በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራስን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌን ተዋጋ

ራስን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌን ተዋጋ

2ኛው ቁልፍ

ራስን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌን ተዋጋ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ ምንነት ፈትኖ ያሳይ፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያነጻጽር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ የሚመካበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

ተፈታታኙ ሁኔታ ምንድን ነው? ሰዎች ስንባል ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ይቀናናል። ይህን የምናደርገው በተለያየ መንገድ ከእኛ ከሚያንሱ ሰዎች ጋር ሊሆን ይችላል፤ ብዙውን ጊዜ ግን ራሳችንን የምናወዳድረው በጉልበት፣ በሀብት ወይም በችሎታ ከእኛ ከሚበልጡ ሰዎች ጋር ነው። በሁለቱም አቅጣጫ ብንሄድ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም። ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድር ከሆነ የአንድ ሰው ዋጋማነት የሚለካው ባለው ወይም ማከናወን በቻለው ነገር ነው የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አዳብረናል ማለት ነው። በተጨማሪም ሰዎች ቅናት እንዲሰማቸውና የፉክክር መንፈስ እንዲያድርባቸው ልናደርግ እንችላለን።—መክብብ 4:4

ምን ማድረግ ትችላለህ? አምላክ አንተን በሚያይበት መንገድ ራስህን ለማየት ሞክር። የአምላክ አመለካከት ለራስህ በምትሰጠው ግምት ላይ ለውጥ እንዲያመጣ አድርግ። “ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ *፣” NW] ግን ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) ይሖዋ ዋጋማነትህን የሚለካው አንተን ከሌላ ሰው ጋር በማወዳደር ሳይሆን ልብህን በማንበብ እንዲሁም አስተሳሰብህን፣ ስሜትህንና ዝንባሌህን በመመርመር ነው። (ዕብራውያን 4:12, 13) ይሖዋ ያለብህን የአቅም ገደብ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ አንተም አቅምህን አውቀህ እንድትኖር ይፈልጋል። ዋጋማነትህን ለመለካት ራስህን ከሌሎች ጋር የምታወዳድር ከሆነ ትዕቢተኛ አሊያም ፈጽሞ የማይረካ ሰው ትሆናለህ። ስለዚህ በሁሉም ነገር የተዋጣልህ ሰው ልትሆን እንደማትችል በትሕትና አምነህ ተቀበል።—ምሳሌ 11:2

ታዲያ በአምላክ ዓይን ዋጋ እንዲኖርህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ነቢዩ ሚክያስ በአምላክ መንፈስ መሪነት “ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?” በማለት ጽፏል። (ሚክያስ 6:8) ይህን ምክር የምትከተል ከሆነ አምላክ ይንከባከብሃል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ባለን ረክተን ለመኖር የሚያነሳሳ ከዚህ የበለጠ ምክንያት ሊኖር ይችላል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ የአምላክ ስም ነው።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ዋጋማነታችንን የሚለካው ልባችን ውስጥ ባለው ነገር ነው