በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጊዜም አድናቂ ሁን

ምንጊዜም አድናቂ ሁን

3ኛው ቁልፍ

ምንጊዜም አድናቂ ሁን

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “ስለ ሁሉም ነገር አመስግኑ።”—1 ተሰሎንቄ 5:18

ተፈታታኙ ሁኔታ ምንድን ነው? በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ትዕቢተኛና የማያመሰግኑ ስለሆኑ እነዚህ ባሕርያት በቀላሉ ሊጋቡብን ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ከዚህም በላይ ሕይወታችን በውጥረት የተሞላ ሆኖ ሳለ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ላይ ሌሎች ተጨማሪ ነገሮችን ማከናወን እንዳለብን ይሰማን ይሆናል። ያሉንን ነገሮች ለማድነቅ ወይም ሌሎች ላደረጉልን ነገሮች አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ጊዜ እስክናጣ ድረስ በችግሮች ልንተበተብ ወይም የራሳችንን ፍላጎት ብቻ በማሳደድ ልንጠመድ እንችላለን።

ምን ማድረግ ትችላለህ? ባሉህ ጥሩ ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። እርግጥ ነው፣ በችግሮች እንደተተበተብህ ይሰማህ ይሆናል። እስቲ ንጉሥ ዳዊት የተወልንን ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት ያጋጠሙት ችግሮች እንዳደቀቁትና ልቡ እንደዛለ የተሰማው ጊዜ ነበር። እንደዚያም ሆኖ “ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ አውጠነጠንሁ” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (መዝሙር 143:3-5) ዳዊት በርካታ ችግሮች የደረሱበት ቢሆንም ምንጊዜም አመስጋኝና ባለው የሚረካ ሰው ነበር።

ሌሎች አንተን ለመርዳት ምን እንዳደረጉ ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ላደረጉት ጥረት አመስግናቸው። ኢየሱስ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ወዳጁ የነበረችው ማርያም በጣም ውድ የሆነ ሽቱ በራሱና በእግሮቹ ላይ ባፈሰሰች ጊዜ አንዳንዶች “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል?” የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር። * ይህን ቅሬታ ያሰሙት ሰዎች፣ ሽቱው ተሽጦ ገንዘቡ ለድሆች ሊሰጥ ይችል እንደነበረ ተሰምቷቸው ነበር። ኢየሱስ ግን “ተዉአት። ለምን ታስቸግሯታላችሁ?” አላቸው። አክሎም “እሷ የምትችለውን አድርጋለች” አለ። (ማርቆስ 14:3-8፤ ዮሐንስ 12:3) ኢየሱስ ማርያም ባላደረገችው ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ላደረገችው ነገር አድናቆቱን ገልጿል።

አንዳንዶች የቤተሰብ ሕይወትን፣ ጓደኝነትን ወይም መልካም የሆነን ሌላ ነገር የሚያደንቁት ካጡት በኋላ ነው። አንተ ግን አሁን ባሉህ ጥሩ ነገሮች ላይ በማሰላሰል እንደዚህ ካለው አሳዛኝ ነገር መዳን ትችላለህ! ታዲያ ያሉህን ጥሩ ነገሮች ወደ አእምሮህ በማምጣት ወይም በጽሑፍ በማስፈር ለማሰላሰል ለምን አትሞክርም?

አምላክ ‘የመልካም ስጦታ ሁሉ’ ምንጭ ስለሆነ በጸሎት አመስጋኝነታችንን ልንገልጽለት ይገባል። (ያዕቆብ 1:17) አዘውትረን መጸለያችን ምንጊዜም አመስጋኝ እንድንሆንና ባለን ረክተን እንድንኖር ሊረዳን ይችላል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በእንግድነት በመጣ ሰው ራስ ላይ ሽቱ ማፍሰስ የቤቱ ባለቤት እንግዳው በመምጣቱ ደስ መሰኘቱን የሚያሳይ ተግባር ነበር፤ በእንግዳው እግር ላይ ሽቱ ማፍሰስ ደግሞ ትሕትናን የሚያሳይ ነበር።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሌሎች ላደረጉልህ ነገር አድናቆትህን ትገልጻለህ?