በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ከሁሉ የላቀው ስጦታ ምንድን ነው?

ከሁሉ የላቀ ስጦታ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት

ከሁሉ የላቀ ስጦታ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት

ለአንድ ሰው ተስማሚ የሆነ ስጦታ ፈልጎ ማግኘት ቀላል አይደለም። ምክንያቱም የስጦታው ዋጋማነት የተመካው ተቀባዩ ለስጦታው በሚኖረው አመለካከት ላይ ነው። ደግሞም አንድ ሰው በጣም ጥሩ እንደሆነ የሚሰማውን ስጦታ ሌላ ሰው ያን ያህል ላይወደው ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት ከሁሉ የተሻለ ብሎ የሚቆጥረው ስጦታ፣ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ትልቅ ሰው እንደ ቤተሰብ ቅርስ ያሉ ለእሱ ትልቅ ትርጉም ያላቸውን ስጦታዎች ከፍ አድርጎ ሊመለከታቸው ይችላል። በአንዳንድ ባሕሎች ወጣቶችም ሆኑ ትላልቅ ሰዎች ስጦታው በገንዘብ መልክ ቢሰጣቸው ይመርጣሉ፤ ምክንያቱም ገንዘቡን ለፈለጉት ዓላማ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

ለሚወዱት ሰው ተስማሚ የሆነ ስጦታ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለውን ስጦታ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነቱን ተስማሚ ስጦታ ማግኘት ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም አንዳንድ ነገሮችን በአእምሯችን መያዛችን ተስማሚ ስጦታ የማግኘት አጋጣሚያችን ከፍ እንዲል ሊያደርግ ይችላል። የሚከተሉትን አራት ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባታችን ተቀባዩን የሚያስደስት ስጦታ ለመስጠት ይረዳናል።

የስጦታ ተቀባዩ ፍላጎት። በቤልፋስት፣ ሰሜን አየርላንድ የሚኖር አንድ ሰው የ10 ወይም የ11 ዓመት ልጅ እያለ የተሰጠው ብስክሌት እስካሁን ከተሰጡት ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጥ ስጦታ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲህ የተሰማው ለምንድን ነው? “ምክንያቱም እንደዚያ ዓይነት ብስክሌት እንዲኖረኝ በጣም እፈልግ ነበር” በማለት ተናግሯል። ይህ አስተያየት እንደሚያሳየው የአንድ ስጦታ ዋጋማነት በአብዛኛው የተመካው ተቀባዩ በሚፈልገው ነገር ላይ ነው። ስለዚህ፣ ስጦታ ስለምትሰጠው ሰው አስብ። አንድ ሰው ከፍ አድርጎ የሚያያቸው ነገሮች በፍላጎቱ ላይ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ ግለሰቡ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸውን ነገሮች ለይተህ ለማወቅ ጥረት አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙውን ጊዜ አያቶች ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በመሆኑም ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን ቶሎ ቶሎ ማየት ይፈልጉ ይሆናል። ስለዚህ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ወጣ ብለው ጊዜ ማሳለፍ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢሰጣቸው ይህንን ከየትኛውም ስጦታ ይበልጥ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል።

የአንድን ሰው ፍላጎት ለማወቅ ቁልፉ ጥሩ አዳማጭ መሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመስማት የፈጠንንና ለመናገር የዘገየን’ እንድንሆን ያበረታታናል። (ያዕቆብ 1:19) ከጓደኞቻችሁ ወይም ከዘመዶቻችሁ ጋር ስትጨዋወቱ፣ ምን እንደሚወዱና ምን እንደሚጠሉ የሚጠቁሙ ፍንጮችን ለማግኘት በደንብ አዳምጡ። ይህም እነሱን የሚያስደስት ስጦታ ለመስጠት ይረዳችኋል።

ተቀባዩ የሚያስፈልጉት ነገሮች። አንድ ስጦታ ተቀባዩ የሚያስፈልገውን ነገር የሚያሟላለት ከሆነ ስጦታው ትንሽ ቢሆንም እንኳ በተቀባዩ ዘንድ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

አንዳንዶች፣ ግለሰቡ የሚያስፈልገው ወይም የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ በቀጥታ በመጠየቅ ይህን በቀላሉ ማወቅ እንደሚቻል ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ስጦታውን ተቀባዩ ባልጠበቀው ጊዜ መስጠት ይፈልጋሉ፤ ስለዚህ ግለሰቡን በቀጥታ መጠየቅ፣ በመስጠት የሚያገኙትን ደስታ እንደሚቀንስባቸው ይሰማቸዋል። ከዚህም በላይ አንዳንድ ሰዎች ስለሚወዱትና ስለሚጠሉት ነገር በነፃነት የሚያወሩ ቢሆንም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ግን በግልጽ አይናገሩም።

በመሆኑም ስጦታ የምትሰጠውን ሰው ሁኔታ በጥንቃቄ ለማስተዋል ሞክር። ግለሰቡ ወጣት ነው ወይስ ትልቅ ሰው? ያገባ ነው ያላገባ? የተፋታ ነው ወይስ ሚስቱ የሞተችበት? ሥራ ያለው ነው ወይስ ጡረታ የወጣ? ከዚያም የትኛው ስጦታ ግለሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር እንደሚያሟላ አስብ።

ስጦታ ልትሰጠው ያሰብከው ሰው የሚያስፈልጉት ነገሮች ምን እንደሆኑ ለማወቅ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያለፉ ሌሎች ሰዎችን ማማከር ትችላለህ። እነሱም በዚያ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለሚያስፈልጓቸው አንዳንድ ለየት ያሉ ነገሮች ሊነግሩህ ይችላሉ፤ ሌሎች ሰዎች ስለ እነዚህ ነገሮች እምብዛም አያውቁ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የሚሰጡህ ሐሳብ ግለሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር የሚያሟላ ሆኖም ሌሎች ሰዎች ለመስጠት ያላሰቡትን ዓይነት ስጦታ ለመስጠት ያስችልሃል።

ስጦታው የሚሰጥበት ጊዜ። መጽሐፍ ቅዱስ “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ [ቃል] ምንኛ መልካም ነው!” ይላል። (ምሳሌ 15:23) ይህ ጥቅስ፣ የምንናገርበትን ጊዜ መምረጥ ትልቅ ልዩነት እንደሚያመጣ ያሳያል። ይህ ሐሳብ ከድርጊት ጋር በተያያዘም ይሠራል። በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ለሰሚው በጣም አስደሳች ሊሆን እንደሚችሉ ሁሉ አንድ ስጦታም በተገቢው ጊዜ መሰጠቱ ተቀባዩ ይበልጥ እንዲደሰት አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል።

ስጦታ የሚሰጥባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፤ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች አንድ ሰው ሲያገባ፣ ልጅ ሲወልድ ወይም ትምህርት ጨርሶ ሲመረቅ ስጦታ የመስጠት ልማድ አላቸው። አንዳንዶች በቀጣዩ ዓመት ውስጥ የሚፈጸሙ እንዲህ ያሉ ልዩ ክንውኖችን መመዝገብ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህን ማድረጋቸው ለእነዚህ ክንውኖች ተስማሚ የሆነ ስጦታ አስቀድመው ለማዘጋጀት ያስችላቸዋል። *

እርግጥ ነው፣ ስጦታ ለመስጠት የግድ ልዩ ክንውኖችን መጠበቅ አያስፈልግህም። በመስጠት የሚገኘውን ደስታ በማንኛውም ጊዜ ማጣጣም ይቻላል። ይሁን እንጂ፣ ልትጠነቀቅበት የሚገባ አንድ ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ምንም ለየት ያለ ምክንያት ሳይኖር ለአንዲት ሴት ስጦታ ቢሰጣት፣ ግለሰቡ ከእሷ ጋር የፍቅር ግንኙነት መመሥረት እንደሚፈልግ ልታስብ ትችላለች። ሰጪው እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ከሌለው፣ ስጦታው የተሳሳተ ትርጉም ሊሰጠው ወይም ችግር ሊያስከትል ይችላል። ይህ እውነታ፣ ስጦታ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ግምት ውስጥ መግባት ያለበትን ሌላ አስፈላጊ ነገር ያስታውሰናል፤ እሱም ሰጪው ስጦታ ለመስጠት የተነሳሳበት ምክንያት ነው።

ስጦታው የተሰጠበት ምክንያት። ከላይ የተጠቀሰው ምሳሌ እንደሚያሳየው፣ አንድ ሰው ስጦታ የሰጠበትን ምክንያት ተቀባዩ በተሳሳተ መንገድ ሊተረጉመው ይችል እንደሆነ ማሰቡ ጠቃሚ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰጪው ራሱ ስጦታ ለመስጠት የተነሳሳበት ምክንያት ምን እንደሆነ ራሱን መጠየቁ አስፈላጊ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ስጦታ የሚሰጡት በቅን ልቦና ተነሳስተው እንደሆነ ይናገሩ ይሆናል፤ ሆኖም ብዙ ሰዎች በየዓመቱ የሆነ ወቅት ጠብቀው ስጦታ የሚሰጡት እንዲህ ማድረግ ስለሚጠበቅባቸው ነው። ሌሎች ደግሞ፣ ስጦታ የሚሰጡት አድልዎ እንዲደረግላቸው አስበው ወይም በምላሹ አንድ ነገር ለማግኘት ተስፋ አድርገው ነው።

ታዲያ አንተ ስጦታ የምትሰጠው በቅን ልቦና ተነሳስተህ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የምታደርጉትን ነገር ሁሉ በፍቅር አድርጉ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 16:14) ስጦታ የምትሰጠው፣ ለግለሰቡ ባለህ እውነተኛ ፍቅርና አሳቢነት ተገፋፍተህ ከሆነ ስጦታውን የሚቀበለው ግለሰብም በስጦታው ደስተኛ ይሆናል፤ አንተም ብትሆን በልግስና በመስጠት የሚገኘውን ታላቅ ደስታ ታጣጥማለህ። በተጨማሪም ስጦታህ ከልብ የመነጨ መሆኑ በሰማይ ያለውን አባትህንም ያስደስተዋል። በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበሩት ክርስቲያኖች፣ በይሁዳ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸው በተቸገሩበት ወቅት እነሱን ለመርዳት በደስታ መዋጮ አድርገዋል፤ ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ያለ ልግስና በማሳየታቸው አመስግኗቸዋል። ጳውሎስ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው [ይወዳል]” በማለት ጽፎላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 9:7

ስጦታ ለመስጠት ስታስብ በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባትህ ሌሎችን የሚያስደስት ስጦታ መስጠት እንድትችል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። አምላክ እነዚህንና ሌሎች ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ለሰው ልጆች ከሁሉ የላቀውን ስጦታ አዘጋጅቷል። ከሁሉ የላቀው ይህ ስጦታ ምን እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግክ የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

^ አን.13 ብዙ ሰዎች በልደት ቀንና በሌሎች በዓላት ወቅት ስጦታዎችን ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ በእነዚህ ክብረ በዓላት ወቅት የሚከናወኑት አብዛኞቹ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር ይጋጫሉ። በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኘውን “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ—ክርስቲያኖች ገናን ማክበር አለባቸው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።