝርም እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። እንዲያውም ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖረን ሲል ውድ ልጁን እንኳ ሰጥቶናል!—መዝሙር 84:11ን እና ሮም 8:32ን አንብብ።

9. ይሖዋ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብ እንዴት እናውቃለን?

9 ይሖዋ ለሕዝቡ አሳቢነት የሚያሳየው በቡድን ደረጃ ብቻ አይደለም። ለእያንዳንዱ ግለሰብም ትኩረት ይሰጣል። እስቲ በጥንት ዘመን የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ይሖዋ ለሦስት መቶ ዘመናት ያህል መሳፍንት በማስነሳት የእስራኤልን ብሔር ይመራ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በጠላቶቻቸው ላይ ድል ያቀዳጃቸው ነበር። ይሁንና ከፍተኛ አለመረጋጋት በነበረበት በዚያ ዘመንም እንኳ ይሖዋ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዷ ሩት የተባለች እስራኤላዊት ያልሆነች ሴት ነች። ሩት የሐሰት አምልኮን ትታ ይሖዋን ለማምለክ ስትል ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍላለች። ይሖዋ ሩትን ባልና ወንድ ልጅ በመስጠት ባርኳታል። ይሁንና ያገኘችው በረከት ይህ ብቻ አይደለም። መሲሑ የመጣው በልጇ የዘር ሐረግ በኩል ነው። በተጨማሪም ይሖዋ የሕይወት ታሪኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በስሟ የተጠራ መጽሐፍ ላይ እንዲሰፍር አድርጓል። ሩት ትንሣኤ በምታገኝበት ወቅት ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ስታውቅ ምን ሊሰማት እንደሚችል አስብ!—ሩት 4:13፤ ማቴ. 1:5, 16

10. የይሖዋ አገዛዝ የማያፈናፍን አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

10 የይሖዋ አገዛዝ ጭቆና ያለበት ወይም የማያፈናፍን አይደለም። አገዛዙ ለሰዎች ነፃነት የሚሰጥና ደስታ የሚያስገኝ ነው። (2 ቆሮ. 3:17) ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ሞገስና ግርማ [በአምላክ ፊት] ናቸው፤ ብርታትና ደስታ እሱ በሚኖርበት ስፍራ ይገኛሉ።” (1 ዜና 16:7, 27) በተመሳሳይም መዝሙራዊው ኤታን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እልልታ የሚያውቁ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። ይሖዋ ሆይ፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች በፊትህ ብርሃን ይመላለሳሉ። በስምህ ቀኑን ሙሉ ሐሴት ያደርጋሉ፤ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ።”—መዝ. 89:15, 16

11. የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

11 በይሖዋ ጥሩነት ላይ አዘውትረን ማሰላሰላችን የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። “በሌላ ቦታ አንድ ሺህ ቀን ከመኖር በቅጥር ግቢዎችህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል!” በማለት የተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ይሰማናል። (መዝ. 84:10) ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል፤ ይህንንም አትረፍርፎ ይሰጠናል። ይሖዋ ያወጣቸው መሥፈርቶች በሙሉ እኛን የሚጠቅሙ ናቸው። ይሖዋ የሚጠብቅብንን ነገር ማድረግ አንዳንድ መሥዋዕትነት መክፈል ቢጠይቅብንም እንኳ እሱን መታዘዛችን ደስታ ያስገኝልናል።—ኢሳይያስ 48:17ን አንብብ።

12. የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

12 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በኋላ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የሚያምፁ ሰዎች እንደሚኖሩ ይናገራል። (ራእይ 20:7, 8) እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ምን ሊሆን ይችላል? ከእስር የተፈታው ዲያብሎስ የሰው ልጆችን የራስ ወዳድነት ፍላጎት በመጠቀም ሊያስታቸው ይሞክራል። ሰይጣን ሁልጊዜም እንዲህ ሲያደርግ ኖሯል። ይሖዋን ሳይታዘዙ ለዘላለም መኖር እንደሚቻል ሰዎችን ለማሳመን ይሞክር ይሆናል። ይህ እውነት ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሁንና ‘እንዲህ ዓይነቱን ውሸት ለማመን እፈተን ይሆን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ይሖዋን የምንወደው ከሆነ እንዲሁም በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ እንደሆነና የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት እንዳለው አምነን ከተቀበልን ይህን ውሸት ለማመን ጨርሶ አይዳዳንም። ፍቅር ከሚንጸባረቅበት የይሖዋ አገዛዝ ውጪ በጭራሽ መኖር አንፈልግም።

የአምላክን ሉዓላዊነት በታማኝነት ደግፉ

13. የአምላክን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

13 የይሖዋን ሉዓላዊነት በሙሉ ልባችን መደገፋችን ተገቢ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ከላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ የመግዛት መብት አለው፤ እንዲሁም አገዛዙ ከሁሉ የተሻለ ነው። ንጹሕ አቋማችንን በመጠበቅና አምላክን በታማኝነት በማገልገል የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ እንችላለን። የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችልበት ሌላ መንገድ አለ? አዎ፣ ይሖዋን ለመምሰል ጥረት በማድረግ ይህን ማሳየት እንችላለን። ማንኛውንም ነገር በይሖዋ መንገድ በማከናወን የይሖዋን አገዛዝ እንደምንወድና እንደምንደግፍ እናሳያለን።—ኤፌሶን 5:1, 2ን አንብብ።

14. የጉባኤ ሽማግሌዎችና የቤተሰብ ራሶች ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ምንጊዜም ሥልጣኑን የሚጠቀመው ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ እንደሆነ ይገልጻል። የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚወዱ የቤተሰብ ራሶችና የጉባኤ ሽማግሌዎችም የራሳቸው ሉዓላዊነት ያላቸው ይመስል ከሌሎች ብዙ አይጠብቁም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለመምሰል ይጥራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ የአምላክንና የልጁን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርጓል። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ ሌሎች እንዲሸማቀቁ ከማድረግ ወይም ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ ተማጽኗቸዋል። (ሮም 12:1፤ ኤፌ. 4:1፤ ፊልሞና 8-10) ይሖዋ ሌሎችን የሚይዘው በዚህ መንገድ ነው። በመሆኑም የይሖዋን አገዛዝ የሚወዱና የሚደግፉ ሰዎች የእሱን ምሳሌ መከተል አለባቸው።

15. ሥልጣን ያላቸውን በማክበር የይሖዋን አገዛዝ እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 የይሖዋን አገዛዝ እንደምንደግፍ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ይሖዋ ሥልጣን ከሰጣቸው ሰዎች ጋር በመተባበር ነው። አንድ ውሳኔ የተደረገበት ምክንያት ባይገባን ወይም በውሳኔው ባንስማማም እንኳ ቲኦክራሲያዊውን ሥርዓት መደገፍ ይኖርብናል። ዓለም እንዲህ ያለው ነገር አይዋጥለትም፤ በይሖዋ አገዛዝ ሥር ለመኖር ግን ይህን ማድረግ አስፈላጊ ነው። (ኤፌ. 5:22, 23፤ 6:1-3፤ ዕብ. 13:17) አምላክ እንዲህ እንድናደርግ የሚያዘን ለእኛው አስቦ ስለሆነ ይህን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው።

16. የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የአምላክን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

16 የግል ውሳኔዎች በምናደርግበት ጊዜም የአምላክን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ ለእያንዳንዱ ነገር ቀጥተኛ መመሪያ አይሰጥም። ከዚህ ይልቅ የእሱን አስተሳሰብ እንድናውቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ልብስ መልበስ እንዳለባቸው ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። ከዚህ ይልቅ ልከኛ የሆነ እንዲሁም ለክርስቲያኖች የሚገባ ዓይነት አለባበስና አጋጌጥ እንዲኖረን ይመክረናል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) በተጨማሪም ሌሎችን እንዳናሰናክልና እነሱን ቅር የሚያሰኝ ውሳኔ እንዳናደርግ ያሳስበናል። (1 ቆሮ. 10:31-33) በራሳችን ፍላጎት ላይ ብቻ ሳይሆን በይሖዋ አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተን ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ የእሱን አገዛዝ እንደምንወድና እንደምንደግፍ እናሳያለን።

ውሳኔ በምታደርጉበት ጊዜም ሆነ በቤተሰብ ሕይወታችሁ የአምላክን ሉዓላዊነት ደግፉ (አንቀጽ 16-18ን ተመልከት)

17, 18. ባለትዳሮች የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደሚደግፉ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ክርስቲያን ባለትዳሮች ይሖዋን በመምሰል ሉዓላዊነቱን መደገፍ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። የትዳር ሕይወት ከጠበቃችሁት በላይ ተፈታታኝ ቢሆንባችሁ አልፎ ተርፎም ከባድ ችግሮች ቢያጋጥሟችሁ ምን ታደርጋላችሁ? ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት መለስ ብላችሁ አስቡ። ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር እንደ ባል ሆኖላቸው እንደነበር ተናግሯል። (ኢሳ. 54:5፤ 62:4) ይሁንና እስራኤላውያን ይሖዋን በተደጋጋሚ አሳዝነውት ነበር። ከእነሱ ጋር የነበረው ግንኙነት ሰላም እንዳጣ ትዳር ሆኖ ነበር። ሆኖም ተስፋ ቆርጦ ይህን “ትዳር” ለማፍረስ አልቸኮለም። በተደጋጋሚ ምሕረት ያሳያቸው ሲሆን ከእነሱ ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ታማኝ ሆኗል። (መዝሙር 106:43-45ን አንብብ።) ይሖዋ እንዲህ ያለ ታማኝ ፍቅር ማሳየቱ ይበልጥ ወደ እሱ እንድንቀርብ አያነሳሳንም?

18 የይሖዋን መንገድ የሚወዱ ባለትዳሮችም እሱን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። የትዳር ሕይወት ተፈታታኝ ሲሆንባቸው ከትዳሩ ለመገላገል ሲሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መንገዶችን አይፈላልጉም። ይሖዋ እንዳጣመራቸውና እርስ በርስ ‘ተጣብቀው’ እንዲኖሩ እንደሚፈልግ ይገነዘባሉ። አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ፈቶ ሌላ ሰው ማግባት የሚችልበት ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የፆታ ብልግና ነው። (ማቴ. 19:5, 6, 9) ክርስቲያኖች ትዳራቸው ስኬታማ እንዲሆን የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ የይሖዋን የጽድቅ አገዛዝ እንደሚደግፉ ማሳየት ይችላሉ።

19. ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን አልፎ አልፎ ይሖዋን የሚያሳዝን ነገር ማድረጋችን አይቀርም። እሱም ይህን ስለሚያውቅ በክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ይቅርታ የምናገኝበት ዝግጅት አድርጎልናል። በመሆኑም ይሖዋን የሚያሳዝን ነገር ስናደርግ ይቅር እንዲለን መጠየቅ ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) ነጋ ጠባ ራሳችንን ከመኮነን ይልቅ ከስህተታችን ለመማር ጥረት ማድረግ አለብን። ወደ ይሖዋ ከቀረብን ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም ካለንበት ሁኔታ እንድናገግምና ወደፊት ተመሳሳይ ነገር ሲያጋጥመን በተሻለ መንገድ መወጣት እንድንችል ይረዳናል።—መዝ. 103:3

20. ዛሬ ነገ ሳንል የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ ያለብን ለምንድን ነው?

20 በአዲሱ ዓለም ሁሉም ሰዎች ለይሖዋ ሉዓላዊነት ይገዛሉ፤ እንዲሁም የእሱን የጽድቅ መንገዶች ይማራሉ። (ኢሳ. 11:9) ይሁንና በአሁኑ ጊዜም እንኳ የይሖዋን የጽድቅ መንገዶች እየተማርን ነው። ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እልባት ያገኛል። ንጹሕ አቋማችንን በመጠበቅ፣ በታማኝነት ይሖዋን በማገልገልና በሁሉም የኑሯችን ዘርፍ እሱን ለመምሰል በመጣር ዛሬ ነገ ሳንል የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።