አንደኛ ሳሙኤል 8:1-22

  • እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ጠየቁ (1-9)

  • ሳሙኤል ሕዝቡን አስጠነቀቀ (10-18)

  • ይሖዋ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀበለ (19-22)

8  ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ውስጥ ፈራጆች ሆነው እንዲያገለግሉ ሾማቸው። 2  የበኩር ልጁ ስም ኢዩኤል ሲሆን የሁለተኛው ልጁ ስም ደግሞ አቢያህ+ ነበር፤ እነሱም በቤርሳቤህ ፈራጆች ነበሩ። 3  ይሁንና ልጆቹ የእሱን ፈለግ አልተከተሉም፤ ከዚህ ይልቅ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም+ ለማግኘት ይጥሩ፣ ጉቦ ይቀበሉ+ እንዲሁም ፍርድ ያጣምሙ+ ነበር። 4  ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ አንድ ላይ ተሰብስበው በራማ ወደሚገኘው ወደ ሳሙኤል መጡ። 5  እንዲህም አሉት፦ “እንግዲህ አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህ ደግሞ የአንተን ፈለግ እየተከተሉ አይደለም። ስለዚህ እንደ ሌሎቹ ብሔራት ሁሉ በእኛ ላይ ፈራጅ የሚሆን ንጉሥ ሹምልን።”+ 6  ይሁንና “በእኛ ላይ ፈራጅ የሚሆን ንጉሥ ሹምልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም።* ሳሙኤልም ወደ ይሖዋ ጸለየ፤ 7  ይሖዋም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ የሚልህን ሁሉ ስማ፤ አልቀበልም ያሉት አንተን አይደለም፤ ይልቁንም ንጉሣቸው አድርገው መቀበል ያልፈለጉት እኔን ነው።+ 8  እየፈጸሙ ያሉት ነገር ከግብፅ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከዚህች ዕለት ድረስ ሲያደርጉ የነበሩትን ነው፤ እኔን ትተው+ ሌሎች አማልክትን አገለገሉ፤+ በአንተም ላይ እያደረጉ ያሉት ይህንኑ ነው። 9  ስለዚህ የሚሉህን ስማ። ይሁን እንጂ በጥብቅ አስጠንቅቃቸው፤ በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት እንዳለው ንገራቸው።” 10  በመሆኑም ሳሙኤል ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለጠየቁት ሰዎች የይሖዋን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 11  እንዲህ አላቸው፦ “በእናንተ ላይ የሚነግሠው ንጉሥ እንዲህ እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት አለው፦+ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ+ ሠረገላው ውስጥ ያስቀምጣቸዋል፤+ ፈረሰኞችም+ ያደርጋቸዋል፤ የተወሰኑትንም ከሠረገሎቹ ፊት ፊት እንዲሮጡ ያደርጋል። 12  ለራሱም የሺህ አለቆችንና+ የሃምሳ አለቆችን+ ይሾማል፤ አንዳንዶቹም መሬቱን ያርሳሉ፣+ እህሉን ያጭዳሉ+ እንዲሁም የጦር መሣሪያዎቹንና ለሠረገሎቹ+ የሚሆኑትን ዕቃዎች ይሠራሉ። 13  ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ቅባት ቀማሚዎች፣* ምግብ አብሳዮችና ዳቦ ጋጋሪዎች+ ያደርጋቸዋል። 14  እንዲሁም ከማሳችሁ፣ ከወይን እርሻችሁና ከወይራ ዛፎቻችሁ+ ምርጥ የሆነውን ይወስዳል፤ ለአገልጋዮቹም ይሰጣቸዋል። 15  ከእህል ማሳችሁና ከወይን እርሻችሁ ላይ አንድ አሥረኛውን ወስዶ ለቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱና ለአገልጋዮቹ ይሰጣል። 16  ወንድ አገልጋዮቻችሁንና ሴት አገልጋዮቻችሁን፣ ከከብቶቻችሁ መካከል ምርጥ የሆኑትን እንዲሁም አህዮቻችሁን ይወስዳል፤ ለራሱ ሥራም ይጠቀምባቸዋል።+ 17  ከመንጋችሁ መካከል አንድ አሥረኛውን ይወስዳል፤+ እናንተም የእሱ አገልጋዮች ትሆናላችሁ። 18  ለራሳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሳ የምትጮኹበት ቀን ይመጣል፤+ ሆኖም በዚያ ቀን ይሖዋ አይመልስላችሁም።” 19  ሕዝቡ ግን ሳሙኤል የተናገረውን ለመስማት አሻፈረኝ አለ፤ እንዲህም አለ፦ “አይሆንም፣ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን። 20  ከዚያም እንደ ሌሎች ብሔራት እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ፈራጅ ይሆንልናል፣ ይመራናል እንዲሁም ጦርነት ሲገጥመን ይዋጋልናል።” 21  ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ከሰማ በኋላ የተናገሩትን ነገር ይሖዋ እየሰማ በድጋሚ ተናገረ። 22  ይሖዋም ሳሙኤልን “የሚሉህን ስማ፤ በላያቸው የሚገዛ ንጉሥም አንግሥላቸው”+ አለው። ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ለሳሙኤል መጥፎ ሆኖ ታየው።”
ወይም “ሽቶ ቀማሚዎች።”