በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለተቀበልከው ነገር አድናቆት አለህ?

ለተቀበልከው ነገር አድናቆት አለህ?

“እኛ አምላክ በደግነት የሰጠንን ነገሮች ማወቅ እንችል ዘንድ ከአምላክ የሆነውን መንፈስ ተቀበልን።”1 ቆሮ. 2:12

1. የትኛውን አባባል መስማት የተለመደ ነው?

‘በእጅ ያለ ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል’ ሲባል እንሰማለን፤ ብዙ ሰዎች በእጃቸው ያለውን ውድ ነገር እስኪያጡት ድረስ አያደንቁትም። አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይሰማሃል? አንዳንዶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ያገኙትን ነገር ያን ያህል ቦታ አይሰጡት ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በሀብታም ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ልጅ ያሉትን ነገሮች ላያደንቅ ይችላል። ተሞክሮ የሌላቸው ወጣቶችም እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፤ እነዚህ ወጣቶች በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ በሚገባ አይገነዘቡ ይሆናል።

2, 3. (ሀ) ክርስቲያን ወጣቶች የትኛውን አመለካከት እንዳያዳብሩ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል? (ለ) ያለንን ነገር እንድናደንቅ ምን ሊረዳን ይችላል?

2 በአሥራዎቹ ዕድሜ አሊያም በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ወጣት ከሆንክ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው? በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ያተኮረው በቁሳዊ ነገሮች ላይ ይኸውም ዳጎስ ያለ ደሞዝ፣ ጥሩ ቤት ወይም ጊዜው ያመጣቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማግኘታቸው ላይ ነው። ይሁንና የሚያሳስቡን እነዚህ ነገሮች ብቻ ከሆኑ በጣም አስፈላጊ ለሆነው ነገር ይኸውም ለመንፈሳዊ ሀብት ቦታ አልሰጠንም ማለት ነው። የሚያሳዝነው በዛሬው ጊዜ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት ጥረት እንኳ አያደርጉም። ክርስቲያን ወላጆች ያሳደጓችሁ እናንት ወጣቶች፣ ያገኛችሁት መንፈሳዊ ውርሻ ውድ ዋጋ ያለው መሆኑን  እንዳትዘነጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋችኋል። (ማቴ. 5:3) ለመንፈሳዊ ነገር አድናቆት ማጣት መላ ሕይወትን የሚነካ አሳዛኝ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።

3 ይሁንና እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ እንዳይደርስብህ መከላከል ትችላለህ። መንፈሳዊ ውርሻህን ከፍ አድርገህ እንድትመለከት ምን ሊረዳህ ይችላል? ለመንፈሳዊ ውርሻችን ትልቅ ቦታ መስጠት የጥበብ አካሄድ የሆነበትን ምክንያት የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት። እነዚህ ምሳሌዎች፣ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ ክርስቲያን ያገኘውን መንፈሳዊ ሀብት እንዲያደንቅ የሚረዱ ናቸው።

አድናቆት ጎድሏቸው ነበር

4. 1 ሳሙኤል 8:1-5 ስለ ሳሙኤል ልጆች ምን ይነግረናል?

4 ላገኙት ውድ መንፈሳዊ ውርሻ አድናቆት ያላሳዩ አንዳንድ ሰዎችን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን። የነቢዩ ሳሙኤልን ቤተሰብ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ሳሙኤል ከልጅነቱ ጀምሮ ይሖዋን ከማገልገሉም ሌላ በአምላክ ዘንድ መልካም ስም አትርፏል። (1 ሳሙ. 12:1-5) ለልጆቹ ለኢዮኤልና ለአብያ ግሩም አርዓያ ትቶላቸው ነበር፤ ልጆቹ የእሱን ምሳሌ ቢከተሉ ጥሩ ነበር። እነሱ ግን የአባታቸውን ምሳሌነት ከፍ አድርገው ስላልተመለከቱ መጥፎ አካሄድ ተከተሉ። ከአባታቸው በተቃራኒ እነሱ ‘ፍርድን ያጣምሙ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—1 ሳሙኤል 8:1-5ን አንብብ።

5, 6. የኢዮስያስ ልጆችና የልጅ ልጁ ምን ዓይነት አካሄድ ተከትለዋል?

5 የንጉሥ ኢዮስያስ ልጆችም ተመሳሳይ ስህተት ፈጽመዋል። ኢዮስያስ ይሖዋን በማምለክ ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው። የአምላክ ሕግ መጽሐፍ ሲገኝና ሲነበብለት የይሖዋን መመሪያዎች በተግባር ለማዋል ከልቡ ጥረት አድርጓል። ኢዮስያስ ጣዖት አምልኮንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን ከምድሪቱ ለማስወገድ እርምጃ የወሰደ ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡ ይሖዋን እንዲታዘዙ አበረታትቷል። (2 ነገ. 22:8፤ 23:2, 3, 12-15, 24, 25) በእርግጥም ኢዮስያስ ለልጆቹ ታላቅ መንፈሳዊ ውርስ ትቶላቸው ነበር! ከጊዜ በኋላ ሦስት ልጆቹ እንዲሁም አንድ የልጅ ልጁ ንጉሥ ሆነዋል፤ ይሁንና አንዳቸውም ቢሆኑ ከእሱ ለተቀበሉት ውርሻ አድናቆት አላሳዩም።

6 ኢዮስያስን ተክቶ የነገሠው ልጁ ኢዮአክስ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ [ነገር አድርጓል]።” ኢዮአክስ ለሦስት ወር ብቻ ከገዛ በኋላ የግብፁ ፈርዖን አስሮ የወሰደው ሲሆን የሞተውም በግዞት እያለ ነው። (2 ነገ. 23:31-34) ከዚያም ወንድሙ ኢዮአቄም ለ11 ዓመታት ገዝቷል። እሱም ከአባቱ ለተቀበለው ነገር አድናቆት አልነበረውም። ኢዮአቄም በተከተለው መጥፎ ጎዳና ምክንያት “አህያ እንደሚቀበር ይቀበራል” በማለት ኤርምያስ ስለ እሱ ትንቢት ተናግሯል። (ኤር. 22:17-19) ከኢዮስያስ በኋላ የነገሡት ሌሎች ነገሥታት ይኸውም ልጁ ሴዴቅያስም ሆነ የልጅ ልጁ ዮአኪን የተሻሉ ሆነው አልተገኙም፤ አንዳቸውም ቢሆኑ የኢዮስያስን የጽድቅ ጎዳና አልተከተሉም።—2 ነገ. 24:8, 9, 18, 19

7, 8. (ሀ) ሰለሞን ያገኘውን መንፈሳዊ ውርሻ ሳይጠቀምበት የቀረው እንዴት ነው? (ለ) ለመንፈሳዊ ውርሻቸው አድናቆት ከጎደላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ምን እንማራለን?

7 ንጉሥ ሰለሞን ከአባቱ ከዳዊት ታላቅ ውርስ አግኝቶ ነበር። ሰለሞን ግሩም መንፈሳዊ ሀብት የነበረው ከመሆኑም ሌላ መጀመሪያ ላይ አካሄዱ መልካም ነበር፤ እያደር ግን ለትክክለኛው ጎዳና ያለው አድናቆት ጠፋ። “ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።” (1 ነገ. 11:4) በመሆኑም ሰለሞን የይሖዋን ሞገስ አጣ።

8 ከልጅነታቸው ጀምሮ ይሖዋን ለማወቅና ትክክለኛውን አካሄድ ለመከተል የሚያስችል አጋጣሚ የነበራቸው እስካሁን ያየናቸው ሰዎች ያገኙትን መብት ሳይጠቀሙበት መቅረታቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ይሁንና ጥንትም ሆነ ዛሬ እንዲህ ዓይነት አካሄድ የተከተሉት ሁሉም ወጣቶች አይደሉም። ለወጣት ክርስቲያኖች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ጥሩ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

 ለተቀበሉት ነገር አድናቆት ነበራቸው

9. የኖኅ ልጆች ግሩም ምሳሌ የተዉት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

9 የኖኅ ልጆች ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል። አባታቸው፣ መርከብ እንዲሠራና ቤተሰቡን ይዞ ወደ መርከቡ እንዲገባ ትእዛዝ ተሰጥቶት ነበር። የኖኅ ልጆች የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዘበው እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። እነዚህ ልጆች ከአባታቸው ጋር ተባብረው መሆን አለበት። መርከቡን ሲሠራ ያገዙት ሲሆን በኋላም ወደ መርከቡ አብረውት ገብተዋል። (ዘፍ. 7:1, 7) ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? ዘፍጥረት 7:3 እንደሚገልጸው እንስሳቱን ወደ መርከቡ ያስገቡት “በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ” ሲሉ ነው። ሰዎችም ከጥፋቱ ተርፈዋል። የኖኅ ልጆች ከአባታቸው ለተቀበሉት ነገር ትልቅ ቦታ ስለሰጡ፣ ከጥፋቱ የሚተርፍ የሰው ዘር እንዲኖርና በጸዳችው ምድር ላይ እውነተኛው አምልኮ እንደገና እንዲቋቋም አስተዋጽኦ ማድረግ ችለዋል።—ዘፍ. 8:20፤ 9:18, 19

10. በባቢሎን የነበሩት አራት ወጣት ዕብራውያን ለተማሩት እውነት አድናቆት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?

10 ከበርካታ ዘመናት በኋላ የኖሩ አራት ዕብራውያን ወጣቶችም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ መገንዘባቸውን አሳይተዋል። አናንያ፣ ሚሳኤል፣ አዛርያስና ዳንኤል በግዞት ወደ ባቢሎን የተወሰዱት በ617 ዓ.ዓ. ነው። አስተዋይና መልከ ቀና የሆኑት እነዚህ ወጣቶች ከባቢሎናውያኑ አኗኗር ጋር በቀላሉ ሊላመዱ ይችሉ ነበር። እነሱ ግን እንዲህ አላደረጉም። ውርሻቸውን ይኸውም የተማሩትን ነገር እንዳልዘነጉ ካደረጉት ነገር መመልከት ይቻላል። እነዚህ አራት ወጣቶች ልጅ እያሉ የተማሯቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች አጥብቀው በመከተላቸው ብዙ በረከቶች አጭደዋል።ዳንኤል 1:8, 11-15, 20ን አንብብ።

11. ኢየሱስ ካገኘው መንፈሳዊ ውርስ ሌሎች የተጠቀሙት እንዴት ነው?

11 ግሩም ምሳሌ ስለተዉ ሰዎች ስናነሳ የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን ሳንጠቅስ ብናልፍ ተገቢ አይሆንም። ኢየሱስ ከአባቱ ብዙ ነገሮችን የተቀበለ ሲሆን ለእነዚህም ልባዊ አድናቆት ነበረው። “እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ” ማለቱ ለቀሰመው እውቀት አድናቆት እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። (ዮሐ. 8:28) ኢየሱስ፣ ሌሎችም እሱ ካገኘው ነገር እንዲጠቀሙ ይፈልግ ነበር። “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 4:18, 43) ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት የሌለው የዚህ ‘ዓለም ክፍል አለመሆን’ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን አድማጮቹ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።—ዮሐ. 15:19

ለተቀበልከው ነገር አድናቆት ይኑርህ

12. (ሀ) 2 ጢሞቴዎስ 3:14-17 በዛሬው ጊዜ ባሉ በርካታ ወጣቶች ላይ የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያን ወጣቶች የትኞቹን ጥያቄዎች ሊያስቡባቸው ይገባል?

12 እስካሁን እንደተመለከትናቸው ወጣቶች ሁሉ አንተንም ያሳደጉህ ለይሖዋ አምላክ ያደሩ ወላጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ከሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ጢሞቴዎስ የሚናገሩት ሐሳብ ለአንተም ይሠራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14-17ን አንብብ።) ስለ እውነተኛው አምላክና እሱን እንዴት ማስደሰት እንደምትችል ‘የተማርከው’ ከወላጆችህ ነው። ወላጆችህ ከጨቅላነትህ ጀምሮ አስተምረውህ ይሆናል። ይህ ደግሞ “በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንድታገኝ እንዲሁም ለአምላክ አገልግሎት “ሙሉ በሙሉ ብቁ” እንድትሆን እንደረዳህ ጥርጥር የለውም። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘ለተቀበልከው ነገር አድናቆት አለህ?’ የሚለው ነው። ይህን ለመመለስ ራስህን መመርመር ያስፈልግህ ይሆናል። እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች መጠየቅህ ለዚህ ይረዳሃል፦ ‘ከጥንት ጀምሮ ከነበሩ የአምላክ ታማኝ ምሥክሮች እንደ አንዱ በመቆጠሬ ምን ይሰማኛል? አምላክ ከሚያውቃቸው ጥቂት ሰዎች መካከል በመሆኔስ? እውነትን ማወቅ ምን ያህል ልዩና ታላቅ መብት መሆኑን እገነዘባለሁ?’

13, 14. አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች ምን ፈተና ያጋጥማቸዋል? ለዚህ ፈተና መሸነፍ ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

13 ክርስቲያን ወላጆች ያሳደጓቸው አንዳንድ  ወጣቶች እኛ ባለንበት መንፈሳዊ ገነት እና በጨለማ በተዋጠው የሰይጣን ዓለም መካከል ያለው የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ላይታያቸው ይችላል። አንዳንዶች ዓለም ምን እንደሚመስል ለማየት ይፈተኑ ይሆናል። ይሁንና በመኪና መገጨት ምን ያህል ሥቃይ እንደሚያስከትል አሊያም ሊገድል የሚችል መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ስትል እየበረረ ያለ መኪና ውስጥ ዘለህ ትገባለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! በተመሳሳይም በዚህ ዓለም ላይ ያለው “ያዘቀጠ ወራዳ ሕይወት” ምን ያህል ሥቃይ እንደሚያስከትል ለማየት ስንል ብቻ ይህን ዓይነቱን አኗኗር መከተል አያስፈልገንም።—1 ጴጥ. 4:4

14 በእስያ የሚኖረው ጄነር ያደገው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው። በ12 ዓመቱ ተጠመቀ። ጄነር በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ግን የዓለም አካሄድ ይስበው ጀመር። “ዓለም የሚያቀርበውን ‘ነፃነት’ ማየት ፈለግሁ” ብሏል። በዚህም ምክንያት ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት ጀመረ። ጄነር 15 ዓመት ሲሆነው የአንዳንድ መጥፎ ጓደኞቹን አካሄድ ይከተል ጀመር። ልክ እንደ እነሱ የአልኮል መጠጥ ይጠጣ ብሎም ጸያፍ ቃላትን ይጠቀም ነበር። ብዙውን ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር ፑል እና ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው የኮምፒውተር ጌሞች ሲጫወት አምሽቶ ቤት የሚገባው ሌሊት ነበር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ዓለም የሚያቀርበው ነገር እውነተኛ እርካታ እንደማያስገኝ ተገነዘበ። እንዲህ ያለው ሕይወት ባዶ እንደሆነ አስተዋለ። አሁን ወደ ጉባኤ የተመለሰ ቢሆንም እንዲህ ይላል፦ “አሁንም ፈተና የሚሆኑብኝ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሆኖም ከይሖዋ የማገኘው በረከት ከተውኳቸው ነገሮች ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።”

15. እውነት ቤት ያላደጉ ወጣቶችም ሊያስቡበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

15 እርግጥ ነው፣ በጉባኤ ውስጥ እውነት ቤት ያላደጉ ወጣቶችም አሉ። ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ ከሆንክ ፈጣሪህን ማወቅና ማገልገል ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ አትዘንጋ! በምድር ላይ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። በመሆኑም ይሖዋ በደግነት ወደ ራሱ ከሳባቸው ብሎም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከገለጠላቸው ሰዎች መካከል መሆን በእርግጥም ታላቅ በረከት ነው። (ዮሐ. 6:44, 45) ዛሬ በምድር ላይ ካሉ 1,000 ሰዎች መካከል የእውነት ትክክለኛ እውቀት ያለው 1ዱ ነው ማለት ይቻላል፤ አንተም እንዲህ ያለ እውቀት ካላቸው ሰዎች መካከል ነህ። ታዲያ እውነትን የሰማንበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ እንዲህ ያለ እውቀት በማግኘታችን ልንደሰት አይገባም? (1 ቆሮንቶስ 2:12ን አንብብ።) ጄነር እንዲህ ብሏል፦ “የአጽናፈ ዓለም ገዢ በሆነው በይሖዋ ዘንድ ለመታወቅ እኔ ማን ነኝ? ይህን ማሰቡ እንኳ ይከብደኛል።” (መዝ. 8:4) ጄነር በሚኖርበት አካባቢ ያለች አንዲት ክርስቲያን “ተማሪዎች፣ መምህራቸው የተለየ ትኩረት ሲሰጣቸው ኩራት  ይሰማቸዋል። ታዲያ ታላቅ አስተማሪ በሆነው በይሖዋ መታወቅማ ከዚህ የላቀ ግሩም መብት አይደለም?” ብላለች።

ውሳኔህ ምንድን ነው?

16. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወጣቶች ምን ማድረጋቸው የጥበብ አካሄድ ነው?

16 በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ፣ በሕይወታቸው ውስጥ ትክክለኛ ውሳኔ ያደረጉ ሰዎች ጥቂት ናቸው፤ ታዲያ አንተስ ታላቅ መብት ያለህ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ለምን ቁርጥ ውሳኔ አታደርግም? እንዲህ ካደረግህ ከጥንት ጀምሮ ከነበሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አንዱ ትሆናለህ። እንዲህ ያለ የጥበብ ውሳኔ ማድረግ፣ ልክ እንደ ደነዘዘ ሰው ከዚህ ዓለም ጋር ወደ ጥፋት እየተነዱ ያሉትን አብዛኞቹን ወጣቶች ከመከተል በጣም የተሻለ እንደሆነ ጥያቄ የለውም።—2 ቆሮ. 4:3, 4

17-19. ከዓለም የተለዩ መሆንን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንድታዳብር ሊረዳህ የሚችለው ምንድን ነው?

17 ይህ ሲባል ግን ከዓለም የተለዩ መሆን ሁልጊዜ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። ሆኖም ቆም ብለህ ካሰብከው የተለዩ መሆን የጥበብ እርምጃ ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድን የኦሎምፒክ ተወዳዳሪ እንውሰድ። ግለሰቡ እዚያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከሌሎች ሰዎች የተለየ መሆን እንዳለበት ምንም ጥርጥር የለውም። ጊዜውንና ትኩረቱን በመሻማት የሚያስፈልገውን ሥልጠና እንዳያገኝ እንቅፋት የሚሆኑ ብዙ ነገሮችን መተው እንደሚኖርበት ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ግን ከእኩዮቹ የተለየ ለመሆን ፈቃደኛ መሆኑ፣ የበለጠ ሥልጠና ለማግኘትና ግቡ ላይ ለመድረስ ያስችለዋል።

18 ዓለም ለሕይወት ያለው አመለካከት አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ነው። የወደፊት ሕይወትህን ከግምት ያስገባ አመለካከት ካለህ ከዓለም መለየትህ እንዲሁም በዓለም ካሉ መንፈሳዊነትህንም ሆነ ሥነ ምግባራዊ አቋምህን ከሚያበላሹ ነገሮች መራቅህ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት [አጥብቀህ ለመያዝ]” ያስችልሃል። (1 ጢሞ. 6:19) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለምታምንበት ነገር አቋም የምትወስድ ከሆነ የኋላ ኋላ መደሰትህ አይቀርም። እንዲህ ማድረግህ የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ተቋቁመህ ለማለፍ የሚያስችል ጥንካሬ እንዳለህ ያረጋግጣል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ በአንተ እንደሚኮራና ፈገግ ብሎ እንደሚመለከትህ ማሰብ ትችላለህ! ይህም፣ ከሌሎች በመለየትህ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርግሃል!”

19 አንድ ሰው አሁን በሚያገኘው ነገር ላይ ብቻ ካተኮረ ሕይወት ምንም ትርጉም አይኖረውም። (መክ. 9:2, 10) ስለ ሕይወትህ ትርጉም እንዲሁም ምን ያህል መኖር እንደምትፈልግ በቁም ነገር የምታስብ ወጣት ከሆንክ ግን ‘አሕዛብ እንደሚመላለሱት’ ከመመላለስ ይልቅ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራትህ አስተዋይነት አይሆንም?—ኤፌ. 4:17፤ ሚል. 3:18

20, 21. ትክክለኛ ውሳኔዎች ማድረጋችን ወደፊት ምን ያስገኝልናል? ከእኛስ ምን ይጠበቃል?

20 ትክክለኛ ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የሚያረካ ሕይወት መምራት ወደፊት ደግሞ ‘ምድርን ወርሰን’ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንችላለን። የተዘጋጁልን ስፍር ቁጥር የሌላቸው አስደናቂ በረከቶች አእምሯችን ሊገምተው ከሚችለው በላይ ናቸው። (ማቴ. 5:5፤ 19:29፤ 25:34) እርግጥ ነው፣ አምላክ እነዚህን በረከቶች ሲሰጠን ከእኛ የሚጠብቀው ነገር አለ። (1 ዮሐንስ 5:3, 4ን አንብብ።) ሆኖም በረከቶቹን ለማግኘት ስንል አሁን አምላክን በታማኝነት ብናገለግል የሚያስቆጭ አይሆንም!

21 ከአምላክ የተቀበልነው ነገር እንዴት ብዙ ነው! ስለ ቃሉ ትክክለኛ እውቀት ያለን ከመሆኑም ሌላ ስለ እሱና ስለ ዓላማው እውነቱን አውቀናል። በስሙ የመጠራትና ስለ እሱ የመመሥከር መብት አግኝተናል። በተጨማሪም ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቶልናል። (መዝ. 118:7) እንግዲያው ወጣቶችም ሆንን አዋቂዎች ሁላችንም፣ ለይሖዋ “ለዘላለም ክብር” የመስጠት ልባዊ ፍላጎት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ሕይወታችንን በመምራት አድናቆታችንን እንግለጽ።—ሮም 11:33-36፤ መዝ. 33:12