ኢያሱ 24:1-33

  • ኢያሱ የእስራኤላውያንን ታሪክ በድጋሚ ተረከ (1-13)

  • ይሖዋን እንዲያገለግሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው (14-24)

    • “እኔና ቤተሰቤ ግን ይሖዋን እናገለግላለን” (15)

  • ኢያሱ ከእስራኤላውያን ጋር የገባው ቃል ኪዳን (25-28)

  • ኢያሱ ሞቶ ተቀበረ (29-31)

  • የዮሴፍ አፅም በሴኬም ተቀበረ (32)

  • አልዓዛር ሞቶ ተቀበረ (33)

24  ከዚያም ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ በሴኬም አንድ ላይ ሰበሰባቸው፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ዳኞችና አለቆች+ ጠራ፤ እነሱም በእውነተኛው አምላክ ፊት ቆሙ።  ኢያሱም ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአብርሃምና የናኮር አባት የሆነውን ታራን ጨምሮ አባቶቻችሁ+ ከረጅም ጊዜ በፊት+ ከወንዙ* ማዶ ይኖሩ ነበር፤ እነሱም ሌሎች አማልክትን ያገለግሉ ነበር።+  “‘እኔም ከጊዜ በኋላ አባታችሁን አብርሃምን+ ከወንዙ* ማዶ አምጥቼ በመላው የከነአን ምድር እንዲዘዋወር አደረግኩት፤ ዘሩንም አበዛሁለት።+ ይስሐቅን ሰጠሁት፤+  ከዚያም ለይስሐቅ ያዕቆብንና ኤሳውን ሰጠሁት።+ በኋላም ለኤሳው ሴይር ተራራን ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤+ ያዕቆብና ልጆቹ ደግሞ ወደ ግብፅ ወረዱ።+  በኋላም ሙሴንና አሮንን ላክኋቸው፤+ ግብፅንም በመካከላቸው በፈጸምኩት ነገር በመቅሰፍት መታኋት፤+ ከዚያም እናንተን አወጣኋችሁ።  አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸውና+ ወደ ባሕሩ በደረሳችሁ ጊዜ ግብፃውያኑ የጦር ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን አሰልፈው አባቶቻችሁን እየተከታተሉ እስከ ቀይ ባሕር ድረስ መጡ።+  እነሱም ወደ ይሖዋ መጮኽ ጀመሩ፤+ በመሆኑም በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ እንዲኖር አደረገ፤ ባሕሩንም በላያቸው ላይ በመመለስ አሰመጣቸው፤+ በግብፅ ያደረግኩትንም የገዛ ዓይኖቻችሁ አይተዋል።+ ከዚያም በምድረ በዳ ለብዙ ዓመታት* ኖራችሁ።+  “‘ከዮርዳኖስ ማዶ* ይኖሩ ወደነበሩት ወደ አሞራውያንም ምድር አመጣኋችሁ፤ እነሱም ተዋጓችሁ።+ ሆኖም ምድራቸውን እንድትወርሱ እነሱን በእጃችሁ አሳልፌ ሰጠኋችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው።+  ከዚያም የሞዓብ ንጉሥ የሆነው የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነስቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። የቢዖርን ልጅ በለዓምንም እናንተን እንዲረግም አስጠራው።+ 10  እኔ ግን በለዓምን ልሰማው አልፈለግኩም።+ በመሆኑም ደጋግሞ ባረካችሁ፤+ እኔም ከእጁ አዳንኳችሁ።+ 11  “‘ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ+ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ።+ የኢያሪኮ መሪዎች* የሆኑት አሞራውያን፣ ፈሪዛውያን፣ ከነአናውያን፣ ሂታውያን፣ ገርጌሻውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ተዋጓችሁ፤ እኔ ግን እነሱን በእጃችሁ አሳልፌ ሰጠኋችሁ።+ 12  ከእናንተ አስቀድሜ ጭንቀት* ላክሁ፤ ሁለቱንም የአሞራውያን ነገሥታት ከፊታችሁ አባረራቸው።+ ይህም የሆነው በሰይፋችሁ ወይም በቀስታችሁ አይደለም።+ 13  ስለዚህ ያልደከማችሁበትን ምድር፣ ያልገነባችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፤+ እናንተም በዚያ መኖር ጀመራችሁ። ካልተከላችሁት የወይን ተክልና የወይራ ዛፍ እየበላችሁ ነው።’+ 14  “ስለዚህ ይሖዋን ፍሩ፤ በንጹሕ አቋምና* በታማኝነትም* አገልግሉት፤+ አባቶቻችሁ ከወንዙ* ማዶና በግብፅ ምድር ያገለገሏቸውን አማልክት አስወግዱ፤+ ይሖዋን አገልግሉ። 15  ይሖዋን ማገልገል መጥፎ መስሎ ከታያችሁ ደግሞ የምታገለግሉትን ዛሬውኑ ምረጡ፤+ ከወንዙ* ማዶ የነበሩት አባቶቻችሁ ያገለገሏቸውን አማልክትም+ ይሁን አሁን በምትኖሩበት ምድር ያሉት አሞራውያን የሚያገለግሏቸውን አማልክት+ መምረጥ ትችላላችሁ። እኔና ቤተሰቤ ግን ይሖዋን እናገለግላለን።” 16  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በእኛ በኩል ይሖዋን መተውና ሌሎች አማልክትን ማገልገል ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። 17  እኛንም ሆነ አባቶቻችንን ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣን፣+ እነዚህን ታላላቅ ምልክቶች በፊታችን የፈጸመው+ እንዲሁም በሄድንበት መንገድ ሁሉና አቋርጠን ባለፍናቸው ሕዝቦች ሁሉ መካከል የጠበቀን+ አምላካችን ይሖዋ ነው። 18  ይሖዋ አሞራውያንን ጨምሮ ከእኛ በፊት በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች በሙሉ አባረረ። ስለዚህ እኛም ይሖዋን እናገለግላለን፤ ምክንያቱም እሱ አምላካችን ነው።” 19  ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ አምላክን ማገልገል አትችሉም፤ ምክንያቱም እሱ ቅዱስ አምላክ ነው፤+ እንዲሁም እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።+ መተላለፋችሁንና* ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም።+ 20  ይሖዋን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን ብታገለግሉ እሱም መልካም ነገር ካደረገላችሁ በኋላ በእናንተ ላይ ይዞርባችኋል፤ ደግሞም ያጠፋችኋል።”+ 21  ሕዝቡ ግን ኢያሱን “በፍጹም፣ እኛ ይሖዋን እናገለግላለን!” አሉት።+ 22  ስለዚህ ኢያሱ ሕዝቡን “በራሳችሁ ፍላጎት ይሖዋን ለማገልገል ስለመረጣችሁ እናንተ በራሳችሁ ላይ ምሥክሮች ናችሁ” አላቸው።+ እነሱም “አዎ፣ ምሥክሮች ነን” አሉ። 23  “እንግዲህ አሁን በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ አዘንብሉ።” 24  ሕዝቡም ኢያሱን “አምላካችንን ይሖዋን እናገለግላለን፤ ቃሉንም እንሰማለን!” አለው። 25  በመሆኑም ኢያሱ በዚያ ቀን ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ ለእነሱም በሴኬም ሥርዓትና ደንብ ደነገገላቸው። 26  ከዚያም ኢያሱ እነዚህን ቃላት በአምላክ የሕግ መጽሐፍ+ ላይ ጻፋቸው፤ ትልቅ ድንጋይም ወስዶ+ በይሖዋ መቅደስ አጠገብ በሚገኘው ትልቅ ዛፍ ሥር አቆመው። 27  ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ ይህ ድንጋይ ይሖዋ የነገረንን ሁሉ ስለሰማ በእኛ ላይ እንደ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል፤+ እንዲሁም አምላካችሁን እንዳትክዱ በእናንተ ላይ እንደ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።” 28  ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ፣ እያንዳንዱን ወደየርስቱ አሰናበተ።+ 29  ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ የይሖዋ አገልጋይ የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ።+ 30  እነሱም ከጋአሽ ተራራ በስተ ሰሜን በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ በሚገኘው ርስቱ ውስጥ በቲምናትሰራ+ ቀበሩት። 31  እስራኤላውያን ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከኢያሱ በኋላ በሕይወት በኖሩትና ይሖዋ ለእስራኤላውያን ሲል ያደረገውን ነገር በሙሉ በሚያውቁት ሽማግሌዎች ሁሉ ዘመን ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጠሉ።+ 32  እስራኤላውያን ከግብፅ ይዘውት የወጡት የዮሴፍ አፅም + ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር+ ልጆች ላይ በ100 ጥሬ ገንዘብ በገዛው+ በሴኬም በሚገኘው እርሻ ውስጥ ተቀብሮ ነበር፤ ይህም የዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ።+ 33  የአሮን ልጅ አልዓዛርም ሞተ።+ እነሱም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ለልጁ ለፊንሃስ+ ተሰጥቶት በነበረው ኮረብታ ቀበሩት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ቃል በቃል “ቀናት።”
በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።
“ባለ ርስት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ድንጋጤ፤ ሽብር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ያለነቀፋና።”
ወይም “በእውነትም።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
ወይም “ዓመፃችሁንና።”