በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

አመለካከት ለውጥ ያመጣል!

አመለካከት ለውጥ ያመጣል!

ከሚከተሉት ውስጥ ለደስታህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የትኛው ይመስልሃል?

 • ያለህበት ሁኔታ

 • በዘር የወረስከው ነገር

 • አመለካከትህ

አንዳንዶች “ያለህበት ሁኔታ” የሚለውን ይመርጡ ይሆናል፤ ከዚያም . . .

 • “ብዙ ገንዘብ ቢኖረኝ ኖሮ . . .

 • “አስደሳች ትዳር ቢኖረኝ ኖሮ . . .

 • “ጥሩ ጤንነት ቢኖረኝ ኖሮ . . . ደስተኛ እሆን ነበር” ይላሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አብዛኛውን ጊዜ ከደስታ ጋር በተያያዘ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ያለንበት ሁኔታ ወይም በዘር የወረስነው ነገር ሳይሆን አመለካከታችን ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ሊያስደስተን ይገባል። ለምን? ምክንያቱም በሁኔታህና በዘር በወረስከው ነገር ላይ ያን ያህል ለውጥ ማድረግ አትችልም፤ አመለካከትህን ግን መቆጣጠር ትችላለህ።

“ጥሩ መድኃኒት”

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው፤ የተደቆሰ መንፈስ ግን ኃይል ያሟጥጣል” ይላል። (ምሳሌ 17:22) በእርግጥም አመለካከትህ ለውጥ ያመጣል! ይህም ግብህ ላይ መድረስ እንድትችል አሊያም ተስፋ ቆርጠህ እንድትተወው ያደርግህ ይሆናል። ወይም ደግሞ የደረሰብህ አንድ አሳዛኝ ክስተት ጥንካሬህ አሊያም ድክመትህ አፍጥጦ እንዲወጣ ያደርጋል።

አንዳንድ ሰዎች ይህ ሐሳብ አይዋጥላቸው ይሆናል። እንዲህ ሊሉ ይችላሉ፦

 • ‘ደስተኛ መስዬ በመታየት ችግሬን ምን አስደበቀኝ?’

 • ‘የፈለገውን ያህል ቀና አመለካከት ቢኖረኝ ያለሁበት ሁኔታ አይቀየር።’

 • ‘በቁሜ ከምቃዥ ሐቁን ተቀብዬ ብኖር ይሻለኛል።’

እነዚህ ሐሳቦች እውነታ ያላቸው ይመስሉ ይሆናል። ያም ሆኖ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ብዙ ጠቃሚ ጎኖች አሉት። እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ሁኔታዎች አስብባቸው።

አሌክስ እና ብራየን በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ በተለያየ ፕሮጀክት ላይ ተመድበው ሥራቸውን በትጋት ያከናውናሉ። አለቃቸው ሥራቸውን ከገመገመ በኋላ በሁለቱም ፕሮጀክቶች ላይ ያለውን የጎላ ድክመት ጠቀሰ።

 • አሌክስ፦ “ይህ ፕሮጀክት እንዲሳካ ብዙ ጊዜና ጉልበት ባፈስስም አልተሳካልኝም። በዚህ ሥራ መቼም ስኬታማ የምሆን አይመስለኝም። ምንም ያህል ብለፋ ጉድለት አያጣውም። ታዲያ ምን አደከመኝ?”

 • ብራየን፦ “አለቃዬ የሥራዬን መልካም ጎኖች ነግሮኛል፤ ይሁንና አንዳንድ ከባድ ስህተቶችን ሠርቻለሁ። ለሚቀጥለው የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለኝን ልምድ አግኝቼበታለሁ።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል?

 • ከስድስት ወር በኋላ ሥራውን ለማከናወን የተሻለ ብቃት የሚኖረው ማን ነው? አሌክስ ወይስ ብራየን?

 • አሠሪ ብትሆን ኖሮ የምትቀጥረው ወይም በድርጅትህ ውስጥ እንዲቀጥል የምትፈልገው ማንን ነው?

 • አንተስ ያሰብከው ነገር ሳይሳካ ቢቀር የምትሰጠው ምላሽ እንደ አሌክስ ነው ወይስ እንደ ብራየን?

አንድሬያ እና ብሪትኒ ከብቸኝነት ስሜት ጋር ይታገላሉ። ሁለቱም ይህን ችግር ለመቋቋም የተለያየ ዘዴ ይጠቀማሉ።

 • አንድሬያ በዋነኝነት ትኩረት የምታደርገው በራሷ ላይ ነው። ለሰዎች አንድ ነገር የምታደርገው እነሱ ቀድመው የሆነ ነገር ካደረጉላት ብቻ ነው። ‘ውለታ ለማይመልሱልኝ ሰዎች ጊዜዬን የማባክንበት ምን ምክንያት አለ?’ የሚል አስተሳሰብ አላት።

 • ብሪትኒ ሰዎች ያደረገችላቸውን ነገር ባያደንቁም እንኳ ለሰዎች ደግነት ለማሳየትና መልካም ነገር ለማድረግ ከልቧ ትጥራለች። የምትመራው ‘ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም አድርጉላቸው’ በሚለው ወርቃማ ሕግ ነው። (ሉቃስ 6:31) ብሪትኒ መልካም ማድረግ በራሱ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማታል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል?

 • ከሁለቱ ሴቶች መካከል ለጓደኝነት የትኛዋ ትሻላለች?

 • ከጓደኞቿ ጋር ባላት ግንኙነት ይበልጥ ደስተኛ የምትሆነው የትኛዋ ነች?

 • አንተስ ከብቸኝነት ስሜት ጋር እየታገልክ ከሆነ ሁኔታውን የምትይዘው እንደ አንድሬያ ነው ወይስ እንደ ብሪትኒ?

እንደ ብራየንና ብሪትኒ ያሉ ሰዎች ታውቅ ይሆናል። እንዲያውም አንተ ራስህ እንደ እነሱ እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል። ከሆነ አመለካከትህ በሕይወትህ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ መገንዘብህ አይቀርም። በሌላ በኩል ግን እንደ አሌክስ ወይም እንደ አንድሬያ ዓይነት ሰው ከሆንክስ? መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ውጣ ውረዶች ይበልጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ እንድትወጣ ሊረዱህ የሚችሉ ሦስት መንገዶችን ይገልጻል።

1 አፍራሽ አመለካከትን አስወግድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል።”—ምሳሌ 24:10

ይህ ምን ማለት ነው? አፍራሽ አመለካከት፣ ያለህበት ሁኔታ እንዲሻሻል ለማድረግ ወይም ሁኔታውን ለመወጣት የሚያስችልህ ኃይል እንዲሟጠጥ ያደርግብሃል።

ምሳሌ፦ ዩሊሳ ያሳለፈችው የልጅነት ሕይወት አሳዛኝ ነው። አባቷ የመጠጥ ሱሰኛ ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቦቿ ድሆች ነበሩ። ብዙ ጊዜ የመኖሪያ ቦታ ቀያይረዋል። መጀመሪያ አካባቢ ዩሊሳ በሕይወቷ ውስጥ ባጋጠሟት ነገሮች የተነሳ አሉታዊ አመለካከት አዳብራ ነበር። ሆኖም ይህን አመለካከቷን መለወጥ ችላለች። እንዲህ እንድታደርግ የረዳት ምንድን ነው? ዩሊሳ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ያሉባቸውን ችግሮች ከማሸነፋቸው በፊት እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ አመለካከቴን እንዳስተካክል ረድቶኛል። ዛሬም ድረስ አፍራሽ የሆነ አመለካከት እንዳይጠናወተኝ የረዳኝ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሰዎች ደስ የማይለኝን ባሕርይ ሲያሳዩ እንዲህ እንዲሆኑ ምክንያት የሆነውን ነገር ለመረዳት ጥረት አደርጋለሁ።”

ዩሊሳ ማስተዋል እንደቻለችው መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን ይዟል። በውስጡ የያዘው ምክር የሚያጋጥሙህን መጥፎ ሁኔታዎች መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤፌሶን 4:23 “አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ” ይላል።

ይህ ጥቅስ እንደሚያመለክተው አመለካከት ድንጋይ ላይ እንደተቀረጸ ጽሑፍ አይደለም፤ ሊቀየር ይችላል። አስተሳሰብህ ‘ሊታደስ’ ይችላል። እንዲያውም ይህ ዓይነቱ ለውጥ ቀጣይ ነው። ጥቅሱ “እየታደሰ ይሂድ” የሚለው ለዚህ ነው።

2 አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ አተኩር

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ጎስቋላ ሰው ዘመኑ ሁሉ አስከፊ ነው፤ ደስተኛ ልብ ያለው ሰው ግን ሁልጊዜ ግብዣ ላይ ያለ ያህል ነው።”—ምሳሌ 15:15

ይህ ምን ማለት ነው? ለሁሉም ነገር አሉታዊ አመለካከት ካለህ “ጎስቋላ” ትሆናለህ፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ቀን “አስከፊ” ወይም ጨለማ ይሆንብሃል። አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ የምታተኩር ከሆነ ግን “ደስተኛ ልብ” ይኖርሃል። ምርጫው ለአንተ የተተወ ነው።

ምሳሌ፦ ያንግኮ፣ በአንጎሉ ውስጥ ያለውን ዕጢ ለማስወገድ በርካታ ቀዶ ጥገናዎች ከተደረጉለት በኋላ እንደ ልቡ መንቀሳቀስና መናገር ተሳነው። ይህ ሁኔታ ግቦቹ ላይ ከመድረስ እንደሚያግደው ስለተሰማው ለብዙ ዓመታት በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዋጠ። በኋላ ላይ ግን አመለካከቱን መቀየር ችሏል። እንዴት? “ባሉብኝ የአቅም ገደቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ አበረታች በሆኑ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ጀመርኩ” ብሏል።

ያንግኮ ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ማድረጌ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳኛል። የረጅም ጊዜ ግቦቼን ሙሉ በሙሉ አልተውኳቸውም፤ ሆኖም አሁን ትኩረት የማደርገው ልደርስባቸው በምችላቸው የአጭር ጊዜ ግቦች ላይ ነው። ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ወደ አእምሮዬ ሲመጡ ለደስታዬ ምክንያት በሚሆኑ በርካታ ነገሮች ላይ አሰላስላለሁ።”

እንደ ያንግኮ ሁሉ አንተም አፍራሽ አመለካከቶችን አስወግደህ በአዎንታዊ አመለካከት ልትተካቸው ትችላለህ። ያንግኮ እንዳጋጠመው ከጤና ችግር ጋር አሊያም ከሌሎች መጥፎ ሁኔታዎች ጋር እየታገልክ ከሆነ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ያለሁበት ሁኔታ ምንም ተስፋ የለውም? ያጋጠመኝ የማልወጣው ችግር ነው? ወይስ ላልፈው የምችል መሰናክል?’ አበረታች በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ አሉታዊ አስተሳሰብን ለማስወገድ ጥረት አድርግ።

3 ለሌሎች መልካም አድርግ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ይህ ምን ማለት ነው? ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት መስጠት ጥልቅ እርካታ ያስገኛል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የተፈጠርነው ከራሳችን አልፈን ስለ ሌሎች ፍላጎትም እንድናስብ ተደርገን ስለሆነ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4፤ 1 ዮሐንስ 4:11) በመስጠት የሚገኘው ደስታ፣ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት ይረዳናል።

ምሳሌ፦ ሆስዋ፣ ስፓይና ቢፊዳ የተባለ ከባድ የአከርካሪ በሽታ አለበት። ይህ በሽታ ብዙውን ጊዜ ከባድ ሥቃይ ያስከትልበታል። ይሁንና ሆስዋ ሌሎችን መርዳቱ አርኪ የሆነ ሕይወት እንዲመራ አስችሎታል። እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ነገር ለማድረግ ሳስብ ‘ከአቅሜ በላይ ነው’ ከማለት ይልቅ ሌሎችን መርዳት የምችልበትን መንገድ እፈልጋለሁ። ለሌሎች መልካም ነገር ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ፤ ይህ ደግሞ ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል።”

ምን ማድረግ ትችላለህ?

የራስህን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፈልግ። ለምሳሌ ለታመመ ጎረቤትህ ምግብ ማዘጋጀት ትችላለህ? በቤት ውስጥ ሥራ እገዛ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያን ታውቃለህ?

አንድን የአትክልት ቦታ ለመንከባከብ ጥረት እንደምታደርግ ሁሉ ጥሩ አመለካከት ለመያዝም ጥረት አድርግ። መርዘኛ አረም የሆኑትን አሉታዊና አፍራሽ አመለካከቶችን ከሥራቸው ነቅለህ ጣል። በእውነታ ላይ የተመሠረተ የአዎንታዊ አመለካከት ዘር ዝራ፤ እንዲሁም ጥሩ ስሜት እንዲኖርህ የሚያደርጉ ሥራዎችን በመሥራት ዘሩ ላይ ማዳበሪያ ጨምርበት ። በዚህ መንገድ ሕይወትህ ይበልጥ አርኪ እንዲሆን በማድረግ መልካም ፍሬ ማጨድ ትችላለህ። ይህ ደግሞ አመለካከት ለውጥ ያመጣል የሚለውን ሐቅ ያጠናክራል።

አንዳንድ ሰዎች ለጤንነታችው ሲሉ የተወሰኑ ምግቦችን ከመመገብ እንደሚቆጠቡ ሁሉ አሉታዊ አመለካከቶችን ላለማስተናገድም ጥረት ማድረግ ትችላለህ