ሚክያስ 6:1-16

  • አምላክ ከእስራኤል ጋር ይሟገታል (1-5)

  • “ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?” (6-8)

    • ፍትሕ፣ ታማኝነት፣ ልክን ማወቅ (8)

  • የእስራኤል በደልና የደረሰበት ቅጣት (9-16)

6  ይሖዋ የሚለውን እባካችሁ ስሙ። ተነሱ፤ በተራሮች ፊት ሙግታችሁን አቅርቡ፤ኮረብቶችም ቃላችሁን ይስሙ።+   ተራሮች ሆይ፣ እናንተ ጽኑ የምድር መሠረቶች፣የይሖዋን ሙግት ስሙ፤+ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር ሙግት አለውና፤ከእስራኤልም ጋር ይከራከራል፦+   “ሕዝቤ ሆይ፣ ምን ያደረግኩህ ነገር አለ? ያደከምኩህስ ምን አድርጌ ነው?+ እስቲ መሥክርብኝ።   ከግብፅ ምድር አወጣሁህ፤+ከባርነትም ቤት ዋጀሁህ፤+ሙሴን፣ አሮንንና ሚርያምን+ በፊትህ ላክሁ።   ሕዝቤ ሆይ፣ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ያሴረብህን ነገር፣+የቢዖር ልጅ በለዓምም የሰጠውን መልስ+ እባክህ አስታውስ፤የይሖዋን የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድከሺቲም+ እስከ ጊልጋል+ ድረስ የሆነውን ነገር አስታውስ።”   በይሖዋ ፊት ምን ይዤ ልቅረብ? ከፍ ባለ ስፍራ በሚኖረው አምላክ ፊት ምን ይዤ ልስገድ? ሙሉ በሙሉ የሚቃጠሉ መባዎችናየአንድ ዓመት ጥጃዎች ይዤ ልቅረብ?+   ይሖዋ በሺህ በሚቆጠሩ አውራ በጎችወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋል?+ ለሠራሁት በደል የበኩር ወንድ ልጄን፣ለሠራሁትም* ኃጢአት የሆዴን ፍሬ ላቅርብ?+   ሰው ሆይ፣ መልካም የሆነውን ነግሮሃል። ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣*+ ታማኝነትን እንድትወድና*+ልክህን አውቀህ+ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!+   የይሖዋ ድምፅ ከተማዋን ይጣራል፤ጥበበኞች* ስምህን ይፈራሉ። የበትሩን ድምፅና ቅጣቱን የወሰነውን ስሙ።+ 10  ክፉ በሆነ ሰው ቤት፣ በክፋት የተገኘ ሀብትእንዲሁም አስጸያፊ የሆነ ጎዶሎ የኢፍ መስፈሪያ* አሁንም አለ? 11  አባይ ሚዛንና* የተዛቡ* የድንጋይ መለኪያዎች የያዘ ከረጢት+ እየተጠቀምኩንጹሕ ሥነ ምግባር ሊኖረኝ ይችላል?* 12  ባለጸጎቿ በግፍ የተሞሉ ናቸው፤ነዋሪዎቿም ውሸት ይናገራሉ፤+ምላሳቸው በአፋቸው ውስጥ አታላይ ነው።+ 13  “ስለዚህ መትቼ አቆስልሃለሁ፤+ከኃጢአትህ የተነሳ አጠፋሃለሁ። 14  ትበላለህ፤ ግን አትጠግብም፤ሆድህም ባዶ ይሆናል።+ የምትወስዳቸውን ነገሮች ጠብቀህ ማቆየት አትችልም፤ጠብቀህ ያቆየኸውንም ነገር ሁሉ ለሰይፍ አሳልፌ እሰጠዋለሁ። 15  ዘር ትዘራለህ፤ ሆኖም የምታጭደው ነገር አይኖርም። የወይራ ፍሬ ትጨምቃለህ፤ ሆኖም ዘይቱን አትጠቀምበትም፤ደግሞም አዲስ የወይን ጠጅ ትጨምቃለህ፤ ሆኖም የወይን ጠጅ አትጠጣም።+ 16  የኦምሪን ደንቦችና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ትከተላላችሁና፤+ምክራቸውንም ተከትላችሁ ትሄዳላችሁ። ስለዚህ አንተን መቀጣጫ፣ነዋሪዎቿንም ማፏጫ አደርጋለሁ፤+የሰዎችንም ፌዝ ትሸከማላችሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍሴ ለሠራችውም።”
ወይም “ደግነትና ታማኝነት የሚንጸባረቅበት ፍቅር እንድታሳይና።” ቃል በቃል “ታማኝ ፍቅርን እንድትወድና።”
ወይም “ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ።”
ወይም “ማስተዋል የታከለበት ጥበብ ያላቸው።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቅን ልሆን እችላለሁ?”
ወይም “ለማጭበርበር የሚያገለግሉ።”
ወይም “ሐሰተኛ ሚዛንና፤ ትክክል ያልሆነ ሚዛንና።”