በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እምነት ጨምርልን”

“እምነት ጨምርልን”

“እምነቴ እንዲጠነክር . . . እርዳኝ!”—ማር. 9:24

መዝሙሮች፦ 81, 135

1. እምነት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

‘ከታላቁ መከራ በሕይወት ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም እንዲገቡ ይሖዋ ከሚፈቅድላቸው ሰዎች መካከል እገኝ ይሆን?’ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ? እርግጥ ነው፣ ለመዳን የተለያዩ ባሕርያትን ማዳበር ያስፈልጋል፤ ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አንድ መሥፈርት ሲገልጽ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” ብሏል። (ዕብ. 11:6) ይህ ቀላል ነገር ሊመስል ይችላል፤ ሐቁ ግን “እምነት ሁሉም ሰው የሚኖረው ነገር አይደለም።” (2 ተሰ. 3:2) እነዚህ ጥቅሶች ጠንካራ እምነት ማዳበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዱናል።

2, 3. (ሀ) የእምነትን አስፈላጊነት በተመለከተ ጴጥሮስ ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ግርማንና ክብርን” ለማግኘት “ተፈትኖ የተረጋገጠ” እምነት እንደሚያስፈልግ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 1:7ን አንብብ።) ታላቁ መከራ በፍጥነት እየቀረበ በመሆኑ ክብር የተጎናጸፈው ንጉሣችን በሚገለጥበት ጊዜ በእምነታቸው የተነሳ ከሚያመሰግናቸው ሰዎች መካከል መሆን እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። በእርግጥም፣ “በሕይወት የሚያኖር እምነት” ማዳበር እንፈልጋለን። (ዕብ. 10:39) ይህን ግብ በአእምሯችን በመያዝ “እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ሲል የተማጸነው ሰው ያቀረበው ዓይነት ልመና ማቅረብ እንችላለን። (ማር. 9:24) አሊያም “እምነት ጨምርልን” እንዳሉት የኢየሱስ ሐዋርያት ለማለት እንገፋፋ ይሆናል።—ሉቃስ 17:5

3 ተጨማሪ እምነት ከማስፈለጉ ጋር በተያያዘ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ። ይህን ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? እምነት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እምነት እንዲጨመርልን የምናቀርበው ልመና ምላሽ እንደሚያገኝ ምን ማረጋገጫ አለን?

አምላክን የሚያስደስት እምነት መገንባት

4. እምነታችንን ለማጠናከር የእነማንን ምሳሌ ማየታችን ይጠቅመናል?

4 “ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” ስለተጻፈ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት በርካታ የእምነት ምሳሌዎች ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሮም 15:4) እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ ረዓብ፣ ጌድዮንና ባርቅ ስለመሳሰሉት ሰዎች ስናነብ የሕይወት ታሪካቸው የራሳችንን እምነት እንድንመረምር ይገፋፋን ይሆናል። (ዕብ. 11:32-35) በተጨማሪም በዘመናችን የላቀ እምነት ስላሳዩ ወንድሞችና እህቶች ታሪክ፣ ማንበባችን እምነታችንን ለማጠናከር ትጋት የተሞላበት ጥረት እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል። *

5. ኤልያስ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? እሱ የተወው ምሳሌስ ስለየትኛው ነገር እንድናስብ ያደርገናል?

5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሰዎች መካከል ነቢዩ ኤልያስ አንድ ምሳሌ ነው። በይሖዋ ላይ ያለውን ከፍተኛ እምነት የሚያሳዩትን ቀጥሎ የቀረቡ ሁኔታዎች ተመልከት። ኤልያስ፣ ይሖዋ ድርቅ ሊያመጣ እንደሆነ ለንጉሥ አክዓብ ሲያሳውቀው “ሕያው በሆነው . . . በይሖዋ እምላለሁ፣ በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር . . . ጠል ወይም ዝናብ አይኖርም!” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል። (1 ነገ. 17:1) ኤልያስ በድርቁ ወቅት ይሖዋ ለእሱም ሆነ ለሌሎች የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያቀርብላቸው እምነት ነበረው። (1 ነገ. 17:4, 5, 13, 14) ኤልያስ፣ ይሖዋ ሞቶ የነበረውን ልጅ ሊያስነሳው እንደሚችልም ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። (1 ነገ. 17:21) በተጨማሪም በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ያቀረበውን መሥዋዕት ይሖዋ እሳት ልኮ እንዲበላው እንደሚያደርግ ፈጽሞ አልተጠራጠረም። (1 ነገ. 18:24, 37) ይሖዋ የድርቁ ወቅት እንዲያበቃ የሚያደርግበት ጊዜ ሲደርስ ዝናብ እንደሚመጣ የሚያሳይ ምንም ምልክት ከመታየቱ በፊት እንኳ ኤልያስ አክዓብን “የከባድ ዝናብ ድምፅ እያጉረመረመ ስለሆነ ሂድ ብላ፤ ጠጣም” ብሎታል። (1 ነገ. 18:41) እነዚህ ዘገባዎች እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት እንዳለንና እንደሌለን ራሳችንን እንድንመረምር አያደርጉንም?

እምነታችንን ለመገንባት ምን ማድረግ እንችላለን?

6. እምነታችንን ለመገንባት ከይሖዋ ምን ማግኘት ያስፈልገናል?

6 በራሳችን ጥረት ብቻ እምነት ማዳበር አንችልም። እምነት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ አንድ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:22) በመሆኑም ኢየሱስ ተጨማሪ መንፈስ ለማግኘት እንድንጸልይ የሰጠውን ምክር መስማታችን ጥበብ ነው፤ ምክንያቱም አብ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” እንደሚሰጥ ኢየሱስ በእርግጠኝነት ነግሮናል።—ሉቃስ 11:13

7. እምነታችን ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

7 እምነታችንን ከገነባን በኋላ ጠብቀን ለማቆየት ቀጣይ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እምነታችን ከሚነድ እሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እሳት ስናቀጣጥል መጀመሪያ ላይ ቦግ ብሎ ሊነድ ይችላል። ይሁን እንጂ ዝም ብለን ከተውነው እሳቱ ከስሞ ፍም ብቻ ይቀራል፤ ቀስ በቀስ ደግሞ ሙቀት የሌለው አመድ ይሆናል። ይሁንና በየጊዜው እሳቱ ውስጥ እንጨት የምንጨምር ከሆነ መቀጣጠሉን ይቀጥላል። በተመሳሳይም የአምላክን ቃል አዘውትረን የምንመገብ ከሆነ እምነታችን ሕያው ሆኖ ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስን በቀጣይነት በማጥናት ለቃሉና ለቃሉ ባለቤት ጥልቅ ፍቅር ማዳበር እንችላለን፤ ይህ ደግሞ እምነታችን እያደገ እንዲሄድ የሚያስችል መሠረት ይሆነናል።

8. እምነታችንን ለመገንባትና ጠብቀን ለማቆየት የሚረዳን ነገር ምንድን ነው?

8 ጠንካራ እምነት ለመገንባትና ጠብቀህ ለማቆየት ማድረግ የምትችለው ሌላው ነገር ምንድን ነው? እስክትጠመቅ ድረስ ባገኘኸው እውቀት ረክተህ አትኑር። (ዕብ. 6:1, 2) ፍጻሜያቸውን ስላገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መማርህን ቀጥል፤ ምክንያቱም እነዚህ ትንቢቶች እምነትህን እንድትገነባ የሚያስችሉ በቂ ማስረጃዎች እንድታገኝ ያደርጉሃል። ከዚህ በተጨማሪ ጠንካራ እምነት ካላቸው ሰዎች መካከል የሚያስቆጥረን እምነት ያለህ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የአምላክን ቃል እንደ መለኪያ አድርገህ መጠቀም ትችላለህ።—ያዕቆብ 1:25ን እና 2:24, 26ን አንብብ።

9, 10. (ሀ) ጥሩ ባልንጀርነት፣ (ለ) የጉባኤ ስብሰባ፣ (ሐ) የመስክ አገልግሎት ጠንካራ እምነት እንድንገነባ የሚረዳን እንዴት ነው?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ‘እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንበረታታ’ ብሏቸው ነበር። (ሮም 1:12) ከእምነት ባልንጀሮቻችን፣ በተለይ ደግሞ “ተፈትኖ የተረጋገጠ” እምነት እንዳላቸው ካሳዩ ወንድሞቻችን ጋር ስንሆን አንዳችን የሌላውን እምነት መገንባት እንችላለን። (ያዕ. 1:3) መጥፎ ባልንጀርነት እምነት ያጠፋል፤ በአንጻሩ ግን ጥሩ ባልንጀርነት እምነት ይገነባል። (1 ቆሮ. 15:33) ‘መሰብሰባችንን ቸል እንዳንል’ ከዚህ ይልቅ ‘እርስ በርስ እንድንበረታታ’ የተመከርንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) ሌላው ምክንያት ደግሞ በስብሰባዎች ላይ የሚቀርበው ትምህርት በራሱ እምነት የሚገነባ መሆኑ ነው። ይህም ጳውሎስ “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ሮም 10:17) ታዲያ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን የሕይወታችን ክፍል አድርገነዋል?

10 በመስክ አገልግሎት ስንካፈል ሌሎች እምነት እንዲያዳብሩ ከመርዳታችን በተጨማሪ የራሳችንም እምነት እያደገ ይሄዳል። እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እናዳብራለን፤ እንዲሁም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በድፍረት መናገር እንችላለን።—ሥራ 4:17-20፤ 13:46

11. ካሌብና ኢያሱ ጠንካራ እምነት ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው? እኛስ እንደ እነሱ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት እንደሚረዳንና ለጸሎታችን እንዴት መልስ እንደሚሰጥ ስንመለከት እምነታችን ያድጋል። የካሌብና የኢያሱ ሁኔታ ይህን ያሳያል። ተስፋይቱን ምድር በሰለሉበት ወቅት በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። ይሁንና ከዚያ በኋላ በእያንዳንዱ የሕይወታቸው ክፍል የይሖዋን አመራር ሲመለከቱ እምነታቸው ይበልጥ እያደገ ሄዷል። ኢያሱ “አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም [አልቀረችም]” በማለት ለእስራኤላውያን በእርግጠኝነት መናገሩ የሚያስገርም አይደለም። ከጊዜ በኋላም “ስለዚህ ይሖዋን ፍሩ፤ በንጹሕ አቋምና በታማኝነትም አገልግሉት፤ . . . እኔና ቤተሰቤ ግን ይሖዋን እናገለግላለን” ብሏቸዋል። (ኢያሱ 23:14፤ 24:14, 15) እኛም የይሖዋን ጥሩነት ስንቀምስ እንዲህ ዓይነት የጸና እምነት ማዳበር እንችላለን።—መዝ. 34:8

እምነታችንን በተግባር ማሳየት

12. ያዕቆብ ከእምነት ጋር በተያያዘ የጠቀሰው አስፈላጊ ነገር ምንድን ነው?

12 ሕያው እምነት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “እኔ ደግሞ እምነቴን በሥራ አሳይሃለሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ለዚህ መልስ ይሰጠናል። (ያዕ. 2:18) ተግባራችን ሕያው እምነት እንዳለን ያሳያል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

በአገልግሎት ብዙ ለማከናወን ጥረት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ያሳያሉ (አንቀጽ 13ን ተመልከት)

13. በስብከቱ ሥራ የምናደርገው ተሳትፎ እምነት እንዳለን የሚያሳየው እንዴት ነው?

13 በስብከቱ ሥራ መካፈል እምነታችንን በተግባር የምናሳይበት ግሩም መንገድ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በስብከቱ ሥራ መካፈላችን አምላክ ይህን ሥርዓት ለማጥፋት የወሰነው ጊዜ እንደሚመጣና ‘እንደማይዘገይ!’ እምነት እንዳለን ያሳያል። (ዕን. 2:3) በፈቃደኝነት ተነሳስተን በአገልግሎት ብዙ ለማከናወን የምናደርገው ጥረት እምነታችን የሚለካበት አንዱ መንገድ ነው። ታዲያ የምንችለውን ያህል እያደረግን ምናልባትም በሥራው ያለንን ተሳትፎ ማሳደግ የምንችልባቸውን መንገዶች እየፈለግን ነው? (2 ቆሮ. 13:5) አዎን፣ ‘እምነታችንን በይፋ መናገራችን’ በልባችን ውስጥ እምነት እንዳለ የምናሳይበት አሳማኝ ማስረጃ ነው።—ሮም 10:10ን አንብብ።

14, 15. (ሀ) በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እምነት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ጠንካራ እምነት በተግባር የታየበት አንድ ተሞክሮ ተናገር።

14 በተጨማሪም በየዕለቱ ከሚያጋጥሙን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ጋር በምናደርገው ትግል እምነት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። ሕመም፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ ድህነት ወይም ሌላ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋና ልጁ “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ” ድጋፍ እንደሚያደርጉልን እርግጠኞች ነን። (ዕብ. 4:16) ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ነገሮችም እርዳታ ለማግኘት በመጸለይ እንዲህ ዓይነት እምነት እንዳለን እናሳያለን። ኢየሱስ “የዕለቱን ምግባችንን” ጨምሮ ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች መጸለይ እንደምንችል ተናግሯል። (ሉቃስ 11:3) ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚሰጠን ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በግልጽ መረዳት እንችላለን። በእስራኤል ከባድ ድርቅ በተከሰተበት ጊዜ ይሖዋ ለኤልያስ ምግብና ውኃ አቅርቦለታል። ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት “ቁራዎቹም ጠዋትና ማታ ምግብና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ እሱም ከጅረቱ ይጠጣ ነበር።” (1 ነገ. 17:3-6) ይሖዋ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንዲሟሉልን ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚችል እናምናለን።

በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የምናደርገው ጥረት እምነት እንዳለን ያሳያል (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

15 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት እንደምንችል ምንም ጥያቄ የለውም። ሬቤካ የተባለች በእስያ የምትኖር አንዲት ባለትዳር እህት፣ የዚህን እውነተኝነት በቤተሰቧ ሕይወት አይታለች። የአምላክን መንግሥት በማስቀደምና ትጉህ ሠራተኞች በመሆን በማቴዎስ 6:33 እና በምሳሌ 10:4 ላይ የሚገኘውን ምክር በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ አደረጉ። ሬቤካ ባለቤቷ የሥራው ባሕርይና ያስከተለበት ውጥረት መንፈሳዊነታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ስለተሰማው ሥራውን እንደለቀቀ ተናግራለች። ይሁንና ገና የእነሱን እርዳታ የሚሹ አራት ልጆች ነበሯቸው። ሬቤካ ምን እንዳደረጉ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ጣፋጭ ምግቦችን እየሠራን መሸጥ ጀመርን። ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚህ ሥራ ስንተዳደር ቆይተናል፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ፈጽሞ እንዳልተወን ተሰምቶናል። የምንበላው አጥተን አናውቅም።” አንተስ መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬም ለሰዎች ከሁሉ የተሻለ መመሪያ የያዘ መሆኑን እንደምታምን በተግባር አሳይተሃል?

16. በአምላክ የምንታመን ከሆነ የኋላ ኋላ ምን እናገኛለን?

16 የአምላክን አመራር ከተከተልን ጥሩ ውጤት እንደምናገኝ ፈጽሞ መጠራጠር የለብንም። ጳውሎስ፣ ዕንባቆም በመንፈስ መሪነት የተናገረውን ጠቅሶ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ሲል ጽፏል። (ገላ. 3:11፤ ዕን. 2:4) ስለዚህ ሊረዳን በሚችለው አምላክ ላይ እምነት መጣላችን ወሳኝ ነገር ነው። ጳውሎስ፣ አምላክ “በእኛ ውስጥ ከሚሠራው ኃይሉ ጋር በሚስማማ ሁኔታ፣ ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” እንደሚችል አስገንዝቦናል። (ኤፌ. 3:20) የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ይሁንና የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ስለሚገነዘቡ ጥረታቸውን እንዲባርክላቸው ወደ ይሖዋ ዘወር ይላሉ። ታዲያ አምላካችን ከእኛ ጋር መሆኑ የሚያስደስት አይደለም?

እምነት እንዲጨመርላቸው ያቀረቡት ልመና ምላሽ አገኘ

17. (ሀ) ሐዋርያት እምነት እንዲጨመርላቸው ያቀረቡት ልመና ምላሽ ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) እምነት እንዲጨመርልን የምናቀርበው ልመና መልስ እንደሚያገኝ መጠበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

17 እስካሁን የተወያየንበት ሐሳብ ሐዋርያት “እምነት ጨምርልን” በማለት ለጌታ ያቀረቡት ዓይነት ጥያቄ ለማቅረብ ይገፋፋን ይሆናል። (ሉቃስ 17:5) ሐዋርያቱ ያቀረቡት ጥያቄ በተለይ በ33 ዓ.ም. መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰባቸውና የአምላክን ዓላማ በተመለከተ ጥልቅ ማስተዋል በተሰጣቸው ጊዜ ምላሽ አግኝቷል። ይህም እምነታቸውን አጠናክሮላቸዋል። ደግሞም በወቅቱ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የስብከት ዘመቻ እንዲያካሂዱ አስችሏቸዋል። (ቆላ. 1:23) እኛስ እምነት እንዲጨመርልን የምናቀርበው ልመና መልስ እንደሚያገኝ መጠበቅ እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ’ መልስ እንደምናገኝ ማረጋገጫ ይሰጠናል።—1 ዮሐ. 5:14

18. ይሖዋ እምነት የሚያዳብሩ ሰዎችን የሚባርካቸው እንዴት ነው?

18 ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ይሖዋ በእሱ ሙሉ በሙሉ በሚታመኑ ሰዎች ይደሰታል። ይሖዋ እምነት እንዲጨመርልን ለምናቀርበው ልመና መልስ የሚሰጥ በመሆኑ እምነታችን እጅግ እያደገ ሄዶ ‘ለአምላክ መንግሥት ብቁ ሆነን እንድንቆጠር ሊያደርገን’ ይችላል።—2 ተሰ. 1:3, 5

^ አን.4 ለምሳሌ ያህል፣ የሊሊያን ጎባይታስ ክሎዘን (ሐምሌ 22, 1993 ንቁ! እንግሊዝኛ)፣ የፌሊክስ ቦሪስን (የካቲት 22, 1994 ንቁ! እንግሊዝኛ) እና የጆሴፊን ኤሊአስን (መስከረም 2009 ንቁ!) የሕይወት ታሪክ ተመልከት።