በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈሳዊ ፍላጎትህን አርካ

መንፈሳዊ ፍላጎትህን አርካ

5ኛው ቁልፍ

መንፈሳዊ ፍላጎትህን አርካ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3

ተፈታታኙ ሁኔታ ምንድን ነው? በዓለም ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች አሉ፤ ይሁንና ብዙዎቹ መንፈሳዊ ፍላጎትን ማርካት ስለሚቻልበት መንገድ የሚያስተምሩት ትምህርት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። ታዲያ እውነቱን የሚያስተምረውና በእርግጥ አምላክን የሚያስደስተው ሃይማኖት የትኛው እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? አንዳንድ የታወቁ ደራሲዎች በአምላክ ማመንም ሆነ ለእሱ ያደሩ መሆን ከምክንያታዊ አስተሳሰብ የራቀ አልፎ ተርፎም ጎጂ እንደሆነ ይናገራሉ። ማክሊንስ የተባለ መጽሔት አምላክ የለሽ የሆኑ አንድ ታዋቂ ሰው የሰጡትን አስተያየት እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “ሳይንስ ያልደረሰበትና በስሜት ሕዋሳቶቻችን አማካኝነት ልናውቀው ከምንችለው በላይ የሆነ አንድ ነገር አለ የሚለው የክርስትና አስተሳሰብ አሁን ያለችንን ሕይወት እንዳንጠቀምባት የሚያደርገን ከመሆኑም ሌላ እርስ በርስ እንድንጋጭ ምክንያት ይሆናል።”

ምን ማድረግ ትችላለህ? አምላክ መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን መርምር። (ሮም 1:20፤ ዕብራውያን 3:4) ‘የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? መከራ የበዛው ለምንድን ነው? እንዲሁም አምላክ ከእኔ የሚፈልገው ምንድን ነው?’ እንደሚሉት ላሉ አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከምታደርገው ጥረት ማንም እንዳያደናቅፍህ ተጠንቀቅ። ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘትህ ምንጊዜም ባለህ ረክተህ እንድትኖር የሚያስችልህ ወሳኝ ነገር ነው።

ይህ ሲባል ግን ሰዎች የሚነግሩህን ነገር ሁሉ በጭፍን መቀበል አለብህ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማሰብ ችሎታህን’ ተጠቅመህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምን እንደሆነ መርምረህ እንድታረጋግጥ ያበረታታሃል። (ሮም 12:1, 2) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ጥረትህ መልሶ ይክስሃል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ ብትመድብና ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ምክሮቹን በሥራ ላይ ብታውል ችግሮችን ማስወገድ፣ ጭንቀትን መቀነስ እንዲሁም ከሕይወት የምታገኘውን ደስታ መጨመር ትችላለህ። ይህ ተስፋ የማይጨበጥ አይደለም። ከሁሉም ዓይነት ዘርና የኑሮ ደረጃ የመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን በመማራቸው ተጠቅመዋል። ለምሳሌ በዚህ መጽሔት ከገጽ 18 እስከ 21 ላይ የቀረቡትን እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች ማንበብ ትችላለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግህ የምታገኘው ጥቅም ለአምላክ የማደር ፍላጎትህ እንዲጨምር ያደርጋል። በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና እናበረታታሃለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል” በማለት ጽፏል፤ አንተም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ማረጋገጥ ትችላለህ።—1 ጢሞቴዎስ 6:6

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምን እንደሆነ መርምረህ አረጋግጥ