በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የአምላክ መንግሥት፣ ይሖዋ አምላክ ያቋቋመው እውን የሆነ መስተዳድር ነው። “የአምላክ መንግሥት” በሰማይ ሆኖ ስለሚያስተዳድር “መንግሥተ ሰማያት” ተብሎም ተጠርቷል። (ማርቆስ 1:14, 15፤ ማቴዎስ 4:17) ይህ መንግሥት ከሰብዓዊ መንግሥታት ጋር የሚያመሳስሉት ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ከእነዚህ መንግሥታት በሁሉም መንገድ የላቀ ነው።

  •   ገዢዎች። አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን የዚህ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል፤ እንዲሁም የትኛውም ሰብዓዊ ገዢ ሊኖረው ከሚችለው የበለጠ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ማቴዎስ 28:18) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እምነት የሚጣልበትና ርኅሩኅ መሪ መሆኑን ስላስመሠከረ ይህን ሥልጣኑን የሚጠቀምበት በጎ ለማድረግ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ማቴዎስ 4:23፤ ማርቆስ 1:40, 41፤ 6:31-34፤ ሉቃስ 7:11-17) ኢየሱስ፣ ከእሱ ጋር በሰማይ የሚሆኑ ሰዎችን በአምላክ አመራር ሥር ሆኖ ከሁሉም ብሔራት መርጧል፤ እነዚህ ሰዎች ከእሱ ጋር ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።’​—ራእይ 5:9, 10

  •   የግዛት ዘመን። በየጊዜው ከሚለዋወጡት ሰብዓዊ መንግሥታት በተለየ መልኩ የአምላክ መንግሥት “ፈጽሞ የማይፈርስ” ነው።​—ዳንኤል 2:44

  •   ተገዢዎች። ሰዎች፣ ዘራቸው ወይም የትውልድ ቦታቸው ምንም ይሁን ምን የአምላክን ፈቃድ እስካደረጉ ድረስ የአምላክ መንግሥት ዜጎች መሆን ይችላሉ።​—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

  •   ሕግጋት። የአምላክ መንግሥት ሕግጋት (ወይም ትእዛዞች) ሰዎች መጥፎ ነገር እንዳያደርጉ በመከልከል ብቻ አይወሰኑም። እነዚህ ሕግጋት ዜጎቹ የተሻለ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።” (ማቴዎስ 22:37-39) የአምላክ መንግሥት ዜጎች፣ ለአምላክና ለባልንጀራቸው ያላቸው ፍቅር ሌሎችን የሚጠቅም ነገር እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።

  •   ትምህርት። የአምላክ መንግሥት ዜጎች ላቅ ያሉ መሥፈርቶችን እንዲከተሉ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህን ማድረግ የሚችሉበትን መንገድም ይማራሉ።​—ኢሳይያስ 48:17, 18

  •   ተልዕኮ። የአምላክ መንግሥት፣ ዜጎቹን በመበደል የገዢዎቹን ጥቅም አያራምድም። ከዚህ ይልቅ አምላክ፣ እሱን የሚወዱ ሁሉ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ያለውን ዓላማ ጨምሮ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም ያደርጋል።​—ኢሳይያስ 35:1, 5, 6፤ ማቴዎስ 6:10፤ ራእይ 21:1-4