በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ገናን የማያከብሩት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ገናን የማያከብሩት ለምንድን ነው?

የተሳሳቱ ግንዛቤዎች

  የሚባለው፦ የይሖዋ ምሥክሮች ገናን የማያከብሩት በኢየሱስ ስለማያምኑ ነው።

 ሐቁ፦ እኛ ክርስቲያኖች ነን። መዳን የሚገኘው በኢየሱስ በኩል ብቻ እንደሆነ እናምናለን።—የሐዋርያት ሥራ 4:12

 የሚባለው፦ ሰዎች ገናን እንዳያከብሩ በማስተማር ቤተሰብን ትከፋፍላላችሁ።

 ሐቁ፦ የቤተሰብ ጉዳይ በጣም ያሳስበናል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነውን ሐሳብ ተግባራዊ የምናደርገውም ጠንካራ የሆነ የቤተሰብ ትስስር እንዲኖር ነው።

 የሚባለው፦ በዓሉን ባለማክበራችሁ እንደ ልግስና፣ ዓለም አቀፍ ሰላም እና የመልካም ምኞት መግለጫ ያሉ ነገሮች ያመልጧችኋል።

 ሐቁ፦ ምንጊዜም ለጋስና ሰላማዊ ለመሆን እንጥራለን። (ምሳሌ 11:25፤ ሮም 12:18) ለምሳሌ ስብሰባችንን የምናከናውንበትና የምንሰብክበት መንገድ ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት ከሰጠው ትእዛዝ ጋር የሚስማማ ነው። (ማቴዎስ 10:8) በተጨማሪም በዓለም ላይ እውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርገው የአምላክ መንግሥት መሆኑን እንናገራለን።—ማቴዎስ 10:7

የይሖዋ ምሥክሮች ገናን የማያከብሩት ለምንድን ነው?

  •   ኢየሱስ እንድናከብር ያዘዘን የሞቱን መታሰቢያ እንጂ ልደቱን አይደለም።—ሉቃስ 22:19, 20

  •   የኢየሱስ ሐዋርያትም ሆኑ የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ገናን አላከበሩም። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “የኢየሱስ ልደት እስከ 243 [ዓ.ም.] ድረስ መከበር አልጀመረም ነበር።” ይህ ደግሞ ሐዋርያት ከሞቱ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ መሆኑ ነው።

  •   ኢየሱስ ታኅሣሥ 29 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 25) እንደተወለደ የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም፤ የተወለደበት ቀን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አልተጠቀሰም።

  •   የገና በዓል አምላክን አያስደስተውም፤ ምክንያቱም ከአረማውያን ልማድና ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:17

ገናን ባለማክበር ለምን የሰው ዓይን ውስጥ ትገባላችሁ?

 ብዙ ሰዎች፣ የገና አመጣጥ አረማዊ እንደሆነ ብሎም በዓሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደሌለው ቢያውቁም ያከብሩታል። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች የሚከተለውን ጥያቄ ያነሱ ይሆናል፦ ክርስቲያኖች በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የሚያሳጣ ነገር ለምን ያደርጋሉ? ለምን የሰው ዓይን ውስጥ ትገባላችሁ?

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማሰብ ችሎታችንን’ ተጠቅመን ነገሮችን እንድናመዛዝን ያበረታታናል። (ሮም 12:1, 2) ለእውነት ትልቅ ቦታ እንድንሰጥም ይመክረናል። (ዮሐንስ 4:23, 24) በመሆኑም ሰዎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት ቢያሳስበንም እንኳ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስንል የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ አንጥስም።

 ገናን ባናከብርም እያንዳንዱ ሰው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳለው እንገነዘባለን። በመሆኑም ሌሎች ገናን ሲያከብሩ ጣልቃ አንገባም።