በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ክርስቲያኖች ገናን ማክበር አለባቸው?

ክርስቲያኖች ገናን ማክበር አለባቸው?

በዓለም ዙሪያ ያሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገና የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩት ሐዋርያቱና ደቀ መዛሙርቱ ገናን አክብረው የሚያውቁ ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ የልደት በዓል ማክበርን አስመልክቶ ምን እንደሚልስ ታውቃለህ? እነዚህን ጥያቄዎች መመርመራችን ‘ክርስቲያኖች ገናን ማክበር አለባቸው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ የኢየሱስም ሆነ የየትኛውም ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ልደት እንደተከበረ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ የልደት በዓላቸውን እንዳከበሩ የተጠቀሱት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው። ሁለቱም ሰዎች ይሖዋ አምላክን የማያመልኩ ሰዎች ነበሩ፤ እንዲሁም በሁለቱም ሰዎች የልደት በዓል ወቅት መጥፎ ነገር እንደተፈጸመ ተገልጿል። (ዘፍጥረት 40:20፤ ማርቆስ 6:21) ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደገለጸው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “የአረማውያን ልማድ የሆነውን ልደት ማክበርን” ይቃወሙ ነበር።

ኢየሱስ የተወለደበት ቀን ይታወቃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን አይናገርም። በማክሊንቶክና በስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ “ክርስቶስ የተወለደበትን ትክክለኛ ቀን ከአዲስ ኪዳንም ሆነ ከሌላ ምንጭ ማወቅ አይቻልም” በማለት ይናገራል። ኢየሱስ ተከታዮቹ ልደቱን እንዲያከብሩ ቢፈልግ ኖሮ የተወለደበትን ቀን እንዲያውቁ ያደርግ እንደነበር አያጠራጥርም።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ገናን እንዳከበሩ የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የለም። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደሚናገረው የገና በዓል ስለ መከበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው በ336 [ዓ.ም.] በተዘጋጀው “የፊሎካለስ ክሮኖግራፍ” በተባለው የሮማውያን አልማናክ ውስጥ ነው። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀና ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖረ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። በመሆኑም በማክሊንቶክና በስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው “የገና በዓል አምላክ የደነገገው ወይም በአዲስ ኪዳን ላይ የተመሠረተ በዓል አይደለም።” *

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያከብሩ ያዘዘው የትኛውን በዓል ነው?

ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ እንደመሆኑ መጠን ተከታዮቹ እንዲያደርጉ የሚፈልገውን ነገር በተመለከተ ግልጽ መመሪያዎችን የሰጠ ሲሆን እነዚህ መመሪያዎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል። ሆኖም ገናን ማክበር እንዳለባቸው ተናግሮ አያውቅም። አንድ አስተማሪ ተማሪዎቹ ከተሰጣቸው መመሪያ እንዲወጡ እንደማይፈልግ ሁሉ ኢየሱስም ተከታዮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ከተጻፈው [እንዲያልፉ]” አይፈልግም።—1 ቆሮንቶስ 4:6

በሌላ በኩል ደግሞ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በደንብ የሚያውቁት አንድ በጣም አስፈላጊ በዓል የነበረ ሲሆን እሱም የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ነው። ይህ በዓል መቼ መከበር እንዳለበት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸውና እንዴት እንደሚከበር ያሳያቸው ኢየሱስ ራሱ ነው። እነዚህ ግልጽ መመሪያዎችና ኢየሱስ የሞተበት ትክክለኛ ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል።—ሉቃስ 22:19፤ 1 ቆሮንቶስ 11:25

ከላይ እንዳየነው ገና የሚከበረው የኢየሱስ ልደት ቀን ነው ተብሎ ሲሆን የጥንት ክርስቲያኖች ደግሞ ከአረማውያን የመጣውን ልደት የማክበር ልማድ አይከተሉም ነበር። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስም ሆነ ሌላ ማንኛውም ሰው ገናን እንዳከበረ አይናገርም። ከእነዚህ ማስረጃዎች አንጻር በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ገናን ማክበር እንደሌለባቸው ወስነዋል።

^ አን.6 የአብዛኞቹን የገና በዓል ልማዶች አመጣጥ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በታኅሣሥ 1, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . . የገና በዓልን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ተመልከት፤ መጽሔቱ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።