በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤዛው የዘላለም ሕይወት ስለሚያስገኝ ይህ ስጦታ አምላክ የሰጠን ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ከሁሉ የላቀው ስጦታ ምንድን ነው?

ከሁሉ የላቀው ስጦታ ምንድን ነው?

ከሁሉ የላቀው ስጦታ ምንድን ነው?

“መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት [ነው]።” (ያዕቆብ 1:17) ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ሰማዩ አባታችን ስለ ይሖዋ አምላክ ልግስና ነው። አምላክ ለሰው ልጆች በርካታ ስጦታዎችን ሰጥቷል። ሆኖም ከእነዚህ ስጦታዎች ሁሉ የላቀ አንድ ስጦታ አለ። ይህ ስጦታ ምንድን ነው? ኢየሱስ በዮሐንስ 3:16 ላይ የተናገረው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”

አምላክ አንድያ ልጁን መስጠቱ ከኃጢአት፣ ከእርጅናና ከሞት ባርነት ነፃ ለመውጣት ያስችለናል፤ በመሆኑም ይህ ስጦታ ልናገኝ ከምንችለው ከየትኛውም ስጦታ የላቀ ነው። (መዝሙር 51:5፤ ዮሐንስ 8:34) በራሳችን የምናደርገው ማንኛውም ጥረት ከዚህ ባርነት ነፃ ሊያወጣን አይችልም። ይሁን እንጂ አምላክ በታላቅ ፍቅሩ ተገፋፍቶ ያዘጋጀልን ስጦታ ከዚህ ባርነት ነፃ ለመውጣት ያስችለናል። ይሖዋ አምላክ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ይሁን እንጂ ቤዛ ማለት ምን ማለት ነው? አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው? ደግሞስ ከቤዛው ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ቤዛ አንድን ያጣነውን ነገር መልሶ ለመግዛት ወይም ከባርነት ለማስለቀቅ የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ኃጢአት እንዳልነበረባቸውና ከዘሮቻቸው ጋር ሆነው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንደነበራቸው ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:26-28) የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን አምላክን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ኃጢአተኞች የሆኑ ሲሆን ይህን ሁሉ ነገር አጥተዋል። ይህስ ምን አስከተለ? መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” በማለት መልስ ይሰጣል። (ሮም 5:12) አዳም ለዘሮቹ ፍጹም ሕይወት በማስተላለፍ ፋንታ ኃጢአትንና የኃጢአት ውጤት የሆነውን ሞትን አወረሳቸው።

ለአንድ ነገር ቤዛ በሚከፈልበት ወቅት፣ የሚከፈለው ነገር ከጠፋው ነገር ጋር እኩል መሆን አለበት። አዳም የአምላክን ትእዛዝ ሆን ብሎ ሲጥስ ኃጢአት የሠራ ሲሆን ይህም ሞት አስከትሎበታል፤ በዚህ መልኩ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ጠፍቷል። ይህ ደግሞ የአዳምን ዘሮች ለኃጢአትና ለሞት ባርነት እንደዳረጋቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በመሆኑም የአዳምን ዘሮች ከዚህ ባርነት ለማስለቀቅ አንድ ሌላ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት፣ ማለትም የኢየሱስ ሕይወት ቤዛ ሆኖ መቅረብ ነበረበት። (ሮም 5:19፤ ኤፌሶን 1:7) አዳምና ሔዋን ያጡትን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሌሎች የሰው ልጆች ሊያገኙ የሚችሉት አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ ቤዛውን ስለከፈለ ብቻ ነው።—ራእይ 21:3-5

ቤዛው የዘላለም ሕይወት ስለሚያስገኝ ይህ ስጦታ አምላክ የሰጠን ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው። ባለፈው ርዕስ ላይ አንድን ስጦታ ዋጋማ የሚያደርጉ አራት መሥፈርቶችን ተመልክተን ነበር። ቤዛው “ፍጹም ገጸ በረከት” ነው የምንለው ለምን እንደሆነ ማስተዋል እንድንችል ይህ ስጦታ እነዚህን አራት መሥፈርቶች በላቀ ደረጃ የሚያሟላው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የምንፈልገውን ነገር ያሟላል። ሁላችንም ለዘላለም የመኖር ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን። (መክብብ 3:11) ሆኖም ይህን ፍላጎታችንን በራሳችን ማሟላት አንችልም፤ ቤዛው ግን ሊያሟላልን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ይላል።—ሮም 6:23

የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላል። ሰዎች ቤዛ መክፈል አይችሉም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ለሕይወታቸው የሚከፈለው የቤዛ ዋጋ እጅግ ውድ ስለሆነ መቼም ቢሆን ከአቅማቸው በላይ ነው።” (መዝሙር 49:8) በመሆኑም ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለመውጣት የግድ የአምላክ እርዳታ ያስፈልገናል። አምላክ “ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት” የሚያስፈልገንን ነገር አሟልቶልናል።—ሮም 3:23, 24

በተገቢው ጊዜ የተሰጠ ስጦታ። መጽሐፍ ቅዱስ “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ [ሞቶልናል]” በማለት ይናገራል። (ሮም 5:8) ቤዛው የተሰጠን “ገና ኃጢአተኞች ሳለን” መሆኑ ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ አምላክ በጣም እንደሚወደን ያሳያል። በተጨማሪም ኃጢአት ያስከተለውን መዘዝ ተቋቁመን ለመኖር ብንገደድም እንኳ በጉጉት የምንጠብቀው ግሩም ተስፋ እንዲኖረን አድርጓል።

ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት የተሰጠ ስጦታ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ልጁን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥ ያነሳሳውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል። ይህ ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፦ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደን ነው።”—1 ዮሐንስ 4:9, 10

ከሁሉ ለላቀው ለዚህ ስጦታ አድናቆት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በዮሐንስ 3:16 ላይ እንደተናገረው ማንኛውም ሰው ለመዳን ከፈለገ የግድ በእሱ ‘ማመን’ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት” እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 11:1) ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ለመሆን ደግሞ ትክክለኛ እውቀት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም፣ ይህን “ፍጹም ገጸ በረከት” ስለሰጠን ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲሁም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የተዘረጋልህን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለማግኘት ማድረግ ስለሚጠበቅብህ ነገር ይበልጥ ለማወቅ ጥረት እንድታደርግ እናበረታታሃለን።

ስለ ይሖዋና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ማድረግ ስለሚጠበቅብን ነገር ይበልጥ ለማወቅ www.jw.org/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ የሚገኙትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሐሳቦች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። ከሁሉ ስለላቀው ስለዚህ ስጦታ ይበልጥ ስታውቅና ስጦታው የሚያስገኘውን ጥቅም ስታጣጥም “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” በማለት አድናቆትህን ለመግለጽ እንደምትገፋፋ እርግጠኞች ነን።—ሮም 7:25