በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል

ይሖዋ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል

“የመጽናናት ሁሉ አምላክ . . . በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።” —2 ቆሮ. 1:3, 4

መዝሙሮች፦ 33, 41

1, 2. ይሖዋ መከራ በሚደርስብን ወቅት የሚያጽናናን እንዴት ነው? የአምላክ ቃል በዚህ ረገድ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

አንድ ያላገባ ወጣት ወንድም “የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” በሚለው በ1 ቆሮንቶስ 7:28 ላይ በሚገኘው ሐሳብ ላይ ሲያሰላስል በአእምሮው ውስጥ አንዳንድ ጥያቄዎች ተፈጠሩ። በመሆኑም ባለትዳር የሆነን በዕድሜ የገፋ የጉባኤ ሽማግሌ ቀርቦ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘መከራ’ ምንድን ነው? ደግሞስ ካገባሁ ይህን ‘መከራ’ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” ሽማግሌው ጥያቄውን ከመመለሱ በፊት ይሖዋ ‘በሚደርስብን መከራ [“ፈተና፣” ግርጌ] ሁሉ የሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ እንደሆነ የሚገልጸውን ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ሐሳብ ጠቀሰለት።—2 ቆሮ. 1:3, 4

2 በእርግጥም ይሖዋ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ የሚያጽናናን አፍቃሪ አባታችን ነው። አንተም ምናልባት በአንድ ወቅት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ አምላክ በቃሉ አማካኝነት ድጋፍ እና መመሪያ ሰጥቶህ እንደነበረ ታስታውስ ይሆናል። ይሖዋ፣ እንደ ጥንት አገልጋዮቹ ሁሉ እኛም የተሻለውን ነገር እንድናገኝ ይፈልጋል።—ኤርምያስ 29:11, 12ን አንብብ።

3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 የተለያዩ ችግሮች ወይም ፈተናዎች ሲያጋጥሙን መንስኤው ምን እንደሆነ ማወቃችን ችግሩን በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም እንደሚረዳን ግልጽ ነው። ከትዳር ወይም ከቤተሰብ ሕይወት ጋር በተያያዘ የሚደርስብንን መከራ በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ጳውሎስ እንደተናገረው ‘በሥጋችን ላይ መከራ’ ሊደርስብን የሚችለው ለምንድን ነው? በጥንት ጊዜ የኖሩትንም ሆነ በዘመናችን ያሉትን አንዳንድ ሰዎች ምሳሌ መመርመራችን መጽናኛ እንድናገኝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መቋቋም እንድንችል ይረዳናል።

‘በሥጋችን ላይ የሚደርሱ መከራዎች’

4, 5. ባልና ሚስቶች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንዲደርስ’ ሊያደርጉ የሚችሉ ምን ሁኔታዎች አሉ?

4 ይሖዋ ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ወደ አዳም አመጣት፤ በዚህ መንገድ የመጀመሪያውን ትዳር አቋቋመ። ከዚያም እንዲህ አለ፦ “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍ. 2:24) እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን ትዳር በምንመሠርትበት ጊዜ አንዳንድ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። (ሮም 3:23) ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሴት ከማግባቷ በፊት ለወላጆቿ ሥልጣን ትገዛ ነበር። በትዳር ውስጥ ግን ባል የሚስቱ ራስ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮ. 11:3) ለትዳር ሕይወት አዲስ የሆኑ አንዳንድ ባሎችና ሚስቶች ከራስነት ሥልጣን ጋር በተያያዘ የተሰጣቸውን ድርሻ መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። የአምላክ ቃል እንደሚናገረው፣ ሚስት በወላጆቿ ሳይሆን በባሏ ሥልጣን ሥር እንደሆነች መቀበል ይኖርባታል። በዚህ የተነሳ ከአማቾች ጋር አለመግባባት ይፈጠር ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ለአዲሶቹ ተጋቢዎች ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል።

5 ሚስትየው ስታረግዝ ደግሞ ውጥረት የሚያስከትሉ አዳዲስ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ልጅ ማግኘት በራሱ በጣም የሚያስደስት ነገር ቢሆንም በእርግዝና ወቅት ወይም ከዚያ በኋላ ሊያጋጥም የሚችለውን ከጤና ጋር የተያያዘ ችግር ማሰባቸው ደስታቸውን ሊያደበዝዘው ይችላል። በተጨማሪም ልጅ መውለድ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደሚያስከትል የታወቀ ነው። ልጁ ከተወለደ በኋላ ባልና ሚስቱ ተጨማሪ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እናትየው አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው ልጇን በመንከባከብ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ባልየው ሚስቱ ትኩረት እንደነፈገችው ሊሰማው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ባልየው ራሱ አባት መሆኑ የሚያስከትልበት ተጨማሪ ኃላፊነት ይኖራል። ለሚስቱ ብቻ ሳይሆን ለልጁም ጭምር እንክብካቤ ማድረግና የሚያስፈልገውን ማሟላት ይጠበቅበታል።

6-8. ልጅ መውለድ እየፈለጉ መውለድ ያልቻሉ ባለትዳሮች ምን ሊሰማቸው ይችላል?

6 አንዳንድ ባለትዳሮች ደግሞ የተለየ ዓይነት መከራ ይደርስባቸዋል። ልጅ ለመውለድ የሚጓጉ ቢሆንም እንኳ መውለድ ሳይችሉ ይቀራሉ። ሚስትየዋ ማርገዝ አለመቻሏ ከባድ የስሜት ሥቃይ ሊያስከትልባት ይችላል። እርግጥ ማግባትም ሆነ ልጅ መውለድ ከጭንቀት ነፃ ለመሆን ዋስትና አይሆንም፤ ይሁንና ልጅ እየፈለጉ መውለድ አለመቻልም ራሱ ‘በሥጋ ላይ የሚደርስ መከራ’ ነው። (ምሳሌ 13:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ መሃን መሆን እንደሚያሳፍር ነገር ተደርጎ ይቆጠር ነበር። የያዕቆብ ሚስት የሆነችው ራሔል እንደ እህቷ ልጆች መውለድ ባለመቻሏ ምሬቷን ገልጻ ነበር። (ዘፍ. 30:1, 2) ብዙ ልጆችን መውለድ የተለመደ በሆነባቸው አገሮች የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን ለምን ልጆች እንዳልወለዱ ብዙ ሰዎች ይጠይቋቸዋል። ልጆች ስለማይወልዱበት ምክንያት በዘዴ ሊያስረዷቸው ቢሞክሩም ሰዎቹ ብዙ ጊዜ “እንግዲህ እንጸልይላችኋለን!” የሚል መልስ ይሰጧቸዋል።

7 በእንግሊዝ አገር የምትኖር አንዲት እህት ያጋጠማትንም ሁኔታ እንመልከት፤ ልጅ መውለድ በጣም ትፈልግ የነበረ ቢሆንም እንኳ ምኞቷ እውን ሊሆንላት አልቻለም። ይህ ፍላጎቷ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሊሳካ እንደማይችል ስታውቅ በጣም አዝና እንደነበር ተናግራለች። በኋላም እሷና ባለቤቷ የማደጎ ልጅ ለማሳደግ ወሰኑ። ይሁንና እንዲህ ብላለች፦ “ያኔም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልተጽናናሁም። የማደጎ ልጅ ማሳደግ የራሴን ልጅ እንደ መውለድ ሊሆንልኝ እንደማይችል ታውቆኝ ነበር።”

8 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቲያን ሴቶች ሲናገር “ልጅ በመውለድ ደህንነቷ ተጠብቆ ትኖራለች” ይላል። (1 ጢሞ. 2:15) ይህ ማለት ግን ልጆች መውለድ ወይም ማሳደግ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል ማለት አይደለም። ታዲያ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? አንዲት ሴት ልጆች በማሳደግና በሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች መጠመዷ ከሐሜትና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ ሊያደርጋት እንደሚችል መግለጹ ነው። (1 ጢሞ. 5:13) ያም ሆኖ ከትዳርና ከቤተሰብ ሕይወት ጋር የተያያዙ መከራዎች ሊያጋጥሟት ይችላሉ።

የምንወደውን ሰው በሞት በምናጣበት ወቅት ሐዘኑን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል? (አንቀጽ 9, 12ን ተመልከት)

9. የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት ለየት ያለ ፈተና ነው የምንለው ለምንድን ነው?

9 ባለትዳሮች ሊደርሱባቸው ከሚችሉ መከራዎች አንዱ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ነው። ብዙዎች የትዳር ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው ለየት ያለ ፈተና አጋጥሟቸዋል። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣው ሰው በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዲህ ያለ ፈተና ያጋጥመኛል ብሎ አልጠበቀ ይሆናል። ክርስቲያኖች ኢየሱስ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት አላቸው። (ዮሐ. 5:28, 29) የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው ይህን ተስፋ ማወቁ ምን ጥቅም ያስገኝለታል? በጣም እንደሚያጽናናው የታወቀ ነው። አፍቃሪ የሆነው አባታችን በቃሉ አማካኝነት እንዲህ ያሉ ተስፋዎችን በመስጠት መከራ የሚደርስባቸውን ሰዎች ያጽናናል። አሁን ደግሞ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ በሚሰጠው መጽናኛ ብርታት ያገኙት እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ፈተና በሚደርስብን ጊዜ መጽናኛ ማግኘት

10. ሐና የተጽናናችው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

10 የሕልቃና ሚስት የነበረችው ሐና ምን ፈተና አጋጥሟት እንደነበር እንመልከት። ሐና መሃን የነበረች ሲሆን ጣውንቷ ፍናና ግን ብዙ ልጆች ነበሯት። (1 ሳሙኤል 1:4-7ን አንብብ።) በዚህ ምክንያት ፍናና “በየዓመቱ” ሐናን ታበሳጫት ነበር። ይህም በሐና ላይ ከፍተኛ መከራና ሐዘን አስከትሎባት ነበር። ጉዳዩን ለይሖዋ በመግለጽ እፎይታ እንዲሰጣት ለመነች። እንዲያውም ወደ አምላክ ቤት በመሄድ “በይሖዋ ፊት ለረጅም ሰዓት” ጸለየች። ይሖዋ ያቀረበችውን ልመና እንደሚሰማ ጠብቃ ይሆን? ጸሎቷን እንደሚሰማ ተስፋ አድርጋ መሆን አለበት። ያም ሆነ ይህ ‘ዳግመኛ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።’ (1 ሳሙ. 1:12, 17, 18) ይሖዋ ልጅ እንደሚሰጣት አለዚያም በሌላ መንገድ እንደሚያጽናናት ተማምና ነበር።

11. ፈተና ሲያጋጥመን መጽናናት እንድንችል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

11 ፍጽምና የጎደለን እንዲሁም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ የምንኖር እንደመሆናችን መጠን ፈተናና መከራ ይደርስብናል። (1 ዮሐ. 5:19) ይሁንና ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! የሚደርሱብንን ፈተናዎች ወይም መከራዎች ለመቋቋም የሚያስችለንን እርዳታ የምናገኝበት አንዱ መንገድ ጸሎት ነው። ሐና ልቧን አፍስሳ ወደ ይሖዋ ጸልያለች። እኛም በተመሳሳይ፣ መከራ በሚደርስብን ጊዜ የገጠመንን ችግር በጸሎታችን ላይ እንዲሁ ከመጥቀስ ያለፈ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ለይሖዋ ምልጃ ማቅረብ ይኸውም ስሜታችንን ሁሉ አውጥተን በመግለጽ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይገባናል።—ፊልጵ. 4:6, 7

12. መበለቷ ሐና ደስተኛ እንድትሆን የረዳት ምንድን ነው?

12 ልጅ መውለድ ባለመቻላችንም ሆነ የምንወደውን ሰው በሞት በማጣታችን ምክንያት በውስጣችን የባዶነት ስሜት ቢሰማንም እንኳ መጽናኛ ማግኘት እንችላለን። በኢየሱስ ዘመን የነበረችው ነቢዪቱ ሐና ባሏን በሞት ያጣችው በተጋቡ ገና በሰባት ዓመታቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሐና ልጆች ይኑሯት አይኑሯት የሚናገረው ነገር የለም። ታዲያ እንድትጽናና የረዳት ነገር ምን ነበር? ሉቃስ 2:37 “ሌትና ቀንም በጾምና በምልጃ ቅዱስ አገልግሎት እያቀረበች ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር” ይላል። ሐና በ84 ዓመቷም እንኳ ለመጸለይና ይሖዋን ለማምለክ ወደ ቤተ መቅደስ ትሄድ ነበር። ፈተና ቢደርስባትም እንኳ እንድትጽናና ብሎም ደስተኛ እንድትሆን የረዳት ይህ ነው።

13. የቤተሰባችን አባላት ማበረታቻ በማይሰጡን ጊዜም እንኳ እውነተኛ ጓደኞች ሊያጽናኑን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

13 ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በተቀራረብን መጠን እውነተኛ ጓደኞችና የልብ ወዳጆች ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 18:24) ፖላ ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሳለች እናቷ እውነትን ተወች፤ በዚህ የተነሳ በጣም አዝና እንደነበር ታስታውሳለች። ይህን ፈተና መቋቋም ቀላል አልነበረም። ይሁንና አን የተባለች በጉባኤው ውስጥ የምትገኝ አቅኚ እህት ትኩረት ሰጥታ ስለረዳቻት በመንፈሳዊ መበረታታት ችላለች። ፖላ እንዲህ ብላለች፦ “አን ከእኔ ጋር የሥጋ ዝምድና ባይኖራትም እንኳ ያሳየችኝ አሳቢነት በጣም ጠቅሞኛል። ይሖዋን ማገልገሌን እንድቀጥል ረድቶኛል።” ፖላ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሏን ቀጥላለች። እናቷም በድጋሚ ይሖዋን ማገልገል በመጀመሯ ፖላ በጣም ተደስታለች። አንም ብትሆን ለፖላ መንፈሳዊ እናት መሆን መቻሏ አስደስቷታል።

14. ሌሎችን ስናጽናና ምን ጥቅም እናገኛለን?

14 ለሌሎች ሰዎች ልባዊ አሳቢነት ስናሳይ ራሳችን የሚሰማን አሉታዊ ስሜት እየቀለለን ይሄዳል። ለምሳሌ ያህል ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ብዙ እህቶች ምሥራቹን በማወጅ ከአምላክ ጋር አብረው መሥራታቸው ታላቅ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። ግባቸው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እሱን ማስከበር ነው። እንዲያውም አንዳንዶች አገልግሎት ለሕመማቸው መድኃኒት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሁላችንም በክልላችንና በጉባኤው ውስጥ ላሉ ሰዎች አሳቢነት ማሳየታችን በጉባኤው ውስጥ ለሚኖረው አንድነት አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችለናል። (ፊልጵ. 2:4) ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። በተሰሎንቄ ጉባኤ ለነበሩት ሰዎች ‘እንደምታጠባ እናት’ አሳቢነት አሳይቷቸዋል፤ እንዲሁም “አባት ለልጆቹ እንደሚያደርገው” ለወንድሞቹ ማበረታቻና ማጽናኛ ሰጥቷቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 2:7, 11, 12ን አንብብ።

ቤተሰቦችን ማጽናናት

15. በዋነኝነት ልጆችን ስለ ይሖዋ የማስተማር ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው?

15 በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦች ማጽናኛና እርዳታ መስጠታችንም በጣም አስፈላጊ ነው። በእውነት ቤት ብዙም ያልቆዩ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋ ሲያስተምሩ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲረዷቸው፣ አልፎ ተርፎም ልጆቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑላቸው የሚጠይቁበት ጊዜ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በዋነኝነት ልጆችን የማስተማርና የማሠልጠን ኃላፊነት ያለባቸው ወላጆች ናቸው። (ምሳሌ 23:22፤ ኤፌ. 6:1-4) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ በዚህ ረገድ ሌሎች እርዳታ ማበርከታቸው አስፈላጊና ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ወላጆችን ከኃላፊነት ነፃ አያደርጋቸውም። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው።

16. ልጆችን በምንረዳበት ወቅት ምን ነገሮችን ማስታወስ ይኖርብናል?

16 አንድ ወላጅ ሌላ ሰው ልጆቹን እንዲያስጠናለት ከወሰነ ልጆቹን የሚያስጠናው ሰው የወላጆቹን ኃላፊነት ለመውሰድ መሞከር የለበትም። የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ወላጆች ያሏቸውን ልጆች የምናስጠናበት ጊዜም ይኖራል። ይህ በሚሆንበት ወቅት፣ ለልጆቹ መንፈሳዊ እርዳታ ስላበረከትን ብቻ የልጆቹ ወላጆች እንደሆንን ሊሰማን አይገባም። በተጨማሪም ልጆቹን ቤታቸው ውስጥ ማስጠናቱ የተሻለ ነው፤ በዚህ ወቅት ቤት ውስጥ ወላጆቻቸው ወይም ሌላ የጎለመሰ የይሖዋ ምሥክር ቢኖር ይመረጣል። አለዚያ ደግሞ ሰዎች በሚገኙበት ሌላ ቦታ ማስጠናታችን ጥበብ ይሆናል። ይህን ማድረጋችን ሌላ ሰው ጉዳዩን በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዳው ያደርጋል። ወላጆቻቸው ከጊዜ በኋላ የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን።

17. ልጆች የመጽናኛ ምንጭ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ለእውነተኛው አምላክ ፍቅር ያዳበሩና የእሱን ቃል በተግባር የሚያውሉ ልጆች ለቤተሰባቸው የመጽናኛ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉት ወላጆቻቸውን በማክበርና በሌሎች ተግባራዊ መንገዶች ወላጆቻቸውን በመርዳት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለቤተሰቡ መንፈሳዊነት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። ከጥፋት ውኃው በፊት ላሜህ ይሖዋን ያመልክ ነበር። ላሜህ ልጁን ኖኅን በተመለከተ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፦ “[ኖኅ] ይሖዋ በረገማት ምድር የተነሳ ከምንለፋው ልፋትና ከምንደክመው ድካም በማሳረፍ ያጽናናናል።” ከጥፋት ውኃው በኋላ ይሖዋ ምድርን ዳግመኛ እንደማይረግም በተናገረ ጊዜ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዘፍ. 5:29፤ 8:21) በዛሬው ጊዜም ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ልጆች ለቤተሰባቸው የመጽናኛ ምንጭ መሆን ይችላሉ። የቤተሰባቸው አባላት በአሁኑ ጊዜ የሚደርስባቸውን ፈተና እንዲቋቋሙ ብሎም ከጥፋት ውኃው ይበልጥ አስከፊ ከሆነ ጥፋት እንዲተርፉ መርዳት ይችላሉ።

18. ምንም ዓይነት መከራ ወይም ፈተና ቢያጋጥመን በድፍረት ለመጽናት የሚረዳን ምንድን ነው?

18 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጸለያቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላቸው እንዲሁም ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መቀራረባቸው ፈተና ሲደርስባቸው እንዲጽናኑ ረድቷቸዋል። (መዝሙር 145:18, 19ን አንብብ።) ዘላቂ የሆነ መጽናኛ የምናገኘው ከይሖዋ መሆኑን ማወቃችን አሁንም ሆነ ወደፊት ምንም ዓይነት መከራ ቢያጋጥመን በድፍረት መጽናት እንድንችል ይረዳናል።