በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አዲስ ዓለም ትርጉም ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው?

አዲስ ዓለም ትርጉም ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው?

 አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ክፍል የወጣው በ1950 ነው። ይህ ትርጉም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይለያል፤ በመሆኑም ይህ ትርጉም ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በትርጉሙ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ያነሱ እንዲሁም አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች አሉ። a በአብዛኛው ይህ ትርጉም ከሌሎች ትርጉሞች እንዲለይ ያደረጉት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።

 •   ተአማኒነት። አዲስ ዓለም ትርጉም ምሁራን በቅርብ ጊዜ የደረሱበትን ምርምር እና ይበልጥ እምነት የሚጣልባቸው በእጅ የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎችን መሠረት ያደረገ ትርጉም ነው። ከዚህ በተለየ መልኩ በ1611 የተዘጋጀው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መሠረት ያደረጋቸው በእጅ የተጻፉ ቅጂዎች አዲስ ዓለም ትርጉም ከተተረጎመባቸው በእጅ የተጻፉ ቅጂዎች ጋር ሲወዳደሩ ተአማኒነታቸውም ሆነ ያስቆጠሩት ዕድሜ አነስተኛ ነው።

 •   ለመልእክቱ ታማኝ መሆን። የአዲስ ዓለም ትርጉም ተርጓሚዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምንም ሳያዛቡ ለማስተላለፍ ብዙ ጥረት አድርገዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ማየት እንደሚቻለው አንዳንድ የሰው ወጎች በተርጓሚዎቹ ሥራ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ የተሰኘው የአምላክ ስም እንደ ጌታ ወይም እግዚአብሔር ባሉት የማዕረግ ስሞች ተተክቷል።

 •   ቃል በቃል የተቀመጠ መሆኑ። በራስ አባባል ከሚዘጋጁ (ፓራፍሬዝድ) የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተለየ መልኩ የአዲስ ዓለም ትርጉምን በተቻለ መጠን ቃል በቃል ለመተርጎም ጥረት ተደርጓል፤ እርግጥ ነው፣ እንዲህ የሚደረገው ሐሳቡ እንግዳ የሆነ ትርጉም የማያመጣ ወይም መልእክቱን የማይደብቅ እስከሆነ ድረስ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በራሳቸው አባባል የሚያስቀምጡ ትርጉሞች፣ የሰዎችን ሐሳብ ሊያስገቡ ወይም አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን ሊያስቀሩ ይችላሉ።

በአዲስ ዓለም ትርጉም እና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል ያለው ልዩነት

 አንዳንድ መጽሐፎች አለመካተታቸው። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በመጽሐፍ ቅዱሶቻቸው ላይ አንዳንድ መጽሐፎችን ጨምረዋል፤ እነዚህ መጽሐፎች አዋልድ ይባላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ መጽሐፎች በአይሁዳውያን ቀኖና ወይም የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ አይገኙም፤ “የአምላክ ቅዱስ ቃል በአደራ [የተሰጠው]” ደግሞ ለአይሁዳውያን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮም 3:1, 2) ከዚህ አንጻር አዲስ ዓለም ትርጉም እና ሌሎች ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአዋልድ መጽሐፎችን አላካተቱም።

 አንዳንድ ጥቅሶች አለመገኘታቸው። አንዳንድ ትርጉሞች በእጅ በሚገኙት ጥንታዊ ቅጂዎች ውስጥ የሌሉ አንዳንድ ጥቅሶችን ይዘዋል፤ አዲስ ዓለም ትርጉም ግን እነዚህን የተጨመሩ ጥቅሶች አውጥቷቸዋል። ብዙ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም እነዚህን የተጨመሩ ጥቅሶች አውጥተዋቸዋል፤ ወይም ደግሞ ጥቅሶቹ ይበልጥ ተአማኒ በሆኑት ምንጮች ውስጥ እንደማይገኙ ይገልጻሉ። b

 የተለየ አገላለጽ። መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል ሲተረጎም አንዳንድ ጊዜ ግልጽ ላይሆን ወይም የተሳሳተ ትርጉም ሊያስተላልፍ ይችላል። ለምሳሌ፣ በማቴዎስ 5:3 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ብዙውን ጊዜ “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው” (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ተብሎ ተተርጉሟል። ብዙ ሰዎች ቃል በቃል የተተረጎመውን “በመንፈስ ድኾች የሆኑ” የሚለውን አገላለጽ መረዳት ይከብዳቸዋል፤ አንዳንዶች ደግሞ ኢየሱስ እዚህ ጥቅስ ላይ ሊናገር የፈለገው ትሕትና ወይም ድሃ መሆን ስላለው ጥቅም እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና ኢየሱስ ሊናገር የፈለገው ነጥብ እውነተኛ ደስታ የምናገኘው በሕይወታችን የአምላክ አመራር እንደሚያስፈልገን አምነን ስንቀበል መሆኑን ነው። ከዚህ አንጻር አዲስ ዓለም ትርጉም የጥቅሱን መልእክት በትክክል ለማስተላለፍ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ” የሚለውን አገላለጽ ተጠቅሟል።—ማቴዎስ 5:3

የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች ስለ አዲስ ዓለም ትርጉም የሰጡት አዎንታዊ አስተያየት

 •   ኤድገር ጆንሰን ጉድስፒድ የተባሉ የታወቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚና ምሁር፣ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በተመለከተ ታኅሣሥ 8, 1950 በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፦ “የእናንተ ሰዎች የሚሠሩት ሥራና የሥራው ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያስደስተኛል፤ እንዲሁም ለዛ ያለው፣ ግልጽ የሆነውና ብዙ የተለፋበት ትርጉማችሁ በጣም አርክቶኛል። ብዙ ቁምነገር ግልጽ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ብዬ ለመናገር እችላለሁ።”

  ኤድገር ጆንሰን ጉድስፒድ

 •   በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት አለን ዊክግረን ሌሎች ትርጉሞችን ከመከተል ይልቅ ከዋናዎቹ ጥንታዊ ቅጂዎች ለመተርጎም ጥረት ካደረጉ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል አንዱ አዲስ ዓለም ትርጉም እንደሆነ ተናግረዋል።—ዚ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 99

 •   የብሪታንያው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አሌክሳንደር ቶምሰን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ይህ ትርጉም ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ጎበዝ ምሁራን የሥራ ውጤት መሆኑ ግልጽ ነው፤ የጥንታዊውን የግሪክኛ ቅጂ ስሜት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሊገልጽ የሚችለውን ያህል በትክክል ለማንጸባረቅ ሞክረዋል።”—ዘ ዲፈረንሺየተር፣ ሚያዝያ 1952፣ ገጽ 52

 •   ቻርልስ ፍራንሲስ ፖተር የተባሉት ጸሐፊ አዲስ ዓለም ትርጉም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንግዳ የሆነ አተረጓጎም እንዳጋጠማቸው ከተናገሩ በኋላ እንዲህ ብለዋል፦ “ስማቸው ያልተጠቀሰው ተርጓሚዎቹ፣ ምርጥ ከተባሉት የግሪክኛና የዕብራይስጥ በእጅ የተጻፉ ቅጂዎች የተረጎሙ ሲሆን ሥራቸው ድንቅ ችሎታና ጥበብ የሚታይበት ነው።”—ዘ ፌይዝስ ሜን ሊቭ ባይ፣ ገጽ 300

 •   ራበርት ማኮይ አዲስ ዓለም ትርጉም ከሌሎች ትርጉሞች ለየት እንዲል የሚያደርጉ ነገሮችና ጥሩ ጎኖች እንዳሉት ከተናገሩ በኋላ ግምገማቸውን እንዲህ በማለት አጠቃለዋል፦ “ይህ አዲስ ኪዳን ትርጉም፣ መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ረገድ የሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮችን በዘዴ የመፍታት ብቃት ያላቸው ምሁራን በድርጅቱ [በይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት] ውስጥ መኖራቸውን ያመለክታል”—አንዶቨር ኒውተን ኳርተርሊ፣ ጥር 1963፣ ገጽ 31

 •   ሳሙኤል ማክሊን ጊልሞር የተባሉት ፕሮፌሰር በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ በሚገኙት አንዳንድ አተረጓጎሞች ባይስማሙም ተርጓሚዎቹ “አስደናቂ የግሪክኛ ቋንቋ ችሎታ እንዳላቸው” ተናግረዋል።—አንዶቨር ኒውተን ኳርተርሊ፣ መስከረም 1966፣ ገጽ 26

 •   ፕሮፌሰር ቶማስ ዊንተር የአዲስ ዓለም ትርጉም ክፍል የሆነውን የኪንግደም ኢንተርሊንየር የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉምን ከገመገሙ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ስማቸው ያልተጠቀሰ ተርጓሚዎችን ያቀፈው ኮሚቴ ወቅታዊ ግንዛቤ ያለው ሲሆን መልእክቱን ሳያዛባ አቅርቧል።”—ዘ ክላሲካል ጆርናል፣ ሚያዝያና ግንቦት 1974፣ ገጽ 376

 •   በእስራኤል የዕብራይስጥ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ቤንያሚን ከዳር ኮፕስታይን በ1989 እንደሚከተለው ብለው ነበር፦ “ከዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስና ከትርጉም ጋር በተያያዘ በማደርገው የቋንቋ ምርምር አብዛኛውን ጊዜ የማመሳክረው የአዲስ ዓለም ትርጉም እየተባለ የሚጠራውን የእንግሊዝኛ ትርጉም ነው። ይህንንም ማድረጌ ይህ ትርጉም ጥንታዊውን ቅጂ በተቻለ መጠን በትክክል ለመረዳትና ለማስቀመጥ ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት ሥራ መሆኑን በተደጋጋሚ ለማረጋገጥ አስችሎኛል።”

 •   የሃይማኖታዊ ጥናቶች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄሰን ቤዱን በዘጠኝ ዋና ዋና የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ምርምር ካደረጉ በኋላ “[አዲስ ዓለም ትርጉም] ከመረመርኳቸው ትርጉሞች ሁሉ በትክክለኛነቱ እጅግ የላቀ ነው” በማለት ጽፈዋል። ኅብረተሰቡም ሆነ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን አዲስ ዓለም ትርጉም ከሌሎች ትርጉሞች የተለየ የሆነው፣ ተርጓሚዎቹ እምነታቸው ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ነው የሚል አመለካከት አላቸው፤ ይሁን እንጂ ቤዱን “አብዛኞቹ ልዩነቶች የተፈጠሩት አዲስ ዓለም ትርጉም የጥንቶቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የተጠቀሙባቸውን አገላለጾች ቃል በቃል እንዲሁም በጥንቃቄ በማስቀመጡና [ከሌሎቹ ትርጉሞች] ይበልጥ ትክክለኛ በመሆኑ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።—ትሩዝ ኢን ትራንስሌሽን፣ ገጽ 163, 165

a አስተያየቶቹ የተሰጡት በ2013 ተሻሽሎ ከወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም በፊት ለነበረው ትርጉም ነው።

b ለምሳሌ ያህል ኒው ኢንተርናሽናል ቨርዥን እና ኒው ጀሩሳሌም ባይብል የተባሉትን የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተመልከት፤ በተጨማሪም አዲሱ መደበኛ ትርጉምን መመልከት ትችላለህ። የተጨመሩት ጥቅሶች ማቴዎስ 17:21፤ 18:11፤ 23:14፤ ማርቆስ 7:16፤ 9:44, 46፤ 11:26፤ 15:28፤ ሉቃስ 17:36፤ 23:17፤ ዮሐንስ 5:4 እና ሮም 16:24 ናቸው። ኪንግ ጄምስ ቨርዥን እንዲሁም የ1879 ትርጉም (አማርኛ) በአንደኛ ዮሐንስ 5:7, 8 ላይ ስለ ሥላሴ የሚናገር ሐሳብ አስገብተዋል፤ ይህ ሐሳብ በዚህ ጥቅስ ላይ የተጨመረው መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ነው።