በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እስከ ምድር ዳር ድረስ መጓዝ

እስከ ምድር ዳር ድረስ መጓዝ

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሕይወት

እስከ ምድር ዳር ድረስ መጓዝ

“በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ። በዚያች ከተማ ምሥራቹን ሰብከው በርካታ ደቀ መዛሙርት ካፈሩ በኋላ ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ።”—የሐዋርያት ሥራ 14:20, 21

መንገደኛው ቀዝቃዛውን የማለዳ አየር እየሳበ ጉዞውን ተያይዞታል። እግሮቹ የዛሉ ቢሆንም ያረጁ ጫማዎቹን ተጫምቶ ሙሉ ቀን የሚፈጀውን የእግር ጉዞ ጀመረው።

የማለዳዋን ጀንበር እየሞቀ የወይን እርሻዎችንና የወይራ ዛፎችን አልፎ አቧራማውን መንገድ በመከተል አቀበቱን ተያያዘው። በመንገዱ ላይ ወደ ማሳቸው የሚጓዙ ገበሬዎች፣ ሸቀጦቻቸውን በእንስሳት ላይ ጭነው የሚያዘግሙ ነጋዴዎች እንዲሁም ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዙ ሰዎችና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች መንገደኞች ያጋጥሙታል። መንገደኛውና ጓደኞቹ በጉዟቸው ላይ የሚያገኙትን ማንኛውንም ሰው ያነጋግራሉ። ዓላማቸው ምንድን ነው? ኢየሱስ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ስለ እሱ እንዲመሠክሩ የሰጣቸውን ተልእኮ መፈጸም ነው።—የሐዋርያት ሥራ 1:8

ይህ መንገደኛ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በርናባስ ወይም ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ብርቱ ሚስዮናውያን መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 14:19-26፤ 15:22) እነዚህ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ነገር ተቋቁመው ዓላማቸውን ለማሳካት የቆረጡ ናቸው። በወቅቱ ጉዞ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በባሕር ላይ ሲጓዝ ያጋጠመውን ችግር ሲገልጽ “ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞኛል፣ አንድ ሌሊትና አንድ ቀን በጥልቅ ባሕር ውስጥ ውዬ አድሬያለሁ” በማለት ጽፏል። በየብስ የሚደረገው ጉዞም ቢሆን ቀላል አልነበረም። ጳውሎስ “በወንዝ ሙላት ለሚመጣ አደጋ” እንዲሁም “ወንበዴዎች ለሚያደርሱት አደጋ” ብዙ ጊዜ ይጋለጥ እንደነበር ተናግሯል።—2 ቆሮንቶስ 11:25-27

ከእነዚህ ሚስዮናውያን ጋር መጓዝ ምን ይመስል ነበር? ከእነሱ ጋር ብትሆን በቀን ውስጥ ምን ያህል ርቀት የምትጓዝ ይመስልሃል? ለጉዞ የሚያስፈልጉ ምን ነገሮችን መያዝ ይኖርብሃል? በጉዞህ ላይ የት ማረፍ ትችላለህ?

በየብስ ላይ መጓዝ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሮማውያን በግዛታቸው ውስጥ ያሉ ዋና ዋና ቦታዎችን የሚያገናኙ ሰፊ ርቀት የሚሸፍኑ መንገዶችን ዘርግተው ነበር። እነዚህ መንገዶች በጥንቃቄ የተነደፉና በደንብ የተሠሩ ነበሩ። አብዛኞቹ መንገዶች ስፋታቸው 4.5 ሜትር ሲሆን ድንጋይ የተነጠፈባቸው ነበሩ፤ በመንገዱ ዳርና ዳር ጠርዝ ይሠራላቸው እንዲሁም ርቀት ጠቋሚ ምልክቶች ይደረግላቸው ነበር። እንደነዚህ ባሉ መንገዶች ላይ ጳውሎስን የመሰሉ ሚስዮናውያን በቀን ውስጥ እስከ 32 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት በእግራቸው ሊሸፍኑ ይችላሉ።

በፓለስቲና ግን አብዛኞቹ መንገዶች ጥርጊያ ሲሆኑ በማሳዎችም ሆነ በገደሎች ዙሪያ አጥር አልነበረም፤ እነዚህ መንገዶች ለአደጋ የሚያጋልጡ ነበሩ። አንድ መንገደኛ በጉዞው ላይ አራዊት ወይም ዘራፊዎች ሊያጋጥሙት ሌላው ቀርቶ በመሬት መንሸራተት ምክንያት መንገዶቹ ሊዘጉ ይችላሉ።

መንገደኛው ምን ነገሮችን ይይዛል? መሠረታዊ ከሆኑት ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ራሱን ለመከላከል የሚያገለግለው በትር (1)፣ ተጠቅልሎ የሚያዝ መኝታ (2)፣ የገንዘብ ከረጢት (3)፣ ተለዋጭ ጫማ (4)፣ የምግብ መያዣ ከረጢት (5)፣ ቅያሪ ልብስ (6)፣ በጉዞ ላይ ከጉድጓድ ውኃ የሚቀዳበት ከለፋ ቆዳ የተሠራ ውኃ መቅጃ (7)፣ የውኃ አቁማዳ (8) እንዲሁም ሌሎች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሰብስቦ ለመያዝ የሚጠቀምበት ትልቅ የቆዳ ቦርሳ (9)

ሚስዮናውያኑ፣ ሸቀጦችን በአቅራቢያቸው ላሉ ገበያዎች የሚያቀርቡ ተጓዥ ነጋዴዎች በጉዟቸው ላይ እንደሚያጋጥሟቸው የታወቀ ነው። እነዚህ ነጋዴዎች ዕቃቸውን የሚያጓጉዙት በአስቸጋሪ መንገዶች ላይ ሳይደናቀፉ ወይም ሳይንሸራተቱ መሄድ በሚችሉት አህዮች ነበር። አቀበታማና ድንጋያማ በሆኑ መንገዶች ላይ ያለ ችግር በመጓዝ ረገድ አህዮችን የሚተካከላቸው የለም። ጠንካራ የሆነ አህያ በደንብ ተጭኖ በቀን እስከ 80 ኪሎ ሜትር ሊጓዝ ይችላል። በበሬ የሚጎተቱ ጋሪዎች ፍጥነት የሌላቸው ሲሆኑ በቀን መጓዝ የሚችሉት ከ8 እስከ 20 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ይሁንና በሬዎች ከባድ ጭነቶችን መሸከም የሚችሉ ከመሆኑም ሌላ ለአጭር ርቀት ተመራጭ ናቸው። አንድ መንገደኛ፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰበሰቡ ሸቀጦችን የጫኑ የአህዮች መንጋ ወይም የግመሎች ቅፍለት በጉዞው ላይ ሊያጋጥመው ይችላል። ከቤተ መንግሥት የሚወጡ አዋጆችንና መልእክቶችን ሩቅ ለሚገኙ የሮም ግዛቶች የሚያደርስ ፈረሰኛ በፍጥነት ሲያልፍ ሊመለከትም ይችላል።

ምሽት ላይ መንገደኞቹ ከመንገዱ ወጣ ብለው እንደነገሩ ባበጃጇቸው ዳሶች ውስጥ ሌሊቱን ያሳልፋሉ። አንዳንዶች ደግሞ የእንስሶቻቸውን ጭነት ማራገፍ የሚችሉበት ቦታና እነሱ ራሳቸው የሚያርፉባቸው ባዶ ክፍሎች ባሏቸው ግቢዎች ውስጥ ያድራሉ። ንጽሕና የጎደላቸውና ብዙም ደስ የማይሉት እነዚህ ማረፊያዎች ከብርድም ይሁን ከሌባ ያን ያህል አያስጥሉም። ከቦታ ቦታ የሚጓዙት ሚስዮናውያን በተቻለ መጠን ዘመዶቻቸው ወይም የእምነት ባልንጀሮቻቸው ዘንድ ያርፉ የነበረ ይመስላል።—የሐዋርያት ሥራ 17:7፤ ሮም 12:13

በባሕር ላይ መጓዝ፦ ትንንሽ ጀልባዎች፣ በውኃ ዳርቻዎች ላይ እንዲሁም የገሊላን ባሕር በማቋረጥ ሰዎችንና ሸቀጣ ሸቀጦችን ለማጓጓዝ ያገለግሉ ነበር። (ዮሐንስ 6:1, 2, 16, 17, 22-24) ትልልቅ መርከቦች ደግሞ የሜድትራንያንን ባሕር በማቋረጥ ርቀው ወደሚገኙ ወደቦች ጭነት ያመላልሳሉ። እነዚህ መርከቦች ለሮም ነዋሪዎች ምግብ የሚያመጡ ሲሆን የመንግሥት ባለሥልጣናትንና የጽሑፍ መልእክቶችን ከአንዱ ወደብ ወደ ሌላው ያመላልሱ ነበር።

መርከበኞች የጉዞ አቅጣጫቸውን የሚያውቁት ቀን ቀን ጎልተው የሚታዩ ምልክቶችን፣ ምሽት ላይ ደግሞ ከዋክብትን በመመልከት ነበር። በዚህ ምክንያት የባሕር ላይ ጉዞ በአንጻራዊ ሁኔታ አስተማማኝ የሚሆነው አየሩ ጥሩ በሚሆንባቸው ከግንቦት እስከ መስከረም አጋማሽ ባሉት ወራት ውስጥ ነበር። የመርከብ መሰበር አደጋ በተደጋጋሚ ያጋጥም ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 27:39-44፤ 2 ቆሮንቶስ 11:25

ሰዎች የባሕር ላይ ጉዞን የሚመርጡት ከየብስ ጉዞ ይልቅ ምቹ በመሆኑ አልነበረም። ዋነኛው የባሕር ላይ መጓጓዣ የጭነት መርከብ ሲሆን በእነዚህ መጓጓዣዎች ላይ ለተሳፋሪዎች ምቾት እምብዛም ትኩረት አይሰጥም። መንገደኞች በማንኛውም የአየር ሁኔታ ውሏቸውም ሆነ አዳራቸው በመርከቡ መድረክ ላይ ነበር። ከመድረኩ በታች ያለው ውኃ የማይገባበት ቦታ ውድ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች ይቀመጡበታል። መንገደኞቹ የሚመገቡት ራሳቸው የያዙትን ምግብ ሲሆን መርከቡ ላይ የሚቀርበው የመጠጥ ውኃ ብቻ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የአየሩ ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ጋብ የማይለው ኃይለኛ ማዕበል ተሳፋሪዎቹን ያንገላታቸው ስለነበር ብዙውን ጊዜ በጉዞ ላይ የሚያጋጥሙ እንደ ማጥወልወል ያሉ ሕመሞች ለቀናት ያስቸግሯቸው ነበር።

እንደ ጳውሎስ ያሉ ሚስዮናውያን፣ በየብስና በባሕር ላይ የሚደረገው ጉዞ አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም እንኳ “የመንግሥቱ ምሥራች” በዘመኑ በሚታወቁት የዓለም ክፍሎች በስፋት እንዲሰራጭ አድርገዋል። (ማቴዎስ 24:14) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለ እሱ እንዲመሠክሩ ከነገራቸው ከ30 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ጳውሎስ የመንግሥቱ ምሥራች “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል” እንደተሰበከ መጻፍ ችሏል።—ቆላስይስ 1:23