ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 3:1-18
3 በመጨረሻም ወንድሞች፣ በእናንተ ዘንድ እንደሆነው ሁሉ የይሖዋ* ቃል በፍጥነት መስፋፋቱን እንዲቀጥልና+ እንዲከበር ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቋርጡ፤+
2 ደግሞም ከመጥፎና ከክፉ ሰዎች እንድንድን+ ጸልዩልን፤ እምነት ሁሉም ሰው የሚኖረው ነገር አይደለምና።+
3 ጌታ ግን ታማኝ ነው፤ እሱ ያጠነክራችኋል፤ እንዲሁም ከክፉው ይጠብቃችኋል።
4 ከዚህም በላይ እኛ የጌታ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን፣ ያዘዝናችሁን እያደረጋችሁ እንዳለና ወደፊትም ማድረጋችሁን እንደምትቀጥሉ በእናንተ እንተማመናለን።
5 አምላክን እንድትወዱና+ ክርስቶስን በጽናት+ እንድትከተሉ ጌታ ልባችሁን በትክክለኛው አቅጣጫ መምራቱን ይቀጥል።
6 ወንድሞች፣ በሥርዓት ከማይሄድና+ ከእኛ የተቀበላችሁትን* ወግ* ከማይከተል+ ማንኛውም ወንድም እንድትርቁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።
7 የእኛን አርዓያ እንዴት መከተል እንዳለባችሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤+ ምክንያቱም በመካከላችሁ ሳለን ሥርዓት በጎደለው መንገድ አልተመላለስንም፤
8 እንዲሁም የማንንም ምግብ በነፃ አልበላንም።+ እንዲያውም ብዙ ወጪ በማስወጣት በማናችሁም ላይ ሸክም ላለመሆን ሌት ተቀን በመሥራት እንደክምና እንለፋ ነበር።+
9 ይህን ያደረግነው የእኛን አርዓያ እንድትከተሉ+ ራሳችንን ለእናንተ ምሳሌ አድርገን ለማቅረብ ብለን እንጂ ሥልጣን ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም።+
10 እንዲያውም ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ “መሥራት የማይፈልግ ሁሉ አይብላ” የሚል ትእዛዝ ሰጥተናችሁ ነበር።+
11 አንዳንዶች ሥራ ፈት በመሆን በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ+ ሥርዓት በጎደለው መንገድ በመካከላችሁ እንደሚመላለሱ እንሰማለንና።+
12 እንዲህ ያሉ ሰዎች አርፈው ሥራቸውን በመሥራት በድካማቸው ያገኙትን እንዲበሉ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛቸዋለን፤ እንዲሁም አጥብቀን እንመክራቸዋለን።+
13 እናንተ ግን ወንድሞች፣ መልካም የሆነውን ከማድረግ አትታክቱ።
14 ሆኖም በዚህ ደብዳቤ አማካኝነት ላስተላለፍነው ቃል የማይታዘዝ ሰው ቢኖር ይህን ሰው ምልክት አድርጉበት፤* ያፍርም ዘንድ ከእሱ ጋር አትግጠሙ።+
15 ይሁን እንጂ እንደ ጠላት አትመልከቱት፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ወንድም አጥብቃችሁ መምከራችሁን ቀጥሉ።+
16 የሰላም ጌታ ራሱ በሁሉም መንገድ ዘወትር ሰላም ይስጣችሁ።+ ጌታ ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
17 እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ፤+ ይህ የእጅ ጽሑፍ የደብዳቤዎቼ ሁሉ መለያ ነው፤ አጻጻፌ እንዲህ ነው።
18 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁም ጋር ይሁን።