መዝሙር 118:1-29

  • ይሖዋ ላስገኘው ድል ምስጋና ማቅረብ

    • ‘ያህን ተጣራሁ፤ እሱም መለሰልኝ’ (5)

    • “ይሖዋ ከጎኔ ነው” (6, 7)

    • የተናቀው ድንጋይ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ይሆናል (22)

    • “በይሖዋ ስም የሚመጣው” (26)

118  ይሖዋ ጥሩ+ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።  2  እስራኤል እንዲህ ይበል፦ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”  3  ከአሮን ቤት የሆኑ እንዲህ ይበሉ፦ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”  4  ይሖዋን የሚፈሩ እንዲህ ይበሉ፦ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”  5  በተጨነቅኩ ጊዜ ያህን* ተጣራሁ፤ያህም መለሰልኝ፤ ደህንነት ወደማገኝበት ስፍራም* አመጣኝ።+  6  ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም።+ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?+  7  ይሖዋ ረዳቴ ሆኖ* ከጎኔ አለ፤+የሚጠሉኝን ሰዎች በድል አድራጊነት እመለከታለሁ።+  8  በሰው ከመታመን ይልቅ፣ይሖዋን መጠጊያ ማድረግ ይሻላል።+  9  በመኳንንት ከመታመን ይልቅ፣ይሖዋን መጠጊያ ማድረግ ይሻላል።+ 10  ብሔራት ሁሉ ከበቡኝ፤እኔ ግን በይሖዋ ስምመከትኳቸው።+ 11  ከበቡኝ፤ አዎ፣ ዙሪያዬን ከበቡኝ፤እኔ ግን በይሖዋ ስምመከትኳቸው። 12  እንደ ንብ ከበቡኝ፤ሆኖም በእሳት እንደተያያዘ ቁጥቋጦ ወዲያውኑ ጠፉ። እኔም በይሖዋ ስምመከትኳቸው።+ 13  እወድቅ ዘንድ በኃይል ተገፋሁ፤*ይሖዋ ግን ረዳኝ። 14  ያህ መጠለያዬና ብርታቴ ነው፤አዳኝም ሆኖልኛል።+ 15  በጻድቃን ድንኳኖች ውስጥ፣የሐሴትና የመዳን* ድምፅ ይሰማል። የይሖዋ ቀኝ እጅ ኃይሉን ያሳያል።+ 16  የይሖዋ ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አለ፤የይሖዋ ቀኝ እጅ ኃይሉን ያሳያል።+ 17  የያህን ሥራዎች አስታውቅ ዘንድበሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም።+ 18  ያህ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጥቶኛል፤+ሆኖም ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም።+ 19  የጽድቅን በሮች ክፈቱልኝ፤+በዚያ ገብቼ ያህን አወድሳለሁ። 20  ይህ የይሖዋ በር ነው። ጻድቃን በዚያ በኩል ይገባሉ።+ 21  መልስ ስለሰጠኸኝናአዳኝ ስለሆንከኝ አወድስሃለሁ።+ 22  ግንበኞች የናቁት ድንጋይየማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ።+ 23  ይህ የይሖዋ ሥራ ነው፤+ለዓይናችንም ድንቅ ነው።+ 24  ይህ ይሖዋ የሠራው ቀን ነው፤በዚህ ቀን እንደሰታለን፤ ሐሴትም እናደርጋለን። 25  ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ እንድታድነን እንለምንሃለን! ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ ድል አቀዳጀን! 26  በይሖዋ ስም የሚመጣው የተባረከ ነው፤+በይሖዋ ቤት ሆነን እንባርካችኋለን። 27  ይሖዋ አምላክ ነው፤ብርሃን ይሰጠናል።+ ቅርንጫፎች በመያዝ ወደ በዓሉ ከሚጓዙት ጋር ተቀላቅላችሁ+እስከ መሠዊያው ቀንዶች+ ድረስ ሂዱ። 28  አንተ አምላኬ ነህ፤ እኔም አወድስሃለሁ፤አምላኬ ሆይ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።+ 29  ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤+ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ወይም “ሰፊ ወደሆነ ስፍራም።”
“ከሚረዱኝ ሰዎች ጋር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“በኃይል ገፋኸኝ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የድል።”
ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።”