በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኃጢአት ምንድን ነው?

ኃጢአት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ከአምላክ መሥፈርት ጋር የሚቃረን ማንኛውም ድርጊት፣ ስሜት ወይም አስተሳሰብ ኃጢአት ይባላል። በአምላክ ዓይን ስህተት ወይም የዓመፅ ድርጊት የሆነን ነገር በመፈጸም የእሱን ሕግ መጣስን ይጨምራል። (1 ዮሐንስ 3:4፤ 5:17) ተገቢ የሆነውን ነገር ሳያደርጉ መቅረት ማለትም ትክክል የሆነውን ነገር አለማድረግም ኃጢአት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—ያዕቆብ 4:17

 መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ኃጢአት መሥራት የሚለው አገላለጽ “ዒላማን መሳት” የሚል ትርጉም አለው። ለምሳሌ በጥንት እስራኤል የነበሩ አንዳንድ ወታደሮች ድንጋይ በመወንጨፍ በጣም የተካኑ ከመሆናቸው የተነሳ ዒላማውን ‘አይስቱም’ ነበር። ይህ አገላለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “ኃጢአት አይሠሩም” የሚል ሊሆን ይችላል። (መሳፍንት 20:16) ስለዚህ ኃጢአት መሥራት ሲባል ፍጹም የሆኑትን የአምላክ መሥፈርቶች ‘መሳት’ ማለት ነው።

 አምላክ፣ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የሰው ልጆች የሚመሩባቸውን መሥፈርቶች የማውጣት መብት አለው። (ራእይ 4:11) በመሆኑም ለምናደርጋቸው ነገሮች በእሱ ዘንድ ተጠያቂ ነን።—ሮም 14:12

ፈጽሞ ኃጢአት አለመሥራት ይቻላል?

 አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” ይላል። (ሮም 3:23፤ 1 ነገሥት 8:46፤ መክብብ 7:20፤ 1 ዮሐንስ 1:8) ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

 የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማለትም አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ኃጢአት አልነበረባቸውም። ምክንያቱም የተፈጠሩት በአምላክ መልክ ከመሆኑም ሌላ ፍጹማን ነበሩ። (ዘፍጥረት 1:27) ያም ሆኖ አምላክን ባለመታዘዛቸው ፍጽምናቸውን አጡ። (ዘፍጥረት 3:5, 6, 17-19) ልጆች ሲወልዱ ደግሞ ይህን ኃጢአትና አለፍጽምና አወረሷቸው። (ሮም 5:12) የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “በደለኛ ሆኜ ተወለድኩ” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 51:5

አንዱ ኃጢአት ከሌላው የከፋ ሊሆን ይችላል?

 አዎ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቷ ሰዶም “ከባድ ኃጢአት የሚፈጽሙ ክፉ ሰዎች” እንደነበሩና “ኃጢአታቸውም እጅግ ከባድ” እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍጥረት 13:13፤ 18:20) አንድን ኃጢአት ከባድ የሚያስብሉትን ሦስት ነጥቦች እስቲ እንመልከት።

  1.   የጥፋቱ ክብደት። መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ብልግናን፣ ጣዖት አምልኮን፣ ሌብነትን፣ ስካርን፣ ቀማኝነትን፣ ግድያን እና መናፍስታዊ ድርጊትን ጨምሮ ከባድ ኃጢአቶችን ከመፈጸም እንድንርቅ ያስጠነቅቃል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ራእይ 21:8) በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሳናስብ ስለምንፈጽማቸው ኃጢአቶችም ይናገራል፤ ከእነዚህ መካከል ሌሎችን ሊጎዳ የሚችል ንግግር ወይም ምግባር ይገኝበታል። (ምሳሌ 12:18፤ ኤፌሶን 4:31, 32) ያም ሆነ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ኃጢአት አቅልለን እንዳንመለከት ይመክረናል፤ ምክንያቱም ቀላል የሚመስሉ ኃጢአቶች እንኳ ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸምና የአምላክን ሕግ ወደ መተላለፍ ሊያመሩ ይችላሉ።—ማቴዎስ 5:27, 28

  2.   የልብ ዝንባሌ። አንዳንድ ሰዎች ኃጢአት የሚፈጽሙት የአምላክን መመሪያዎች ስለማያውቁ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:30፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:13) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶች ዝም ተብለው እንደሚታለፉ ባይገልጽም ሆን ብሎ የአምላክን ሕግ በመጣስ ከሚፈጸሙ ኃጢአቶች የተለዩ እንደሆኑ ይናገራል። (ዘኁልቁ 15:30, 31) ምክንያቱም አንድ ሰው ሆን ብሎ ኃጢአት የሚፈጽመው ‘ክፉ ልብ’ ካለው ነው።—ኤርምያስ 16:12

  3.   ጥፋቱ መደጋገሙ። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጊዜ ኃጢአት በመፈጸምና ረዘም ላለ ጊዜ ኃጢአትን ልማድ በማድረግ መካከል ልዩነት እንዳለ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:4-8) ትክክል ስለሆነው ነገር ከተማሩ በኋላም እንኳ ‘ሆን ብለው በኃጢአት ጎዳና የሚመላለሱ’ ሰዎች ከአምላክ ቅጣት አያመልጡም።—ዕብራውያን 10:26, 27

 ከባድ ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች በኃጢአታቸው ክብደት የተነሳ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት “የፈጸምኳቸው ስህተቶች በራሴ ላይ ያንዣብባሉና፤ እንደ ከባድ ሸክም በጣም ከብደውኛል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 38:4) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል፦ “ክፉ ሰው መንገዱን፣ መጥፎ ሰውም ሐሳቡን ይተው፤ ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።”—ኢሳይያስ 55:7