በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኤርምያስ፣ ራሔል ስለ ልጆቿ እንዳለቀሰች ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?

ኤርምያስ 31:15 “ዋይታና መራራ ልቅሶ፣ ከራማ ተሰማ፤ ልጆቿ የሉምና፣ ራሔል አለቀሰች፤ መጽናናትም እንቢ አለች” ይላል።

የራሔል ሁለት ወንዶች ልጆች የሞቱት ከእሷ በኋላ ነው። በመሆኑም ኤርምያስ፣ ራሔል ከሞተች ከ1,000 ዓመታት በኋላ የዘገበው ነገር የተሳሳተ ይመስል ይሆናል።

የራሔል የበኩር ልጅ ዮሴፍ ነው። (ዘፍ. 30:22-24) በኋላም ሌላ ልጅ የወለደች ሲሆን ስሙም ብንያም ተብሏል። ይሁን እንጂ ራሔል ሁለተኛውን ልጇን በምትወልድበት ጊዜ ሞተች። በመሆኑም ኤርምያስ 31:15 ራሔል ልጆቿ ‘ስለሌሉ’ እንዳለቀሰች የሚናገረው ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳል።

የመጀመሪያ ልጇ ዮሴፍ ከጊዜ በኋላ ምናሴንና ኤፍሬምን እንደወለደ ልብ ማለት ያስፈልጋል። (ዘፍ. 41:50-52፤ 48:13-20) ውሎ አድሮም ኤፍሬም ከመላው የሰሜናዊ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ጎላ ብሎ የሚታይና ተደማጭነት ያለው ነገድ ስለሆነ አሥሩንም ነገዶች ይወክል ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የራሔል ሁለተኛ ልጅ የሆነው የብንያም ነገድ፣ ከይሁዳ ነገድ ጋር በደቡባዊ መንግሥት ውስጥ ተካትቶ ነበር። ከዚህ አንጻር ራሔል በመላው እስራኤል ይኸውም በሰሜናዊውም ሆነ በደቡባዊው መንግሥት የሚገኙ እናቶችን እንደምታመለክት ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል።

የኤርምያስ መጽሐፍ በተጻፈበት ጊዜ፣ አሥሩን ነገድ ያቀፈው ሰሜናዊው መንግሥት በአሦራውያን እጅ ወድቆና አብዛኞቹ ሕዝቦቹ በምርኮ ተወስደው ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የኤፍሬም ዝርያዎች ወደ ይሁዳ ክልል ሸሽተው ሊሆን ይችላል። በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን ሁለት ነገዶችን ያቀፈውን የደቡቡን የይሁዳ መንግሥት ድል አደረጉ። ከምርኮኞቹ ብዙዎቹ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በራማ ተሰብስበው ነበር። (ኤር. 40:1) ምናልባትም አንዳንዶቹ የተገደሉት የብንያም ክልል በሆነውና ራሔል በተቀበረችበት በዚህ ስፍራ ሳይሆን አይቀርም። (1 ሳሙ. 10:2) ስለዚህ ራሔል ስለ ልጆቿ እንዳለቀሰች የሚገልጸው ሐሳብ በምሳሌያዊ ሁኔታ በአጠቃላይ ስለ ብንያማውያን ወይም በተለይ በራማ ስለነበሩት ማልቀሷን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ይህ አገላለጽ የአምላክ ሕዝቦች እናቶች በሙሉ፣ ስለሞቱት ወይም በምርኮ ስለተወሰዱት እስራኤላውያን ማልቀሳቸውን የሚያመለክት ይሆናል።

በዚያም ሆነ በዚህ ኤርምያስ፣ ራሔል ስለ ልጆቿ ማልቀሷን አስመልክቶ የተናገረው ሐሳብ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ የሕፃኑ የኢየሱስ ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ በነበረበት ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ የሚገልጽ ትንቢት ነበር። ንጉሥ ሄሮድስ፣ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ በኩል በነበረችው በቤተልሔም የሚገኙ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሚሆኑ ወንድ ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ አውጥቶ ነበር። በመሆኑም እነዚያ ወንዶች ልጆች ስለተገደሉ “የሉም” ሊባል ይችላል። ልጆቻቸው የተገደሉባቸው እናቶች ጩኸትና ለቅሶ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ! ለቅሷቸው ከኢየሩሳሌም በስተ ስሜን በኩል እስከምትገኘው እስከ ራማ ድረስ የተሰማ ያህል ነበር።—ማቴ. 2:16-18

በዚህም ምክንያት ራሔል ስለ ልጆቿ እንዳለቀሰች የሚገልጸው ሐሳብ በኤርምያስም ሆነ በኢየሱስ ዘመን አይሁዳውያን እናቶች ልጆቻቸው በመገደላቸው ምክንያት የደረሰባቸውን ሐዘን የሚጠቁም ተስማሚ መግለጫ ነበር። እርግጥ በሞት በማሸለባቸው፣ “የጠላት ምድር” ወደተባለው ሞት የተጓዙት ሙታን ትንሣኤ ሲያገኙ ከዚያ ጠላት መዳፍ ወጥተው ይመለሳሉ።—ኤር. 31:16፤ 1 ቆሮ. 15:26