በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ትዳር

አድናቆት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

አድናቆት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

አድናቆት መግለጽ ለስኬታማ ትዳር ወሳኝ ነገር ነው። ይሁንና በርካታ ባለትዳሮች የትዳር ጓደኛቸውን ጥሩ ባሕርይ ማድነቅ ይቅርና የትኞቹ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት እንኳ ማስተዋል ተስኗቸዋል። አንድ አማካሪ ኢሞሽናል ኢንፊደሊቲ በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደገለጹት ወደ እሳቸው የሚመጡት አብዛኞቹ ባለትዳሮች “የሚያተኩሩት [ከትዳራቸው] በሚያገኙት ነገር ላይ ሳይሆን ባጡት ነገር ላይ ነው።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ወደ ቢሮዬ ሲመጡ የሚነግሩኝ፣ እንዲለወጥ ስለሚፈልጉት ነገር እንጂ እንዳለ መቀጠል ስለሚገባው ነገር አይደለም። እነዚህ ሰዎች የሚሠሩት ትልቁ ስህተት አድናቆታቸውን በመግለጽ ፍቅር አለማሳየት ነው።”

እናንተስ ከዚህ አደጋ መራቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

አድናቆትን መግለጽ በትዳር ውስጥ የሚፈጠርን ውጥረት ለመቀነስ ይረዳል። አንድ ባልና ሚስት፣ አንዳቸው የሌላውን ጥሩ ባሕርይ ለማስተዋልና ለማድነቅ ጥረት ሲያደርጉ ግንኙነታቸው በእጅጉ ይሻሻላል። ባለትዳሮች የትዳር ጓደኛቸው እንደሚያደንቃቸው የሚሰማቸው ከሆነ በመካከላቸው ከባድ ውጥረት ቢፈጠርም እንኳ ሊፈቱት ይችላሉ።

ለሚስቶች፦ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኢሞሽናል ኢንፊደሊቲ የተባለው መጽሐፍ “በርካታ ሴቶች ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር የማቅረብ ኃላፊነት በወንዶች ላይ የሚፈጥረውን ጫና አቅልለው ይመለከቱታል” በማለት ይናገራል። ሥራ የሚሠሩት ሁለቱም ቢሆኑም እንኳ በአንዳንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ይህ ጉዳይ ይበልጥ የሚያስጨንቀው ወንዶቹን ነው።

ለባሎች፦ አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች፣ ሚስቶች ልጅ በማሳደግ እንዲሁም ቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ በመሥራት ቤተሰቡን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት አቅልለው ይመለከቱታል። በትዳር ሕይወት ሦስት ዓመት ገደማ ያሳለፈችው ፊዮና * እንዲህ ብላለች፦ “ሁሉም ሰው ስህተት እንደሚሠራ የታወቀ ነው፤ እኔም ስህተት ስሠራ በጣም አዝናለሁ። ሆኖም ባለቤቴ ቤት ውስጥ ለሠራሁት ሥራ ሲያመሰግነኝ ድክመት ቢኖርብኝም እንደሚወደኝ ይሰማኛል። እንዲሁም የሚደግፈኝ ሰው እንዳለ ስለሚሰማኝ ደስ ይለኛል!”

በተቃራኒው ደግሞ አንድ ባል ወይም ሚስት ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጣቸው የሚሰማቸው ከሆነ ትዳራቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ቫለሪ የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “የትዳር ጓደኛችሁ ለእናንተ ምንም አድናቆት እንደሌለው የሚሰማችሁ ከሆነ ለእናንተ አድናቆት እንዳለው ወደሚያሳይ ሰው በቀላሉ ልትሳቡ ትችላላችሁ።”

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

አስተዋይ ሁኑ። በቀጣዩ ሳምንት የትዳር ጓደኛችሁ የሚያሳየውን ወይም የምታሳየውን ጥሩ ባሕርይ ትኩረት ሰጥታችሁ ተመልከቱ። በተጨማሪም ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር በማሟላት ረገድ የሚያደርገውን ወይም የምታደርገውን ጥረት ለማስተዋል ሞክሩ፤ ምናልባትም እስካሁን ድረስ ለእነዚህ ነገሮች እምብዛም ትኩረት አልሰጣችሁ ይሆናል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ (1) የምታደንቁትን የትዳር ጓደኛችሁን ባሕርይ እንዲሁም (2) የትዳር ጓደኛችሁ ያደረጋቸውን ወይም ያደረገቻቸውን ለቤተሰቡ የሚጠቅሙ ነገሮች በዝርዝር ጻፉ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ፊልጵስዩስ 4:8

አስተዋይ መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ኤሪካ የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “በትዳር ሕይወት የተወሰኑ ዓመታትን ካሳለፋችሁ በኋላ ለትዳር ጓደኛችሁ ትኩረት መስጠት ልታቆሙ ትችላላችሁ። የትዳር ጓደኛችሁ ባሉት ጥሩ ባሕርያት ላይ ማተኮር ታቆሙና በሌሉት ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ትጀምራላችሁ።”

ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘የትዳር ጓደኛዬ የሚያደርገውን ወይም የምታደርገውን ጥረት አቅልዬ እመለከታለሁ?’ ለምሳሌ ያህል፣ ባለቤትሽ ቤት ውስጥ አንድ ነገር በሚጠግንበት ጊዜ ይህን ማድረግ ግዴታው እንደሆነ በማሰብ እሱን ከማመስገን ትቆጠቢያለሽ? ባል ከሆንክ ደግሞ ልጆችን መንከባከብ የባለቤትህ ግዴታ እንደሆነ በማሰብ ባለቤትህ የምታደርገውን ጥረት ከማድነቅ ወደኋላ ትላለህ? የትዳር ጓደኛችሁ ለቤተሰባችሁ ጥቅም ሲል የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ለማስተዋልና ለማመስገን ግብ አውጡ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሮም 12:10

የማመስገን ልማድ አዳብሩ። መጽሐፍ ቅዱስ እንድናመሰግን ብቻ ሳይሆን ‘አመስጋኝ መሆናችንን እንድናሳይም’ ይነግረናል። (ቆላስይስ 3:15) በመሆኑም የትዳር ጓደኛችሁን የማመስገን ልማድ አዳብሩ። ጄምስ የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ለማደርጋቸው ነገሮች አድናቆቷን ስትገልጽልኝ የተሻልኩ ባል ለመሆን እንዲሁም ትዳራችንን ስኬታማ ለማድረግ ይበልጥ ጥረት ለማድረግ እነሳሳለሁ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ቆላስይስ 4:6

ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን አድናቆት የሚገልጹ ከሆነ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ይጠናከራል። ማይክል የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “ባለትዳሮች የትዳር ጓደኛቸው ባሉት ጥሩ ነገሮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ከሆነ ብዙ ትዳሮች ከመፍረስ ይድናሉ የሚል እምነት አለኝ። እንዲህ ያሉ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸው ያለውን ጥሩ ጎን አዘውትረው ስለሚያስቡ ችግሮች ሲፈጠሩ ትዳሩን ለማፍረስ አይቸኩሉም።”

^ አን.9 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።