በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምን ታመለክታለች?

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምን ታመለክታለች?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” የሚለው መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል፤ ይህች ምሳሌያዊት ከተማ የምታመለክተው፣ ከኢየሱስ ጋር በአምላክ መንግሥት ውስጥ አብረው ለመግዛት ወደ ሰማይ የሚሄዱትን የኢየሱስ ተከታዮች ቡድን ነው። (ራእይ 3:12፤ 21:2) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ቡድን የክርስቶስ ሙሽራ ተብሎም ሊጠራ እንደሚችል ይናገራል።

አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምን እንደምታመለክት ለማወቅ የሚረዱ ነጥቦች

  1.   አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የምትገኘው በሰማይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚለውን መግለጫ በተጠቀመባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ከተማዋ ከሰማይ የምትወርድ እንደሆነች ይናገራል፤ የዚህችን ከተማ በሮች የሚጠብቁትም መላእክት ናቸው። (ራእይ 3:12፤ 21:2, 10, 12) ከተማዋ በጣም ትልቅ መሆኗ በራሱ የምትገኘው በምድር ላይ እንዳልሆነ ያሳያል። ከተማዋ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላት ሲሆን ስትለካም “12,000 ስታዲዮን” ማለትም 2,220 ኪሎ ሜትር ገደማ ነበረች። a (ራእይ 21:16) በመሆኑም እያንዳንዱ የከተማዋ ጎን 560 ኪሎ ሜትር ገደማ ከፍታ ነበረው ማለት ነው።

  2.   አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣ የተገነባችው የክርስቶስ ሙሽራ እንደሆኑ በተገለጹት የኢየሱስ ተከታዮች ቡድን ነው። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ‘የበጉ ሚስት፣ ሙሽራይቱ’ ተብላ ተጠርታለች። (ራእይ 21:9, 10) በዚህ ምሳሌያዊ አገላለጽ ላይ በግ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዮሐንስ 1:29፤ ራእይ 5:12) ‘የበጉ ሚስት’ ወይም የክርስቶስ ሙሽራ የተባለችው ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ለመሆን ወደ ሰማይ የሚሄዱ ክርስቲያኖችን ታመለክታለች። መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስና በእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ዝምድና በባልና ሚስት መካከል ካለው ዝምድና ጋር ያመሳስለዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:2፤ ኤፌሶን 5:23-25) በተጨማሪም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም የመሠረት ድንጋዮች ላይ “የ12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች” ተጽፎ ነበር። (ራእይ 21:14) ይህ ሐሳብ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምን እንደምታመለክት በእርግጠኝነት ለማወቅ ይረዳናል፤ ምክንያቱም ወደ ሰማይ የሚሄዱት ክርስቲያኖች “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ” የተገነቡ ናቸው።—ኤፌሶን 2:20

  3.   አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የአምላክ መንግሥት ክፍል ናት። የጥንቷ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ነበረች፤ ንጉሥ ዳዊት፣ ልጁ ሰለሞን እንዲሁም ዘሮቻቸው የገዙት “በይሖዋ ዙፋን ላይ” ሆነው ነበር። (1 ዜና መዋዕል 29:23) ኢየሩሳሌም “ቅድስቲቱ ከተማ” ተብላ ተጠርታለች፤ በመሆኑም ኢየሩሳሌም ከዳዊት ዘር በሚመጡ ነገሥታት የሚመራውን የአምላክ መስተዳደር ትወክል ነበር። (ነህምያ 11:1) አዲሲቱ ኢየሩሳሌምም “ቅድስቲቱ ከተማ” ተብላ ተጠርታለች፤ የተዋቀረችውም ከኢየሱስ ጋር ለመግዛት ወደ ሰማይ ከሚሄዱትና ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው’ ከሚገዙት ክርስቲያኖች ነው።—ራእይ 5:9, 10፤ 21:2

  4.   አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በምድር ለሚኖሩ ሰዎች በረከት ታመጣለች። አዲሲቱ ኢየሩሳሌም “ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ” ታይታለች፤ ይህም አምላክ ከሰማይ ውጪ ያሉ ነገሮችን ለማከናወን መሣሪያ አድርጎ እንደሚጠቀምባት ያሳያል። (ራእይ 21:2) በተጨማሪም ይህ አገላለጽ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ከአምላክ መንግሥት ጋር ያዛምዳታል፤ አምላክ ይህን መንግሥት “ፈቃዱ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲፈጸም’ ለማድረግ ይጠቀምበታል። (ማቴዎስ 6:10) አምላክ በምድር ላይ ለሚኖሩ የሰው ልጆች ከሚያመጣቸው በረከቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

    •   ኃጢአት ይወገዳል። ከአዲሲቱ ኢየሩሳሌም “የሕይወት ውኃ ወንዝ” የሚፈስ ሲሆን ይህ ወንዝ “ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ” “የሕይወት ዛፎች” ውኃ እንዲያገኙ ያደርጋል። (ራእይ 22:1, 2) ይህ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ፈውስ፣ ኃጢአትን ያስወግዳል እንዲሁም ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያስችላል፤ ይህም አምላክ ከመጀመሪያው አንስቶ ለሰው ልጆች የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ሮም 8:21

    •   በአምላክና በሰዎች መካከል ጥሩ ዝምድና ይኖራል። ኃጢአት የሰው ልጆችን ከአምላክ ለያይቷል። (ኢሳይያስ 59:2) በመሆኑም የኃጢአት መወገድ የሚከተለው ትንቢት በተሟላ መንገድ እንዲፈጸም ያስችላል፦ “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል።”—ራእይ 21:3

    •   መከራና ሞት አይኖርም። አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:4

a ስታዲዮን ሮማውያን ይጠቀሙበት የነበረ የርዝመት መለኪያ ሲሆን አንድ ስታዲዮን 185 ሜትር ነው።