በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተቀይሯል ወይም ተበርዟል?

የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተቀይሯል ወይም ተበርዟል?

 በፍጹም። በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን በማወዳደር የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ላይ ሲገለበጥ ቢቆይም መሠረታዊ መልእክቱ አልተቀየረም።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገለበጥበት ወቅት ምንም ስህተት አልተሠራም ማለት ነው?

 እስከ አሁን በሺዎች የሚቆጠሩ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ተገኝተዋል። በአንዳንዶቹ ቅጂዎች መካከል የተወሰኑ ልዩነቶች መኖራቸው በሚገለበጥበት ወቅት ስህተት እንደተሠራ ይጠቁማል። ሆኖም አብዛኞቹ ልዩነቶች ጥቃቅንና በመልእክቱ ላይ ምንም ለውጥ የማያመጡ ናቸው። እርግጥ ነው፣ በመልእክቱ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ አንዳንድ ልዩነቶችም ተገኝተዋል፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመቀየር ሆን ተብለው የተደረጉ ይመስላሉ። የሚከተሉትን ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት፦

  1.   አንዳንድ ቆየት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ‘በሰማይ የሚመሠክሩት አብ፣ ቃልና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፤ እነዚህ ሦስቱ አንድ ናቸው’ የሚለውን ሐሳብ ይጨምራሉ። ይሁንና አስተማማኝ የሆኑ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ይህ ሐሳብ በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ እንደማይገኝና ከጊዜ በኋላ እንደተጨመረ አረጋግጠዋል። a በመሆኑም አስተማማኝ የሆኑ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ሐሳብ አያካትቱም

  2.   በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ የአምላክ ስም በሺዎች የሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ይገኛል። ሆኖም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል

ወደፊት ተጨማሪ ስህተቶች እንደማይገኙ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

 በአሁኑ ጊዜ በርካታ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ስለተገኙ ስህተቶች ቢኖሩ ኖሮ እነሱን ማግኘት ከምንጊዜውም ይበልጥ ቀላል ነው። b እነዚህን ቅጂዎች በማወዳደር የተገኘው ውጤት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኝነት ምን አረጋግጧል?

  •   ዊልያም ሄንሪ ግሪን የተባሉት ምሁር የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስመልክተው አስተያየት ሲሰጡ “የእነዚህን ያህል በትክክል ተላልፈው ለእኛ የደረሱ ጥንታዊ ጽሑፎች የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ብለዋል።

  •   ፍሬድሪክ ብሩስ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወይም በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብለው የሚጠሩትን መጻሕፍት አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የአዲስ ኪዳን ጽሑፎቻችንን ትክክለኛነት የሚያሳዩት ማስረጃዎች፣ በጥንት ዘመን የነበሩ ጸሐፊዎች ያዘጋጇቸው ሌሎች በርካታ ጽሑፎች ካሏቸው ማስረጃዎች ጋር ሲወዳደሩ በጣም ብዙ ናቸው፤ ያም ሆኖ የእነዚህን ጽሑፎች [ማለትም በጥንት ዘመን የነበሩ ጸሐፊዎች ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች] ትክክለኛነት በተመለከተ ጥያቄ ለማንሳት የሚደፍር ሰው የለም።”

  •   በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ ጥናት ያደረጉ ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን የተባሉ እውቅ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “[ማንኛውም ሰው] ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በእጁ ይዞ መጽሐፉ እውነተኛውን የአምላክ ቃል እንደያዘና ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በመልእክቱ ላይ ያን ያህል ጎልቶ የሚታይ ለውጥ እንዳልተደረገበት አፉን ሞልቶ በልበ ሙሉነት መናገር ይችላል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ መልእክቱ እንዳልተቀየረ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርጉ ምን ሌሎች ምክንያቶች አሉ?

  •   መጽሐፍ ቅዱስን ይገለብጡ የነበሩ አይሁዳውያንም ሆኑ ክርስቲያኖች የአምላክ ሕዝቦች ስለፈጸሟቸው ከባድ ስህተቶች የሚገልጹ ዘገባዎችን ምንም ሳይለውጡ አስፍረዋል። c (ዘኁልቁ 20:12፤ 2 ሳሙኤል 11:2-4፤ ገላትያ 2:11-14) የአይሁድ ብሔር ታዛዥ እንዳልነበረ በሚገልጹና የሰዎችን ወግ በሚያወግዙ ዘገባዎችም ላይ ምንም ለውጥ አላደረጉም። (ሆሴዕ 4:2፤ ሚልክያስ 2:8, 9፤ ማቴዎስ 23:8, 9፤ 1 ዮሐንስ 5:21) እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያሉ ዘገባዎችን በትክክል መገልበጣቸው እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑና የአምላክን ቅዱስ ቃል ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ያሳያል።

  •   አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ መሪነት እንዲጻፍ ካደረገ፣ መልእክቱ ተጠብቆ እንዲቆይም ያደርጋል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይደለም? d (ኢሳይያስ 40:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:24, 25) ደግሞም አምላክ ጥንት የነበሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በዛሬው ጊዜ የምንገኘው እኛም ከዚህ መጽሐፍ ተጠቃሚ እንድንሆን ይፈልጋል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) እንዲያውም “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።”—ሮም 15:4

  •   ኢየሱስም ሆነ ተከታዮቹ ጥንታዊ ከሆኑት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ ይጠቅሱ ነበር፤ ስለ ትክክለኝነታቸው ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አላደረባቸውም።—ሉቃስ 4:16-21፤ የሐዋርያት ሥራ 17:1-3

a ይህ ሐሳብ በኮዴክስ ሲናይቲከስ፣ በኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ፣ በቫቲካን ማኑስክሪፕት 1209፣ በመጀመሪያው ላቲን ቩልጌት፣ በፊሎሲኒየን ሃርክሊየን ሲሪያክ ቨርዥን ወይም በሲሪያክ ፐሺታ ውስጥ አይገኝም።

b ለምሳሌ ያህል፣ ከ5,000 የሚበልጡ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት (አዲስ ኪዳን በመባልም ይታወቃሉ) ጥንታዊ ቅጂዎች ተገኝተዋል።

c መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሚጠቀምባቸው ሰዎች ፈጽሞ ሊሳሳቱ እንደማይችሉ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ “ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለም” በማለት እውነታውን በግልጽ ያስቀምጣል።—1 ነገሥት 8:46

d አምላክ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሚጽፉትን ነገር ሁሉ ቃል በቃል አልነገራቸውም፤ በራሳቸው አባባል ተጠቅመው እሱ የሚፈልገውን መልእክት እንዲያስተላልፉ ያደረገበት ጊዜ አለ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ 2 ጴጥሮስ 1:21