በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም ትረዳለህ?’

‘የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም ትረዳለህ?’

“የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው።”—ሉቃስ 24:45

1, 2. ኢየሱስ ከሞት በተነሳበት ዕለት ደቀ መዛሙርቱን ያበረታታቸው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ከሞት የተነሳበት ዕለት ነው። ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም 11 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኝ መንደር እየተጓዙ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ስላላወቁ በቅርቡ በተከሰቱት ነገሮች በጣም አዝነው ነበር። በድንገት ኢየሱስ ወደ እነሱ ቀርቦ አብሯቸው መጓዝ ጀመረ። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን አጽናናቸው። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እሱ በቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን በሚገባ አብራራላቸው።” (ሉቃስ 24:13-15, 27) “ቅዱሳን መጻሕፍትን ግልጽልጽ አድርጎ [ስላስረዳቸው]” ልባቸው እንደ እሳት ሲቃጠል ተሰማቸው።—ሉቃስ 24:32

2 እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት የዚያኑ ዕለት ምሽት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ሐዋርያቱን ሲያገኟቸውም ያጋጠማቸውን ነገሯቸው። እየተነጋገሩ ሳሉም ኢየሱስ ለሁሉም ተገለጠላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን በጣም ተደናገጡ። በልባቸውም ጥርጣሬ አደረ። ታዲያ ኢየሱስ ያበረታታቸው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው” ይላል።—ሉቃስ 24:45

3. ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? ስለ አገልግሎታችን ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበርስ ምን ሊረዳን ይችላል?

3 እንደ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እኛም አንዳንድ ጊዜ በሐዘን እንዋጥ ይሆናል። የጌታ ሥራ የበዛልን ብንሆንም ውጤቱን አለማየታችን ተስፋ አስቆራጭ ሊሆንብን ይችላል። (1 ቆሮ. 15:58) ወይም መጽሐፍ ቅዱስን  የምናስጠናቸው ሰዎች እምብዛም እድገት አያደርጉ ይሆናል። አሊያም ደግሞ እየረዳናቸው ያሉ ሰዎች ለይሖዋ ጀርባቸውን ሊሰጡ ይችላሉ። ታዲያ ስለ አገልግሎታችን ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ምን ማድረግ እንችላለን? በዚህ ረገድ ጠቃሚ ከሆኑት ነገሮች አንዱ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰፍረው የሚገኙትን የኢየሱስ ምሳሌዎች ትርጉም ሙሉ በሙሉ መረዳት ነው። እስቲ ከእነዚህ ምሳሌዎች ሦስቱን በመመርመር ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።

ሌሊት የተኛው ዘሪ

4. ኢየሱስ ሌሊት ስለተኛው ዘሪ የተናገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?

4 ማርቆስ 4:26-29ን አንብብ። ኢየሱስ ሌሊት ስለተኛው ዘሪ የተናገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው፣ የመንግሥቱን አዋጅ ነጋሪዎች በግለሰብ ደረጃ ያመለክታል። ዘሩ ደግሞ ለልበ ቅኖች የሚሰበከውን የመንግሥቱን መልእክት ይወክላል። አንድ ሰው በዕለት ተዕለት ሕይወቱ እንደሚያደርገው ሁሉ ዘሪው “ሌሊት ይተኛል፣ ቀንም ይነሳል።” ዘሩ ከተዘራበት ጊዜ አንስቶ ሰብሉ እስከሚሰበሰብበት ጊዜ ድረስ ያለው የእድገቱ ሂደት የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል። በዚህ ጊዜ ውስጥ “ዘሩ ይበቅልና ያድጋል።” ዘሩ የሚያድገው ‘በራሱ’ ሲሆን እድገቱ የሚከናወነው ደግሞ ቀስ በቀስና ደረጃ በደረጃ ነው። በተመሳሳይም ሰዎች መንፈሳዊ እድገት የሚያደርጉት ቀስ በቀስ እንዲሁም ደረጃ በደረጃ ነው። አንድ ግለሰብ እድገት እያደረገ ሄዶ አምላክን ለማገልገል ልቡ ሲነሳሳ ፍሬ ያፈራል፤ በሌላ አነጋገር ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ ይጠመቃል።

5. ኢየሱስ ሌሊት ስለተኛው ዘሪ የሚገልጸውን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው? “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ [ባላቸው]” ሰዎች ውስጥ የእውነት ዘር እንዲያድግ የሚያደርገው ይሖዋ መሆኑን እንድንገነዘብ ለመርዳት ነው። (ሥራ 13:48፤ 1 ቆሮ. 3:7) እኛ ዘሩን ልንተክል እንዲሁም ልናጠጣ ብንችልም እድገቱን መቆጣጠር ግን አንችልም። ዘሩ እንዲያድግ ማስገደድ ወይም እድገቱን ማፋጠን አንችልም። በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው ሰው ሁሉ፣ እኛም እድገቱ የሚከናወነው እንዴት እንደሆነ አናውቅም። አብዛኛውን ጊዜ የተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችንን ስናከናውን ዘሩ እንዴት እንደሚያድግ ልብ አንልም። ውሎ አድሮ ግን የመንግሥቱ ዘር ፍሬ ሊያፈራ ይችላል። ከዚያም አዲሱ ደቀ መዝሙር በመከሩ ሥራ አብሮን መካፈል ይጀምራል፤ በሥራው ላይ እገዛ ማድረጉ ደግሞ ይጠቅመናል።—ዮሐ. 4:36-38

6. ከመንፈሳዊ እድገት ጋር በተያያዘ ምን መገንዘብ ይኖርብናል?

6 ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው ሰው የሚያደርገው መንፈሳዊ እድገት ከእኛ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ ትሑት መሆናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን እንዲጠመቅ ከመገፋፋት ወይም ከመጫን እንድንቆጠብ ያደርገናል። አንድን ሰው ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ ራስን ለይሖዋ የመወሰኑ ጉዳይ ግን ሙሉ በሙሉ ለግለሰቡ የተተወ እንደሆነ ማመን ይኖርብናል። አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ የሚወስነው ለአምላክ ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ ነው። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው እንዲህ ያለው ውሳኔ ብቻ ነው።—መዝ. 51:12 NW፤ መዝ. 54:6፤ 110:3

7, 8. (ሀ) ኢየሱስ ሌሊት ስለተኛው ዘሪ ከተናገረው ምሳሌ ምን ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን? ምሳሌ ስጥ። (ለ) ይህ ምሳሌ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?

7 በሁለተኛ ደረጃ፣ የዚህን ምሳሌ ትርጉም መረዳታችን የሥራችንን ውጤት ቶሎ ባናይ ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። በዚህ ረገድ ትዕግሥተኛ መሆን ይኖርብናል። (ያዕ. 5:7, 8) ዘሩ ፍሬ ባያፈራም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችንን ለመርዳት የተቻለንን ያህል ጥረት እስካደረግን ድረስ የእኛ ታማኝነት የሚለካው በሚገኘው ውጤት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልገናል። ይሖዋ የእውነት ዘር ፍሬ እንዲያፈራ የሚያደርገው፣ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ በሆኑ ትሑት ሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ ነው። (ማቴ. 13:23) በመሆኑም የአገልግሎታችንን ስኬት በምናገኘው ውጤት ብቻ መለካት  የለብንም። ይሖዋ የአገልግሎታችንን ውጤታማነት የሚመዝነው የምናስተምራቸው ሰዎች በሚሰጡት ምላሽ አይደለም። የምናገኘው ውጤት ምንም ይሁን ምን ይሖዋ በታማኝነት የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ሉቃስ 10:17-20ን እና 1 ቆሮንቶስ 3:8ን አንብብ።

8 በሦስተኛ ደረጃ፣ ምሳሌው ሰዎች የሚያደርጉትን ለውጥ የምናስተውለው ሁልጊዜ አለመሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ከአንድ ሚስዮናዊ ጋር ያጠኑ የነበሩ ባልና ሚስትን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እነዚህ ባልና ሚስት ያልተጠመቁ አስፋፊዎች መሆን እንደሚፈልጉ ለአስጠኚያቸው ይነግሩታል። እሱም ለአስፋፊነት ብቁ እንዲሆኑ ማጨሳቸውን ማቆም እንዳለባቸው ገለጸላቸው። ባልና ሚስቱ ማጨስ ካቆሙ የተወሰኑ ወራት እንዳለፋቸው ሲነግሩት ሚስዮናዊው በጣም ተገረመ። ማጨስ ያቆሙት ለምንድን ነው? ይሖዋ ሲያጨሱ እንደሚመለከታቸውና ግብዝነትን እንደሚጠላ በመገንዘባቸው ነበር። በመሆኑም እነዚህ ባልና ሚስት ውሳኔ ማድረግ እንዳለባቸው ተሰማቸው፤ የሚያጨሱ ከሆነ በሚስዮናዊው ፊትም ቢሆን ማጨስ፣ ካልሆነ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማቆም እንዳለባቸው አሰቡ። ለይሖዋ ፍቅር ማዳበራቸው ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። ሚስዮናዊው ባያስተውለውም እንኳ እነዚህ ባልና ሚስት መንፈሳዊ እድገት አድርገው ነበር።

መረቡ

9. የመረቡ ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?

9 ማቴዎስ 13:47-50ን አንብብ። ኢየሱስ ስለ መረቡ የተናገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? ኢየሱስ የመንግሥቱ መልእክት ለሰው ዘር ጠቅላላ መሰበኩን፣ መረቡ ወደ ባሕር ከመጣሉ ጋር አመሳስሎታል። መረቡ፣ ዓሦችን ሳይመርጥ ከፍተኛ መጠን ያለው “የተለያየ ዓይነት ዓሣ” እንደሚይዝ ሁሉ የስብከቱ ሥራችንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተለያዩ ዓይነት ሰዎችን ይስባል። (ኢሳ. 60:5) በትላልቅ ስብሰባዎችና በየዓመቱ በሚከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለዚህ ማስረጃ ይሆናሉ። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደ “ጥሩ” ዓሣ በመሆናቸው ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እየተሰበሰቡ ነው። ሌሎቹ ግን ‘እንደማይፈለገው’ ዓሣ ናቸው፤ በመረቡ ከተሰበሰቡት መካከል በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙት ሁሉም አይደሉም።

ማቴዎስ 13:47-50ን ካነበብክ በኋላ . . .

10. ኢየሱስ ስለ መረቡ የሚገልጸውን ምሳሌ የተናገረው ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው? በምሳሌው ላይ የተገለጸው ዓሦቹን የመለየቱ ሥራ የሚያመለክተው በታላቁ መከራ ወቅት የሚሰጠውን የመጨረሻ ፍርድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ምን እንደሚከናወን ያመለክታል። ኢየሱስ፣ እውነት ከሳባቸው ሰዎች መካከል ከይሖዋ ጎን የሚቆሙት ሁሉም እንዳልሆኑ ለማሳየት ሲል በዚህ ምሳሌ ተጠቅሟል። ብዙ ሰዎች በስብሰባዎቻችን ላይ ይገኛሉ። ሌሎች ደግሞ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ቢያጠኑም እርምጃ መውሰድ አይፈልጉም። (1 ነገ. 18:21) ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መምጣታቸውን ያቆሙ ሰዎችም አሉ። ወላጆቻቸው ክርስቲያኖች የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ለይሖዋ መሥፈርቶች ፍቅር አላዳበሩም። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎችን ይሖዋ ‘የሕዝቦች ሀብት’ እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ሐጌ 2:7

. . . በዘመናችን እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ለማስተዋል ሞክር

11, 12. (ሀ) ስለ መረቡ ከሚገልጸው ምሳሌ ምን ጥቅም እናገኛለን? (ለ) ይህ ምሳሌ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?

11 ስለ መረቡ ከሚገልጸው ምሳሌ ምን ጥቅም እናገኛለን? የዚህን ምሳሌ ትርጉም መረዳታችን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን ማጥናት ቢያቆም ወይም ልጃችን እውነትን ሳይቀበል ቢቀር ከልክ በላይ እንዳናዝን አሊያም ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ብናደርግም እንኳ የምንፈልገውን ውጤት ላናገኝ እንችላለን። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ስለተስማማ ወይም በእውነት ውስጥ ስላደገ ብቻ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ የሆነ ዝምድና ይመሠርታል ማለት አይደለም። የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሁሉ ውሎ አድሮ ከሕዝቡ መካከል መለየታቸው አይቀርም።

እውነት ከሳባቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ከይሖዋ ጎን ይቆማሉ (ከአንቀጽ 9-12ን ተመልከት)

 12 እንዲህ ሲባል ታዲያ እውነትን የተዉ ሰዎች በሙሉ ወደ ጉባኤው እንዲመለሱ ፈጽሞ አይፈቀድላቸውም ማለት ነው? ወይም ደግሞ አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ ከመወሰን ወደኋላ ቢል ‘ከማይፈለጉት’ ዓሦች ተመድቦ ይቀራል ማለት ነው? በጭራሽ። እንዲህ ያሉት ሰዎች ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ለመመለስ የሚያስችል አጋጣሚ አላቸው። ይሖዋ፣ እንዲህ ያሉትን ሰዎች “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” በማለት የጋበዛቸው ያህል ነው። (ሚል. 3:7) ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ሌላው ምሳሌ ይህን እውነታ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ሉቃስ 15:11-32ን አንብብ።

አባካኙ ልጅ

13. ስለ አባካኙ ልጅ የሚናገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው?

13 ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ምሳሌ ትርጉም ምንድን ነው? በዚህ ምሳሌ ላይ የተገለጸው ሩኅሩኅ አባት በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችንን ይሖዋን ያመለክታል። ከአባቱ ንብረት ድርሻው እንዲሰጠው የጠየቀውና በኋላም ንብረቱን ያባከነው ልጅ ደግሞ ከጉባኤ ርቀው የሚባዝኑትን የአምላክ አገልጋዮች ይወክላል። እነዚህ ሰዎች ጉባኤውን ትተው በመሄዳቸው “ወደ ሩቅ አገር” ይኸውም ከይሖዋ ወደራቀው የሰይጣን ዓለም የተጓዙ ያህል ነው። (ኤፌ. 4:18፤ ቆላ. 1:21) ከጊዜ በኋላ ግን አንዳንዶቹ ወደ ልቦናቸው የተመለሱ ሲሆን እንደገና ወደ ይሖዋ ድርጅት መመለስ አስቸጋሪ ቢሆንም ይህንን አድርገዋል። ይቅር ባይ የሆነው አባታችን ይሖዋም ንስሐ የገቡትን እነዚህን ትሑት ሰዎች ሞቅ ባለ ስሜት ተቀብሏቸዋል።—ኢሳ. 44:22፤ 1 ጴጥ. 2:25

14. ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው?

14 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ለምንድን ነው? ይሖዋ፣ የባዘኑ አገልጋዮቹ ወደ እሱ እንዲመለሱ እንደሚፈልግ ኢየሱስ ማራኪ በሆነ መንገድ ገልጿል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው አባት፣ ልጁ እንደሚመለስ ምንጊዜም ተስፋ ያደርግ ነበር። ይህ አባት፣ ልጁ ወደ እሱ እየመጣ እንደሆነ ሲመለከት ልጁ “ገና ሩቅ” እያለም እንኳ እሱን ለመቀበል ፈጣን እርምጃ ወስዷል። ይህ፣ እውነትን የተዉ ሰዎች ሳይዘገዩ ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ የሚያነሳሳ እንዴት ያለ ግሩም ማበረታቻ ነው! እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ ዝለው ይሆናል፤ ወደ ጉባኤ ተመልሶ መምጣትም የሚያሳፍርና ከባድ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። ሆኖም እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስቆጭ አይደለም፤ እነሱ ሲመለሱ በሰማይ እንኳ ታላቅ ደስታ ይሆናል።—ሉቃስ 15:7

15, 16. (ሀ) ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ ከተናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ምሳሌ ስጥ። (ለ) ይህ ምሳሌ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?

15 ስለ አባካኙ ልጅ ከሚገልጸው ምሳሌ ምን ጥቅም እናገኛለን? የይሖዋን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። “እጅግ ጻድቅ” መሆንና ንስሐ የገቡ  ኃጢአተኞችን ለመቀበል እንቢተኞች መሆን የለብንም። እንዲህ ማድረግ በእኛ ላይ መንፈሳዊ ‘ጥፋት’ ከማስከተል ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። (መክ. 7:16) ከዚህ ምሳሌ ሌላም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ጉባኤውን ትቶ የሄደን ወንድም “እንደ ጠፋ በግ” እንጂ ጨርሶ ሊመለስ እንደማይችል ሰው አድርገን መቁጠር የለብንም። (መዝ. 119:176) ታዲያ ከጉባኤ ርቆ የባዘነ ሰው ብናገኝ ግለሰቡ መመለስ እንዲችል ፍቅር የሚንጸባረቅበትና ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ለመስጠት እንጥራለን? ሽማግሌዎች ተገቢውን እርዳታ እንዲሰጡት ጉዳዩን ወዲያውኑ እናሳውቃቸዋለን? ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ምሳሌ የያዘውን ትምህርት ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ እንዲህ ዓይነት እርምጃ እንወስዳለን።

16 በዘመናችን የሚገኙ እንደ አባካኙ ልጅ የሆኑ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ ምሕረት እንዲሁም ጉባኤው ላሳያቸው ፍቅርና ላደረገላቸው ድጋፍ አድናቆታቸውን እንዴት እንደገለጹ እንመልከት። ለ25 ዓመታት ተወግዶ የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ጉባኤ ከተመለስኩ በኋላ ከይሖዋ ‘የመታደስ ዘመን’ ስላገኘሁ ደስታዬ እየጨመረ ሄዷል። (ሥራ 3:19) የሁሉም ሰው ድጋፍና ፍቅር አልተለየኝም! አሁን ግሩም የሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ አለኝ።” ለአምስት ዓመታት ያህል ከይሖዋ ርቃ የነበረች አንዲት ወጣት እህት ወደ ጉባኤ መመለሷ ያሳደረባትን ስሜት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “[ወንድሞች] ኢየሱስ የተናገረለትን ዓይነት ፍቅር ሲያሳዩኝ ምን እንደተሰማኝ መግለጽ ያቅተኛል። የይሖዋ ድርጅት አባል መሆን በዋጋ ሊተመን የማይችል ነገር ነው!”

17, 18. (ሀ) እስካሁን ከመረመርናቸው ሦስት ምሳሌዎች ምን ትምህርት አግኝተናል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

17 ከእነዚህ ሦስት ምሳሌዎች ምን ትምህርት አግኝተናል? በመጀመሪያ፣ ሰዎች መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አለማድረጋቸው ከእኛ ቁጥጥር ውጭ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ይህ እንዲሆን የሚያደርገው ይሖዋ ነው። ሁለተኛ፣ ከእኛ ጋር የሚሰበሰቡም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሰዎች በሙሉ ለእውነት አቋም ይወስዳሉ ብለን መጠበቅ የለብንም። በመጨረሻም፣ አንዳንዶች እውነትን ቢተዉና ለይሖዋ ጀርባቸውን ቢሰጡም ወደ ይሖዋ አይመለሱም ብለን መደምደም የለብንም። እነዚህ ሰዎች ከተመለሱ ደግሞ የይሖዋን አመለካከት በሚያንጸባርቅ መንገድ እንቀበላቸው።

18 እንግዲያው ሁላችንም እውቀትን፣ ማስተዋልንና ጥበብን መፈለጋችንን እንቀጥል። ኢየሱስ የሰጣቸውን ምሳሌዎች ስናነብ እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን እንጠይቅ፦ ትርጉማቸው ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገቡት ለምንድን ነው? ከምሳሌዎቹ የምናገኘውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌዎቹስ ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምሩናል? እንዲህ ማድረጋችን በእርግጥም ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ትርጉም እንደተረዳን ያሳያል።