በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈገግታ—ትልቅ ስጦታ!

ፈገግታ—ትልቅ ስጦታ!

አንድ ሰው ሞቅ ያለ ፈገግታ ሲያሳይህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? መልሰህ ፈገግ ማለትህ አይቀርም። እንዲሁም ደስታ ይሰማሃል። አዎ፣ ጓደኞቻችንም ሆኑ የማናውቃቸው ሰዎች ፈገግታ ሲያሳዩን እኛም መልሰን ፈገግ እንላለን፤ ጥሩ ስሜትም ይሰማናል። ባለቤቷ በሞት የተለያት ማግዳሌና የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ጌኦርግ ደስ የሚል ፈገግታ ነበረው። ዓይን ለዓይን ስንገጣጠም የመረጋጋትና የደህንነት ስሜት ይሰማኝ ነበር።”

ከልብ የመነጨ ፈገግታ፣ አንድ ሰው ደስታና እርካታ እንደተሰማው ያሳያል። አሶሴሽን ፎር ሳይኮሎጂካል ሳይንስ የሚያዘጋጀው ኦብዘርቨር የተባለ ኢንተርኔት ላይ የሚወጣ ጽሑፍ “ፈገግታ . . . አብሮን የተፈጠረ ነገር ይመስላል” ብሏል። ጽሑፉ እንደጠቀሰው ገና የተወለዱ ሕፃናትም እንኳ “በፊታችን ላይ የሚታየውን ስሜት በትክክል ማንበብ ይችላሉ።” ጽሑፉ አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሰዎች የአንድን ሰው ፈገግታ ሲመለከቱ ግለሰቡ ምን እንደተሰማው ብቻ ሳይሆን እነሱ ራሳቸውም ምን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።” *

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ በዕድሜ የገፉ ሕመምተኞች በአስታማሚዎቻቸው ፊት ላይ የሚያዩት ስሜት ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ለመመልከት ጥናት አካሂደው ነበር። በአስታማሚዎቹ ፊት ላይ “የወዳጅነት፣ የአሳቢነትና የርኅራኄ ስሜት ሲታይ” ሕመምተኞቹ ይበልጥ እንደሚደሰቱና አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጤንነታቸው እንደሚሻሻል ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል። በአስታማሚዎቹ ፊት ላይ ከላይ የተገለጹት ስሜቶች የማይነበቡ ከሆነ ግን ውጤቱ የተገላቢጦሽ ይሆናል።

ፈገግ ማለትህ አንተንም ሊጠቅምህ ይችላል። ፈገግ ማለት በራስ የመተማመን ስሜትን እንደሚጨምር እንዲሁም ውጥረትን እንደሚቀንስ አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ። በአንጻሩ ግን መኮሳተር ተቃራኒ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ታይቷል።

ፈገግታ “ድፍረት ጨምሮልኛል”

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ማግዳሌና የይሖዋ ምሥክር ነች። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚን ርዕዮተ ዓለም ለመደገፍ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ከሌሎች የቤተሰቧ አባላት ጋር በጀርመን ወደሚገኘው ራቨንስብሩክ ማጎሪያ ካምፕ ተወስዳ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ጠባቂዎቹ ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳናወራ የሚከለክሉን ጊዜ ነበር። በፊታችን ላይ የሚነበበውን ስሜት ግን መቆጣጠር አይችሉም። የእናቴንና የእህቴን ፈገግታ ማየቴ ብቻ ድፍረት ጨምሮልኛል፤ እንዲሁም ለመጽናት ያደረግኩትን ቁርጠኝነት አጠናክሮልኛል።”

ሕይወት በጭንቀት የተሞላ እንደመሆኑ መጠን ፈገግ የሚያሰኝ ነገር እንደሌለ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም የሚሰማህ ስሜት የምታስበው ነገር ነጸብራቅ እንደሆነ አስታውስ። (ምሳሌ 15:15፤ ፊልጵስዩስ 4:8, 9) ታዲያ ቀላል ባይሆንም እንኳ በተቻለህ መጠን ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ለማሰብ ለምን አትሞክርም? * ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸውና መጸለያቸው በዚህ ረገድ ጠቅሟቸዋል። (ማቴዎስ 5:3፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) እንዲያውም “ደስታ” እና “ሐሴት” የሚሉት ቃላትና ከእነዚህ ቃላት የተመሠረቱ ሌሎች ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ! ታዲያ በየቀኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ወይም ሁለት ገጽ ለማንበብ ለምን አትሞክርም? ምናልባት አንተም ፈገግ ለማለት ምክንያት የሚሆኑ ተጨማሪ ነገሮችን ታገኝ ይሆናል።

በተጨማሪም ሌሎች ፈገግታ እስኪያሳዩህ ድረስ አትጠብቅ። ቅድሚያውን ወስደህ ፈገግ በማለት ሌሎች ደስተኛ የሚሆኑበት ተጨማሪ ምክንያት እንዲያገኙ አድርግ። አዎ፣ ፈገግታን ራስህን እና ሌሎችን ይበልጥ ደስተኛ እንደሚያደርግ የአምላክ ስጦታ አድርገህ ተመልከተው።

^ አን.3 መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም አምላክ ፈገግ እንዳለ ይገልጻል። መዝሙር 119:135 እንዲህ ይላል፦ “ለአገልጋይህ ፈገግታ [ሞገስ] አሳይ።”—የግርጌ ማስታወሻ

^ አን.8 በኅዳር 2013 ንቁ! ላይ የወጣውን “‘ሁልጊዜ ግብዣ’ ላይ ነህ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።