በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ደስተኛውን አምላክ’ የሚያገለግሉ ደስተኞች ናቸው

‘ደስተኛውን አምላክ’ የሚያገለግሉ ደስተኞች ናቸው

“አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!”—መዝ. 144:15

መዝሙሮች፦ 44, 125

1. የይሖዋ አገልጋዮች ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

የይሖዋ ምሥክሮች ደስተኛ ሕዝቦች ናቸው። በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በሚገኙበት እንዲሁም ሰብሰብ ብለው በሚዝናኑበት ጊዜ ደስ በሚል መንገድ ሲጨዋወቱና ሲሳሳቁ መስማት የተለመደ ነው። የዚህን ያህል ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው? ዋናው ምክንያት “ደስተኛው አምላክ” የተባለውን ይሖዋን ስለሚያውቁ፣ ስለሚያገለግሉና እሱን ለመምሰል ጥረት ስለሚያደርጉ ነው። (1 ጢሞ. 1:11፤ መዝ. 16:11) አምላክ የደስታ ምንጭ በመሆኑ እኛም ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል፤ ደግሞም ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮችን ሰጥቶናል።—ዘዳ. 12:7፤ መክ. 3:12, 13

2, 3. (ሀ) ደስታ ምንድን ነው? (ለ) ደስተኛ መሆን ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?

2 አንተስ ደስተኛ ነህ? ይበልጥ ደስተኛ መሆንስ ትፈልጋለህ? ደስታ “አንጻራዊ ዘለቄታ ያለው የደህንነት ስሜት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። በተጨማሪም ደስታ “ባለንበት ሁኔታ ከመርካት አንስቶ በሕይወት በመኖራችን እስከሚሰማን ጥልቅና ከፍተኛ የሆነ ሐሴት ድረስ ያሉትን ስሜቶች ያጠቃልላል።” እውነተኛ ደስታ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚያገኙት ነገር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይሁንና በዛሬው ጊዜ ደስተኛ መሆን አስቸጋሪ ነው። ለምን?

3 አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ለምሳሌ የምንወደው ሰው ሲሞት ወይም ከጉባኤ ሲወገድ፣ ትዳራችን ሲፈርስ አሊያም ከሥራ ስንፈናቀል ደስታችንን ልናጣ እንችላለን። ከዚህም ሌላ በቤታችን ውስጥ ጠብና ጭቅጭቅ ካለ አሊያም የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች የሚያሾፉብን ከሆነ ደስታችን እንደሚቀንስ የታወቀ ነው። በእምነታችን ምክንያት ስደት ቢደርስብን ወይም ብንታሰር አሊያም ደግሞ ሥር የሰደደ የጤና እክል ወይም የመንፈስ ጭንቀት ቢኖርብን ደስተኞች መሆን ቀላል እንደማይሆንልን ጥያቄ የለውም። ሆኖም “ደስተኛውና ብቸኛው ኃያል ገዢ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ማጽናናትና ደስታ እንዲያገኙ መርዳት እንደሚያስደስተው እናስታውስ። (1 ጢሞ. 6:15፤ ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ፣ የሰይጣን ዓለም የሚያመጣቸው ችግሮችና ፈተናዎች ቢኖሩም እንኳ ደስተኞች ለመሆን የሚረዱንን ባሕርያት በተራራ ስብከቱ ላይ ጠቅሷል።

ለደስታ ቁልፉ ጠንካራ መንፈሳዊነት ነው

4, 5. ደስተኛ ለመሆንና ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዳን ምንድን ነው?

4 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ መጀመሪያ የጠቀሰው ለደስታ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ነው፤ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና” ብሏል። (ማቴ. 5:3) ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥማት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው? መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ፣ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ በመስጠት እንዲሁም ደስተኛ ለሆነው አምላክ የምናቀርበውን አምልኮ ከምንም ነገር በላይ በማስቀደም ነው። እንዲህ ካደረግን ደስታችን እየጨመረ ይሄዳል። አምላክ የሰጠን ተስፋ እንደሚፈጸም ያለን እምነትም ይጠናከራል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ‘አስደሳች የሆነ ተስፋ’ ችግሮች ቢያጋጥሙንም ለመጽናት ይረዳናል።—ቲቶ 2:13

5 ዘላቂ ደስታ ለማግኘት ቁልፉ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁልጊዜ [በይሖዋ] ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ፊልጵ. 4:4) ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና ለመመሥረት ግን መለኮታዊ ጥበብ ያስፈልገናል። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ጥበብን የሚያገኝ፣ ጥልቅ ግንዛቤንም የራሱ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው፤ ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፤ አጥብቀው የሚይዟትም ደስተኞች ይባላሉ።”—ምሳሌ 3:13, 18

6. ዘላቂ የሆነ ደስታ ማጣጣም የምንችለው ምን ካደረግን ብቻ ነው?

6 ዘላቂ የሆነ ደስታ ለማግኘት ግን የአምላክን ቃል ማንበብ ብቻ ሳይሆን ያነበብነውን በተግባር ማዋልም ይኖርብናል። ኢየሱስ የተማርነውን ነገር በተግባር የማዋልን አስፈላጊነት ሲያጎላ “እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ” ብሏል። (ዮሐ. 13:17፤ ያዕቆብ 1:25ን አንብብ።) መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካትም ሆነ ዘላቂ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ደስታችንን የሚሰርቁ ብዙ ነገሮች ባሉበት ዓለም ውስጥ እየኖርን ደስተኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ቀጥሎ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ እንመልከት።

ደስታ ለማግኘት የሚረዱ ባሕርያት

7. የሚያዝኑ ሰዎች ደስተኞች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?

7 “የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና።” (ማቴ. 5:4) ሆኖም የሚያዝኑ ሰዎች ደስተኞች ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ በየትኛውም ምክንያት የሚያዝኑ ሰዎች በሙሉ ደስተኞች እንደሚሆኑ መናገሩ አልነበረም። ክፉ ሰዎችም እንኳ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ” በተባለው በዚህ ዘመን ውስጥ ባሉት አስጨናቂ ሁኔታዎች ያዝናሉ። (2 ጢሞ. 3:1) ያም ቢሆን እነዚህ ሰዎች የሚያዝኑት የራሳቸው ሁኔታ ስለሚያሳስባቸው ብቻ በመሆኑ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት አይነሳሱም፤ እነዚህ ሰዎች ማዘናቸው ደስታ የማያስገኝላቸው ለዚህ ነው። ኢየሱስ የተናገረው መንፈሳዊ ነገሮችን ስለተጠሙ ሰዎች ነው፤ እነዚህ ግለሰቦች በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ከአምላክ መራቃቸውና እሱን በሚያስደስት መንገድ አለመኖራቸው ያሳዝናቸዋል። ኃጢአተኞች መሆናቸውን ስለሚገነዘቡ እንዲሁም መላው የሰው ዘር በኃጢአት መውደቁ ያስከተለውን መዘዝ ስለሚመለከቱ ያዝናሉ። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ከልባቸው የሚያዝኑ ሰዎችን ይመለከታል፤ እንዲሁም በቃሉ አማካኝነት ያጽናናቸዋል ብሎም ደስታና የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል።ሕዝቅኤል 5:11⁠ን እና 9:4ን አንብብ።

8. ገር መሆን ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

8 “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።” (ማቴ. 5:5) ገር መሆን ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሰዎች የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ሲቀስሙ የባሕርይ ለውጥ ያደርጋሉ። እነዚህ ሰዎች በአንድ ወቅት ጨካኝ፣ ጠበኛና ቁጡ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን ግን “አዲሱን ስብዕና” ስለለበሱ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን” ያሳያሉ። (ቆላ. 3:9-12) በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው ሰላም፣ ፍቅርና ደስታ የሰፈነበት ሆኗል። ከዚህም ሌላ የአምላክ ቃል እንደሚናገረው እንዲህ ያሉ ገር ሰዎች “ምድርን ይወርሳሉ።”—መዝ. 37:8-10, 29

9. (ሀ) ‘ገሮች ምድርን የሚወርሱት’ በምን መንገድ ነው? (ለ) “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው” የተባለው ለምንድን ነው?

9 ‘ገሮች ምድርን የሚወርሱት’ በምን መንገድ ነው? በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘ምድርን ይወርሳሉ’ የሚባለው ነገሥታትና ካህናት ሆነው ምድርን ስለሚያስተዳድሩ ነው። (ራእይ 20:6) ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ የሌላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ቢሆኑ ፍጹም ሆነው በምድር ላይ በሰላምና በደስታ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ስለሚያገኙ ምድርን ይወርሳሉ ሊባል ይችላል። ኢየሱስ “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው” ሲል ስለ እነዚህ ሁለት ቡድኖች መናገሩ ነበር። (ማቴ. 5:6) እነዚህ ሰዎች ለጽድቅ ያላቸው ረሃብና ጥማት በአዲሱ ዓለም በተሟላ ሁኔታ ይረካል። (2 ጴጥ. 3:13) አምላክ ክፋትን ከምድር ገጽ ጠራርጎ ሲያስወግድ ጻድቃን በክፉዎችና በዓመፀኞች ድርጊት ደስታቸውን ሳያጡ ለዘላለም መኖር ይችላሉ።—መዝ. 37:17

10. መሐሪ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

10 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።” (ማቴ. 5:7) መሐሪ መሆንን የሚያመለክተው የዕብራይስጥ ግስ ‘ሞቅ ያለ ስሜትና ርኅራኄ ማሳየት’ የሚል ፍቺ አለው። የግሪክኛው ግስም ቢሆን ችግር ለደረሰበት ሰው አዘኔታ ማሳየትን ያመለክታል። ሆኖም ምሕረት የአዘኔታ ስሜት ከማሳየት ያለፈ ነገርን ይጨምራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሕረት የሚለው ቃል የተሠራበት በአዘኔታ ስሜት ተነሳስቶ ሰዎችን ለመርዳት እርምጃ መውሰድን ለማመልከት ነው።

11. ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ ስለ ምሕረት ምን ያስተምረናል?

11 ሉቃስ 10:30-37ን አንብብ። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ ምሕረት ማሳየት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። ሳምራዊው ጉዳት ለደረሰበት ሰው ከልቡ ስላዘነለትና ስለራራለት የግለሰቡን ሥቃይ ለማስታገሥ አቅሙ የፈቀደውን አድርጓል። ኢየሱስ ምሳሌውን ከተናገረ በኋላ ለአይሁዳዊው “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” ብሎታል። እኛም እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘እኔስ እንደ ደጉ ሳምራዊ ርኅራኄ አሳያለሁ? ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ምሕረት በማሳየትና በደግነት እነሱን በመርዳት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እችል ይሆን? ለምሳሌ፣ በዕድሜ ለገፉ ክርስቲያኖች፣ ለመበለቶች እንዲሁም በመንፈሳዊ ሁኔታ ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት እችላለሁ? “የተጨነቁትን ለማጽናናት” ቅድሚያውን ወስጄ ጥረት አደርጋለሁ?’—1 ተሰ. 5:14፤ ያዕ. 1:27

ለሌሎች ምሕረት ለማሳየት ጥረት ማድረግ ታላቅ ደስታ ያስገኛል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. መሐሪ መሆናችን ደስታ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

12 ይሁን እንጂ መሐሪ መሆናችን ደስታ የሚያስገኝልን እንዴት ነው? ለሌሎች ምሕረት ስናሳይ፣ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን። በተጨማሪም ይሖዋን እያስደሰትን እንደሆነ ስለምናውቅ ደስተኞች እንሆናለን። (ሥራ 20:35፤ ዕብራውያን 13:16ን አንብብ።) ንጉሥ ዳዊት፣ ለሌሎች አሳቢነት የሚያሳይን ሰው በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል። በምድር ላይ ደስተኛ ይባላል።” (መዝ. 41:1, 2) ምሕረትና ርኅራኄ የምናሳይ ከሆነ ይሖዋም ምሕረት ያሳየናል፤ ይህ ደግሞ ለዘላለም ደስተኞች ለመሆን ያስችለናል።—ያዕ. 2:13

“ልባቸው ንጹሕ የሆነ” ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?

13, 14. “ልባቸው ንጹሕ የሆነ” ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?

13 ኢየሱስ “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 5:8) ልባችን ንጹሕ እንዲሆን አስተሳሰባችንም ሆነ ምኞታችን ንጹሕና ከርኩሰት የጸዳ መሆን አለበት። ይሖዋ አምልኳችንን እንዲቀበለው ከፈለግን እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።2 ቆሮንቶስ 4:2ን አንብብ፤ 1 ጢሞ. 1:5

14 ልባቸው ንጹሕ የሆነ ሰዎች በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም ይኖራቸዋል፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ይችላሉ። ይሖዋ “ልብሳቸውን የሚያጥቡ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ራእይ 22:14) “ልብሳቸውን የሚያጥቡ” ሲባል ምን ማለት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ‘ልብሳቸውን አጥበዋል’ የተባለው ይሖዋ ንጹሕ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ነው፤ ይሖዋ ለእነዚህ ክርስቲያኖች የማይሞት ሕይወት እንዲሁም በሰማይ ለዘላለም በደስታ የመኖር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ሕዝብም የአምላክ ወዳጆች በመሆናቸው ይሖዋ እንደ ጻድቅ አድርጎ ይመለከታቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በአሁኑ ጊዜም እንኳ ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም በማጠብ ነጭ አድርገውታል።’—ራእይ 7:9, 13, 14

15, 16. ልባቸው ንጹሕ የሆነ ሰዎች “አምላክን ያያሉ” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

15 ‘ማንም ሰው አምላክን አይቶ በሕይወት መኖር እንደማይችል’ የታወቀ ነው፤ ታዲያ ልባቸው ንጹሕ የሆነ ሰዎች “አምላክን ያያሉ” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ዘፀ. 33:20) “ያያሉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በዓይነ ሕሊና ማየት፣ መረዳት፣ ማወቅ” ተብሎም ሊፈታ ይችላል። በመሆኑም አምላክን ‘በልባቸው ዓይኖች’ የሚያዩት የእሱን ማንነትና ባሕርያት በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች ናቸው። (ኤፌ. 1:18) ኢየሱስ የአምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ስላንጸባረቀ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ብሎ ሊናገር ችሏል።—ዮሐ. 14:7-9

16 የይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች፣ የአምላክን ባሕርያት ከማወቅ በተጨማሪ እሱ በግለሰብ ደረጃ የሚያደርግላቸውን እርዳታ ስለሚመለከቱ ‘አምላክን ያዩታል።’ (ኢዮብ 42:5) ልባቸው ንጹሕ የሆነ ሰዎች ‘አምላክን የሚያዩበት’ ሌላም መንገድ አለ፤ ይህም አምላክ ንጹሕ ሆነው ለመኖርና እሱን በታማኝነት ለማገልገል ለሚጥሩ ሰዎች ባዘጋጃቸው አስደናቂ በረከቶች ላይ ‘የልባቸው ዓይኖች’ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነው። እርግጥ ነው፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሽልማታቸውን ሲቀበሉ ይሖዋን ቃል በቃል ያዩታል።—1 ዮሐ. 3:2

ችግሮች ቢደርሱብንም ደስተኛ መሆን

17. ሰላም ፈጣሪ መሆን ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ “ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው” በማለት ቀጥሎ ተናግሯል። (ማቴ. 5:9) ሰላም ለመፍጠር ቅድሚያውን ወስደው ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ደስተኞች ይሆናሉ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 3:18) ከአንድ የጉባኤያችን ወይም የቤተሰባችን አባል ጋር አለመግባባት ሲያጋጥመን፣ ሰላም ፈጣሪ ለመሆን እንዲረዳን አምላክን ልንለምነው እንችላለን። ይሖዋም በምላሹ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠን ሲሆን ይህም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ ያስችለናል፤ በውጤቱም ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ኢየሱስ፣ ቅድሚያውን ወስዶ ሰላም ፈጣሪ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲያጎላ እንዲህ ብሏል፦ “መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።”—ማቴ. 5:23, 24

18, 19. ክርስቲያኖች ስደት ቢደርስባቸውም ደስተኞች የሚሆኑት ለምንድን ነው?

18 “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።” ኢየሱስ እንዲህ ያለው ለምን ነበር? “በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና” በማለት መልሱን ሰጥቷል። (ማቴ. 5:11, 12) ሐዋርያት የተገረፉና መስበካቸውን እንዲያቆሙ የታዘዙ ቢሆንም ከሳንሄድሪን ሸንጎ የወጡት “ደስ እያላቸው” ነበር። እርግጥ ነው፣ ሐዋርያትን ያስደሰታቸው ግርፋቱ አይደለም። የተደሰቱት “ስለ [ኢየሱስ ስም] ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው” ነው።—ሥራ 5:41

19 በዛሬው ጊዜ ያለን የይሖዋ አገልጋዮችም ስለ ኢየሱስ ስም ውርደት ሲደርስብን ወይም ሌሎች ፈተናዎች ሲያጋጥሙን በደስታ እንጸናለን። (ያዕቆብ 1:2-4ን አንብብ።) እንደ ሐዋርያቱ ሁሉ እኛም የሚያስደስተን መከራ መቀበላችን አይደለም። ሆኖም ፈተና ሲያጋጥመን ታማኝነታችንን ከጠበቅን ይሖዋ እንድንጸና እንዲሁም ደስታችንን እንዳናጣ ይረዳናል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ነሐሴ 1944 የአንድ አምባገነናዊ መንግሥት ባለሥልጣናት ወንድም ሄንሪክ ዶርኒክንና ወንድሙን ወደ ማጎሪያ ካምፕ ልከዋቸው ነበር። ሆኖም ተቃዋሚዎቻቸው “እነሱን ምንም ነገር እንዲያደርጉ ማሳመን የማይቻል ነው። ሰማዕት መሆናቸው ያስደስታቸዋል” በማለት ተናግረው ነበር። ወንድም ዶርኒክ ግን እንዲህ ብሏል፦ “ሰማዕት የመሆን ፍላጎት ባይኖረኝም ለይሖዋ ታማኝ በመሆኔ የሚደርስብኝን ሥቃይ በድፍረትና በክብር መቀበሌ ያስደስተኝ ነበር። . . . ወደ ይሖዋ ከልቤ መጸለዬ ወደ እርሱ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል፤ እርሱም አስተማማኝ ረዳት ሆኖልኛል።”

20. ‘ደስተኛውን አምላክ’ ማገልገላችን የሚያስደስተን ለምንድን ነው?

20 ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነውን የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘን ማወቃችን፣ ስደት ወይም የቤተሰብ ተቃውሞ ቢያጋጥመን አሊያም ብንታመም ወይም ዕድሜያችን ቢገፋም ደስተኛ ለመሆን ይረዳናል። (1 ጢሞ. 1:11) ከዚህም ሌላ “ሊዋሽ የማይችለው አምላክ” የሰጠን አስደናቂ ተስፋ ደስተኛ እንድንሆን ያስችለናል። (ቲቶ 1:2) ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች ሲፈጸሙ የሚኖረው ሁኔታ በጣም አስደሳች ከመሆኑ የተነሳ፣ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙን መከራዎችና ችግሮች ሁሉ ከአእምሯችን ሙሉ በሙሉ ይፋቃሉ። ይሖዋ በገነት ውስጥ የሚሰጠን በረከት ከምንጠብቀው በእጅጉ የላቀ ይሆናል። ከዚያ ቀደም አይተን የማናውቀው ዓይነት ደስታ ይኖረናል። በእርግጥም ‘በብዙ ሰላም እጅግ ደስ ይለናል።’—መዝ. 37:11