በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ከሁሉ የላቀው ስጦታ ምንድን ነው?

“እስከ ዛሬ ከተሰጡኝ ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጥ ስጦታ”

“እስከ ዛሬ ከተሰጡኝ ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጥ ስጦታ”

ይህን የተናገረችው፣ አንዲት ቡችላ በስጦታ መልክ የተሰጠቻት የ13 ዓመት ልጅ ናት። አንዲት የተዋጣላት ነጋዴም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች አባቷ የሰጣት ኮምፒውተር ሕይወቷን እንደለወጠው ተናግራለች። አንድ ሰው ደግሞ ሚስቱ በመጀመሪያ ዓመት የጋብቻ ክብረ በዓላቸው ወቅት የሰጠችው በእጅ የተሠራ ካርድ ከዚያ በፊት ከተሰጡት ስጦታዎች ሁሉ የተሻለ እንደሆነ ተሰምቶታል።

በየዓመቱ በርካታ ሰዎች አንድን ለየት ያለ ወቅት በማስመልከት ለወዳጃቸው ወይም ለዘመዳቸው የሚሰጡትን “ከሁሉ የተሻለ” ስጦታ ለማግኘት ብዙ ጊዜና ጉልበት ያጠፋሉ። ደግሞም አብዛኞቹ ሰዎች፣ ስጦታ በሚሰጡበት ወቅት በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች የሰጡት ዓይነት ምላሽ ቢያገኙ ደስ ይላቸዋል። አንተስ? ከፍ ተደርገው የሚታዩ ስጦታዎች ብትሰጥ ወይም ብትቀበል ደስ አይልህም?

ሁላችንም እንዲህ ያሉ ስጦታዎችን መስጠትም ሆነ መቀበል እንፈልጋለን። ምክንያቱም ስጦታ፣ ተቀባዩን ከመጥቀም ባለፈ ሰጪውንም ጥሩ ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስም “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ተቀባዩ ለስጦታው ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ከሆነ ደግሞ ሰጪው የሚያገኘው ደስታ ያንኑ ያህል ይጨምራል።

ታዲያ የምትሰጠው ስጦታ ለአንተም ሆነ ለተቀባዩ እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ደግሞስ “ከሁሉ የተሻለ” የምትለውን ስጦታ መስጠት ባትችል እንኳ ተቀባዩ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ነገር መስጠት የምትችለው እንዴት ነው?