በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የበዙት ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የበዙት ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ በጣም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የኖሩት ለምንድን ነው? አዳዲስ የመጽሐፍ ትርጉሞች መዘጋጀታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ያግዛል ወይስ እንቅፋት ይፈጥራል? እነዚህን ትርጉሞች ያዘጋጀው ማን እንደሆነና የተዘጋጁበትን ዓላማ ማወቅህ በዚህ ረገድ ሊረዳህ ይችላል።

መጀመሪያ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንዴት ነው? የተጻፈውስ መቼ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች እንመርምር።

የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ በተለምዶ በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው። የመጀመሪያው ክፍል ‘የአምላክን ቅዱስ ቃል’ የያዙ 39 መጻሕፍትን ያካተተ ነው። (ሮም 3:2) የመጀመሪያው መጽሐፍ የተጻፈው በ1513 ዓ.ዓ. ሲሆን የመጨረሻው የተጻፈው ደግሞ ከ443 ዓ.ዓ. በኋላ ነው፤ አምላክ በእነዚህ 1,100 የሚያህሉ ዓመታት ውስጥ ታማኝ ሰዎችን በመንፈሱ እየመራ እነዚህ መጻሕፍት እንዲጻፉ አድርጓል። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የጻፉት በዕብራይስጥ ስለሆነ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተብሎ ይጠራል፤ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን በመባልም ይታወቃል።

ሁለተኛው ክፍል 27 መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን እነዚህም ቢሆኑ “የአምላክ ቃል” ናቸው። (1 ተሰሎንቄ 2:13) አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስን ታማኝ ደቀ መዛሙርት በመንፈሱ በመምራት እነዚህን መጻሕፍት እንዲጽፉ አድርጓል፤ ይህ ክፍል የተጻፈው በአንጻራዊ ሁኔታ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ማለትም ከ41 ዓ.ም. እስከ 98 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ወደ 60 የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የጻፉት በግሪክኛ ስለሆነ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ተብሎ ይጠራል፤ በተለምዶ አዲስ ኪዳን በመባልም ይታወቃል።

እነዚህ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ 66 መጻሕፍት አንድ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ፤ አምላክ ለሰው ዘር የላከው መልእክት እነዚህን መጻሕፍት በሙሉ ያካተተ ነው። ይሁን እንጂ ከዋናው ቅጂ በተጨማሪ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የተዘጋጁት ለምንድን ነው? ከዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች መካከል ሦስቱ የሚከተሉት ናቸው፦

  • ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብ እንዲችሉ ለማድረግ።

  • መጽሐፍ ቅዱስን በእጃቸው ይገለብጡ የነበሩ ሰዎች የሠሯቸውን ስህተቶች በማረም የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ መልሶ ለማስገባት።

  • መጽሐፍ ቅዱስን በዘመናዊ ቋንቋ ለማዘጋጀት።

እነዚህ ነጥቦች ሁለት ጥንታዊ ትርጉሞች እንዲዘጋጁ ምክንያት የሆኑት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም

ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ300 ዓመታት ገደማ በፊት አይሁዳውያን ምሁራን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ሌላ ቋንቋ ማለትም ወደ ግሪክኛ መተርጎም ጀመሩ። ይህ ትርጉም የግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በመባል መታወቅ ጀመረ። ይህ ትርጉም የተዘጋጀው ለምን ነበር? በዚያ ጊዜ ከዕብራይስጥ ይልቅ ግሪክኛ ይናገሩ የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ መረዳትና ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ለመርዳት ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 3:15

በተጨማሪም የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ያልሆኑ ግሪክኛ ተናጋሪ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ማወቅ እንዲችሉ ረድቷቸዋል። እንዴት? ፕሮፌሰር ዊልበርት ፍራንሲስ ሃዋርድ እንደተናገሩት “ሚስዮናውያን ከአንዱ ምኩራብ ወደ ሌላው እየሄዱ ‘ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ከቅዱሳን መጻሕፍት ማስረጃ እየጠቀሱ የሚያብራሩት’ ይህንን ትርጉም ተጠቅመው ነበር፤ በመሆኑም ይህ ትርጉም የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ሆነ።” (የሐዋርያት ሥራ 17:3, 4፤ 20:20) ፍሬድሪክ ፋይቪ ብሩስ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደተናገሩት በርካታ አይሁዳውያን “ለሰብዓ ሊቃናት ትርጉም የነበራቸው ፍቅር እንዲጠፋ” ያደረገው አንዱ ምክንያት ይህ ነበር።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቀስ በቀስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲያገኙ እነዚህን መጻሕፍት ከሰብዓ ሊቃናት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ጋር አንድ ላይ አደረጓቸው፤ በዛሬው ጊዜ በእጃችን ያለው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ላይ የተሰባሰበው በዚህ መልክ ነበር።

የላቲን ቩልጌት ትርጉም

መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀ ከ300 ዓመታት ገደማ በኋላ፣ የሃይማኖት ምሁር የነበረው ጀሮም መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጎመ ሲሆን ይህም ከጊዜ በኋላ ላቲን ቩልጌት ተብሎ መጠራት ጀመረ። ከላቲን ቩልጌት በፊትም ቢሆን በላቲን የተዘጋጁ የተለያዩ ትርጉሞች ነበሩ፤ ታዲያ አዲስ የላቲን ትርጉም ማዘጋጀት ያስፈለገው ለምን ነበር? ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው፣ ጀሮም “በተሳሳተ መንገድ የተተረጎሙ አገላለጾችን፣ በግልጽ የሚታዩ ስህተቶችንና ያለአግባብ የተጨመሩና የተቀነሱ ነገሮችን” ማረም ፈልጎ ነበር።

ጀሮም እንዲህ ያሉትን አብዛኞቹን ስህተቶች ማረም ችሏል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት እጅግ አስከፊ ነገር አደረጉ! ተቀባይነት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የላቲኑ ቩልጌት ብቻ እንደሆነ በይፋ ያወጁ ሲሆን ለቀጣዮቹ ብዙ መቶ ዘመናት ተቀባይነት ያለው ብቸኛ ትርጉም የላቲን ቩልጌት ሆነ። በመሆኑም ይህ ትርጉም ተራ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ እንዲችሉ ከመርዳት ይልቅ አብዛኛው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዳይረዳው አድርጓል፤ ምክንያቱም ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የላቲን ቋንቋ በብዙሃኑ ዘንድ ጨርሶ የማይታወቅ ቋንቋ ሆኖ ነበር።

አዳዲስ ትርጉሞች እየበዙ መጡ

ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተዘጋጁ፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ በአምስተኛው መቶ ዘመን ገደማ ጥቅም ላይ የዋለውና በስፋት የሚታወቀው ሲሪያክ ፐሺታ ነው። ሆኖም እስከ 14ኛው መቶ ዘመን ድረስ ተራው ሕዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት እንዲችል የተጠናከረ ጥረት ማድረግ አልተጀመረም ነበር።

በ14ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ እንግሊዛዊው ጆን ዊክሊፍ የአገሩ ሰዎች በሚገባ ሊረዱት በሚችሉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን አዘጋጀ፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በሞተ ቋንቋ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር የሚያስችል መንገድ ጠርጓል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ዮሐንስ ጉተንበርግ የማተሚያ መሣሪያ የፈለሰፈ ሲሆን ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በመላው አውሮፓ በሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎች ማዘጋጀትና ማሰራጨት እንዲችሉ መንገድ ከፍቶላቸዋል።

ከጊዜ በኋላ ተጨማሪ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ተዘጋጁ፤ በዚህም ምክንያት ተቺዎች ‘በተመሳሳይ ቋንቋ የተለያዩ ትርጉሞችን ማዘጋጀት በእርግጥ አስፈላጊ ነው?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። በ18ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ጆን ሉዊስ የተባሉ እንግሊዛዊ ቄስ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “ቋንቋ በጊዜ ሂደት ያረጃል እንዲሁም ለመረዳት አስቸጋሪ ይሆናል፤ በመሆኑም የጥንት ትርጉሞችን ማሻሻልና አሁን ያለው ትውልድ በሚረዳው ቋንቋ እንደገና ማዘጋጀት ያስፈልጋል።”

በአሁኑ ጊዜ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የድሮ ትርጉሞችን ለማሻሻል በሚያስችል የተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለተጻፈባቸው ቋንቋዎች ያላቸው እውቀት ከምንጊዜውም ይበልጥ ጨምሯል፤ እንዲሁም በቅርብ ጊዜ የተገኙ በርካታ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች አሏቸው። ይህም የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በተሻለ መንገድ ለመረዳት ያስችላቸዋል።

ስለዚህ አዳዲስ የመጽሐፍ ትርጉሞች መዘጋጀታቸው በጣም ጠቃሚ ነው። እርግጥ፣ ከአንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። * ይሁን እንጂ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚያዘጋጁት ሰዎች ይህን ያደረጉት ለአምላክ ባላቸው እውነተኛ ፍቅር ተነሳስተው ከሆነ የትርጉም ሥራቸው ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝልን ይችላል።

 

^ አን.24 በግንቦት 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ተመልከት።