በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥበበኛ ሴት ሕሊናዋ የሚነግራትን ትሰማለች

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? | ፅንስ ማስወረድ

ፅንስ ማስወረድ

ፅንስ ማስወረድ

በየዓመቱ ከ50 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፅንሶች ሆን ተብሎ ውርጃ ይፈጸምባቸዋል፤ ይህ ቁጥር በርካታ አገሮች ካላቸው የሕዝብ ብዛት ይበልጣል።

ለምርጫ የተተወ ጉዳይ ወይስ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት?

ሰዎች ምን ይላሉ?

በርካታ ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ውርጃ ይፈጽማሉ፤ እንደ ምክንያት ከሚጠቅሷቸው ነገሮች መካከል የኢኮኖሚ ችግር፣ ከጓደኛ ጋር መለያየት፣ ተጨማሪ ትምህርት የመከታተል ወይም በሥራ የመሰማራት ፍላጎት ወይም ነጠላ ወላጅ መሆን አለመፈለግ ይገኙበታል። ሆኖም ፅንስ ማስወረድ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንደሆነ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ሰዎች ‘አንዲት ሴት ፅንስ ማስወረዷ የእናትነት ኃላፊነቷን እንዳላከበረች የሚያሳይ ነው’ ይላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በአምላክ ዓይን ሕይወት፣ በተለይ ደግሞ የሰው ሕይወት ቅዱስ ነው። (ዘፍጥረት 9:6፤ መዝሙር 36:9) አምላክ ለሕፃኑ እድገት ተስማሚ አድርጎ ባዘጋጀው ማህፀን ውስጥ ያለ ልጅ ሕይወትም ቢሆን በአምላክ ዘንድ ቅዱስ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “በእናቴ ማህፀን ውስጥ ጋርደህ አስቀመጥከኝ። ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ፤ . . . የተሠሩባቸውን ቀኖች በተመለከተ በዝርዝር ተጻፈ።”—መዝሙር 139:13, 16

አምላክ ለሕይወት ያለው አመለካከት ለእስራኤል ብሔር በሰጠው ሕግ እንዲሁም የእሱ ስጦታ በሆነው ሕሊናችን ላይም ተንጸባርቋል። የአምላክ ሕግ በአንዲት እርጉዝ ሴት ላይ ጥቃት በመሰንዘር በማህፀኗ ውስጥ ያለውን ልጅ የገደለ ሰው በሞት እንዲቀጣ ያዛል፤ በዚህ መንገድ ግለሰቡ ባጠፋው ሕይወት ምትክ የራሱን ሕይወት ይከፍላል። (ዘፀአት 21:22-25) እርግጥ ነው፣ ዳኞቹ ግለሰቡ እንደዚያ ያደረገው ሆን ብሎ መሆን አለመሆኑን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ነበረባቸው።—ዘኁልቁ 35:22-24, 31

የሰው ልጆች ሕሊናም ተሰጥቷቸዋል። አንዲት ሴት ሕሊናዋ የሚያሰማውን ድምፅ በመስማት በማህፀኗ ውስጥ ላለው ሕይወት አክብሮት እንዳላት ካሳየች ሕሊናዋ ጥሩ እንዳደረገች ይመሠክርላታል። * ከሕሊናዋ ጋር የሚጋጭ ድርጊት ከፈጸመች ግን ሕሊናዋ ሊቆረቁራት አልፎ ተርፎም ሊወቅሳት ይችላል። (ሮም 2:14, 15) ደግሞም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፅንስ ያስወረዱ ሴቶች በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው።

ይሁንና እናትየዋ ልጁን ማሳደግ በጣም ከባድ እንደሆነ ቢሰማት ወይም እርግዝናው የመጣው ሳይፈለግ ቢሆንስ? አምላክ የእሱን መመሪያዎች በታማኝነት ለሚከተሉ ሰዎች የገባውን ቃል ተመልከት፦ “ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ፤ እንከን የለሽ ለሆነ ሰው እንከን የለሽ ትሆናለህ።” (መዝሙር 18:25) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም” በማለት ይናገራል።—መዝሙር 37:28

“ሕሊናቸው ከእነሱ ጋር ሆኖ በሚመሠክርበት ጊዜ ሐሳባቸው በውስጣቸው እየተሟገተ አንዴ ይከሳቸዋል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጥፋተኛ አይደላችሁም ይላቸዋል።”ሮም 2:15

ቀደም ሲል ፅንስ ያስወረዱ ሴቶችስ?

ሰዎች ምን ይላሉ?

ሩት የተባለች ነጠላ እናት እንዲህ ብላለች፦ “በወቅቱ ሦስት ልጆች ነበሩኝ፤ ሌላ አራተኛ ልጅ ማሳደግ የምችል አልመሰለኝም። ካስወረድኩ በኋላ ግን በጣም መጥፎ ነገር እንደፈጸምኩ ተሰማኝ።” * ታዲያ አምላክ ሩትን ይቅር አይላትም ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት እንዳለው ያሳያል፦ “እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም።” (ሉቃስ 5:32) የፈጸምነው ኃጢአት ከባድ ቢሆንም ለሠራነው ጥፋት ከልባችን እስከተጸጸትን እንዲሁም ንስሐ ገብተን አምላክ ይቅር እንዲለን እስከጠየቅን ድረስ አምላክ ይቅር ሊለን ፈቃደኛ ነው። (ኢሳይያስ 1:18) መዝሙር 51:17 “አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም” ይላል።

አንድ ሰው ከልቡ ከተጸጸተና በትሕትና ወደ አምላክ ከጸለየ አምላክ ንጹሕ ሕሊናና የአእምሮ ሰላም እንዲኖረው ይረዳዋል። ፊልጵስዩስ 4:6, 7 እንዲህ ይላል፦ “በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” * ሩት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷና የልቧን አውጥታ ለአምላክ መጸለይዋ እንዲህ ያለ ውስጣዊ ሰላም እንድታገኝ አስችሏታል። ‘በአምላክ ዘንድ በእርግጥ ይቅርታ እንዳለ’ ተገንዝባለች።—መዝሙር 130:4

“[አምላክ] እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ ለበደላችን የሚገባውንም ብድራት አልከፈለንም።”መዝሙር 103:10

^ አን.8 የእናትየዋ ወይም የልጁ ጤና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚለው ስጋት ፅንስ ለማስወረድ ተቀባይነት ያለው ምክንያት ሊሆን አይችልም። በወሊድ ወቅት ማትረፍ የሚቻለው የእናትየዋን ወይም የልጁን ሕይወት ብቻ ከሆነ ወላጆቹ የትኛውን እንደሚመርጡ መወሰን ይኖርባቸዋል። ሆኖም በአብዛኞቹ ያደጉ አገሮች ውስጥ በሕክምናው መስክ ከፍተኛ እድገት ስለተደረገ እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥመው ከስንት አንዴ ነው።

^ አን.12 ስሟ ተቀይሯል።

^ አን.14 የትንሣኤ ተስፋም አንድን ሰው ውስጣዊ ሰላም እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል። በእናቱ ማህፀን ሳለ የሞተ ፅንስ የመነሳት ተስፋ ሊኖረው እንደሚችል የሚጠቁሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን የያዘውን በሚያዝያ 15, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።