በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑራችሁ

በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑራችሁ

“እምነት ተስፋ የተደረጉ ነገሮችን በእርግጠኝነት መጠበቅ . . . ነው።”—ዕብ. 11:1

1, 2. አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ መንግሥቱ እንደሚፈጽም ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ምንድን ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ብዙ ጊዜ እንናገራለን፤ እንዲሁም ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ይህንን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ሰዎች እንዲያውቁ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። እኛም የአምላክ መንግሥት ወደፊት በሚያመጣቸው ነገሮች በጣም እንጽናናለን። ይሁንና ይህ መንግሥት የታሰበለትን ዓላማ የሚያሳካ እውን መስተዳድር እንደሆነ ያለን እምነት ምን ያህል ጠንካራ ነው? በመንግሥቱ ላይ የማይናወጥ እምነት እንዲኖረን የሚያደርግ ምን መሠረት አለን?—ዕብ. 11:1

2 መሲሐዊው መንግሥት፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከፍጥረታቱ ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ ለመፈጸም ያደረገው ዝግጅት ነው። ይህ መንግሥት የማይናወጥ መሠረት አለው፤ መሠረቱ ይሖዋ ያለው የመግዛት መብት ነው። ዓቢይ የሆኑ የመንግሥቱ ገጽታዎች ለምሳሌ ንጉሡ፣ ተባባሪ ገዢዎቹና ግዛታቸው በቃል ኪዳኖች ማለትም ሕጋዊ በሆኑ ውሎች ወይም ስምምነቶች አማካኝነት ጸንተዋል፤ እነዚህን ቃል ኪዳኖች ያደረጉት አካላት ይሖዋ አሊያም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ናቸው። በእነዚህ ቃል ኪዳኖች ላይ ማሰላሰላችን የአምላክ ዓላማ በእርግጥ  እንደሚፈጸምና መንግሥቱ በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል።ኤፌሶን 2:12ን አንብብ።

3. በዚህ እና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሚመራው መሲሐዊ መንግሥት ጋር የተያያዙ ስድስት ዋና ዋና ቃል ኪዳኖችን ይጠቅሳል። እነዚህም (1) የአብርሃም ቃል ኪዳን፣ (2) የሕጉ ቃል ኪዳን፣ (3) የዳዊት ቃል ኪዳን፣ (4) እንደ መልከጼዴቅ ያለው የክህነት ቃል ኪዳን፣ (5) አዲሱ ቃል ኪዳን እና (6) የመንግሥቱ ቃል ኪዳን ናቸው። እያንዳንዱ ቃል ኪዳን ከመንግሥቱ ጋር የሚያያዘው እንዲሁም አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ እንዲፈጸም አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።—“ አምላክ ዓላማውን የሚፈጽምበት መንገድ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

የአምላክ ዓላማ እንዴት እንደሚፈጸም የሚገልጥ ተስፋ

4. በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ከሰዎች ጋር በተያያዘ የትኞቹን አዋጆች ተናግሯል?

4 ይሖዋ፣ ለሰው ልጆች ውብ መኖሪያ የሆነችውን ምድርን ካዘጋጀ በኋላ ከሰዎች ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ሦስት አዋጆች ተናገረ፦ (1) አምላካችን ሰዎችን በመልኩ እንደሚፈጥር፣ (2) ሰዎች መላዋን ምድር ወደ ገነትነት እንደሚቀይሯትና ምድርን ጻድቅ በሆኑ ዘሮቻቸው እንደሚሞሏት እንዲሁም (3) ሰዎች መልካምንና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ እንዳይበሉ መከልከላቸውን ገለጸ። (ዘፍ. 1:26, 28፤ 2:16, 17) ከዚህ ሌላ የሚያስፈልግ ነገር አልነበረም። ሰው ከተፈጠረ በኋላ የአምላክ ዓላማ እውን እንዲሆን የሚቀረው ነገር ሁለቱ አዋጆች መፈጸማቸው ብቻ ነበር። ታዲያ ቃል ኪዳኖች ያስፈለጉት ለምንድን ነው?

5, 6. (ሀ) ሰይጣን የአምላክን ዓላማ ለማክሸፍ የሞከረው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን በኤደን ላስነሳው ግድድር ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ?

5 ሰይጣን ዲያብሎስ፣ የአምላክን ዓላማ ለማክሸፍ በማሴር በአምላክ ላይ ዓመፅ አስነሳ። ይህንንም ያደረገው፣ አምላክ ከተናገራቸው አዋጆች መካከል በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያደርግበት የሚችለውን ይኸውም ሰዎች ታዛዥ እንዲሆኑ የሚጠይቅባቸውን አዋጅ በመጠቀም ነው። የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን፣ መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ እንዳይበሉ የተሰጣቸውን መመሪያ እንድትጥስ ገፋፋት። (ዘፍ. 3:1-5፤ ራእይ 12:9) በዚህ መንገድ ሰይጣን፣ አምላክ በፍጡራኑ ላይ ለመግዛት ያለውን መብት ተገዳደረ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰይጣን፣ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች እሱን የሚያመልኩት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነ ገለጸ።—ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5

6 ታዲያ ሰይጣን በኤደን ላስነሳው ግድድር ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ? ዓመፀኞቹን ቢያጠፋቸው ዓመፁን ማስቆም እንደሚችል ጥያቄ የለውም። ይህን ቢያደርግ ኖሮ ግን ምድርን ታዛዥ በሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ለመሙላት ያለው ዓላማ ሳይፈጸም ይቀር ነበር። ጠቢብ የሆነው ፈጣሪ፣ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ከማጥፋት ይልቅ ትልቅ ትርጉም ያለውን አንድ ትንቢት ይኸውም የኤደኑን ተስፋ ተናገረ፤ ይህ ተስፋ አምላክ የተናገረው ነገር በሙሉ አንድም ሳይቀር እንዲፈጸም ያደርጋል።ዘፍጥረት 3:15ን አንብብ።

7. በኤደን የተሰጠው ተስፋ እባቡንና ዘሩን በተመለከተ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

7 ይሖዋ የኤደኑን ተስፋ ሲሰጥ፣ በእባቡና በዘሩ ይኸውም በሰይጣን ዲያብሎስና ከአምላክ የመግዛት መብት ጋር በተያያዘ በተነሳው ጉዳይ ረገድ ከሰይጣን ጎን በሚቆሙ ሁሉ ላይ ፍርድ አስተላለፈ። እውነተኛው አምላክ፣ ሰይጣንን የማጥፋት ሥልጣን የሰጠው ለሴቲቱ ዘር ነው። በመሆኑም በኤደን የተሰጠው ተስፋ፣ በገነት ውስጥ የተነሳው ዓመፅና ከዚያ ጋር ተያይዘው የመጡት መዘዞች ጠንሳሽ እንደሚጠፋ ብቻ ሳይሆን ይህ የሚሆንበትን መንገድም ጭምር ጠቁሟል።

8. ስለ ሴቲቱ እና ስለ ዘሯ ምን ማለት ይቻላል?

8 ታዲያ የሴቲቱ ዘር የሚሆነው ማን ነው?  የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ እንደሚቀጠቅጠው በሌላ አባባል መንፈሳዊ ፍጡር የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን ‘እንዳልነበረ እንደሚያደርገው’ ስለተነገረ ዘሩ መንፈሳዊ ፍጡር መሆን አለበት። (ዕብ. 2:14) ይህ ከሆነ ደግሞ ዘሩን የምትወልደው ሴትም መንፈሳዊ መሆን አለባት። ይሖዋ የኤደኑን ተስፋ ከሰጠ በኋላ የእባቡ ዘሮች እየበዙ ቢሄዱም የሴቲቱና የዘሯ ማንነት ወደ 4,000 ለሚጠጉ ዓመታት ያህል ሚስጥር ሆኖ ነበር። በዚህ መሃል ይሖዋ፣ የዘሩን ማንነት የሚጠቁሙና ሰይጣን በሰው ዘር ቤተሰብ ላይ ያመጣውን መከራ ለማስወገድ አምላክ የሚጠቀመው በዚህ ዘር እንደሆነ ለአገልጋዮቹ የሚያሳውቁ የተለያዩ ቃል ኪዳኖችን ገብቷል።

የዘሩን ማንነት ግልጽ ያደረገ ቃል ኪዳን

9. የአብርሃም ቃል ኪዳን ምንድን ነው? ይህ ቃል ኪዳን የጸናው መቼ ነው?

9 ይሖዋ፣ በሰይጣን ላይ ፍርድ ካስተላለፈ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በኋላ አብርሃምን በሜሶጶጣሚያ ባለው በዑር ከሚገኘው ቤቱ ወጥቶ ወደ ከነዓን ምድር እንዲሄድ አዘዘው። (ሥራ 7:2, 3) ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤት ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ። ‘ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎች በረከት ትሆናለህ። የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህን እረግማለሁ፤ በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣ በአንተ አማካይነት ይባረካሉ።’” (ዘፍ. 12:1-3) የአብርሃም ቃል ኪዳን ማለትም ይሖዋ አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ሰፍሮ የሚገኘው እዚህ ዘገባ ላይ ነው። ይሖዋ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳኑን መጀመሪያ የገባው መቼ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሆኖም ቃል ኪዳኑ የጸናው አብርሃም በ75 ዓመቱ ከካራን ወጥቶ የኤፍራጥስን ወንዝ በተሻገረ ጊዜ ይኸውም በ1943 ዓ.ዓ. ነው።

10. (ሀ) አብርሃም በአምላክ ተስፋዎች ላይ የማይናወጥ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ፣ ስለ ሴቲቱ ዘር የትኞቹን ዝርዝር ጉዳዮች ገልጧል?

 10 ይሖዋ ለአብርሃም የገባለትን ቃል በተለያየ ጊዜ የደገመለት ሲሆን ተጨማሪ ዝርዝር ሐሳቦችንም ነግሮታል። (ዘፍ. 13:15-17፤ 17:1-8, 16) አብርሃም ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆን በአምላክ ተስፋዎች ላይ የማይናወጥ እምነት እንዳለው ባሳየ ጊዜ ይሖዋ በመሃላ ቃል ኪዳኑን አጠናከረው፤ ይህም አምላክ ቃሉን እንደሚፈጽም ለአብርሃም አረጋግጦለታል። (ዘፍጥረት 22:15-18ን እና ዕብራውያን 11:17, 18ን አንብብ።) የአብርሃም ቃል ኪዳን ከጸና በኋላ ይሖዋ፣ ስለ ሴቲቱ ዘር የሚገልጹ አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን በተለያዩ ጊዜያት ተናግሯል። ዘሩ በአብርሃም የዘር ሐረግ እንደሚመጣ፣ ብዙዎችን እንደሚያመለክት፣ ንጉሣዊ ሥልጣን እንደሚኖረው፣ ጠላቶቹን በሙሉ እንደሚያጠፋና ለብዙዎች በረከት እንደሚሆን ተገልጿል።

አብርሃም በአምላክ ተስፋዎች ላይ የማይናወጥ እምነት እንዳለው አሳይቷል (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

11, 12. ቅዱሳን መጻሕፍት የአብርሃም ቃል ኪዳን ታላቅ ፍጻሜ እንዳለው የሚያሳዩት እንዴት ነው? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?

11 የአብርሃም ዘሮች ተስፋይቱን ምድር ሲወርሱ የአብርሃም ቃል ኪዳን የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል፤ ያም ቢሆን ይህ ቃል ኪዳን በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍጻሜ እንዳለው ቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቁማሉ። (ገላ. 4:22-25) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዳብራራው የአብርሃም ቃል ኪዳን ታላቅ ፍጻሜውን በሚያገኝበት ጊዜ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል የሚሆነው ክርስቶስ ሲሆን የዘሩ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ በመንፈስ የተቀቡ 144,000 ክርስቲያኖች ናቸው። (ገላ. 3:16, 29፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 4) ዘሩን የምታስገኘው ሴት “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም” ይኸውም ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን የምታቅፈው የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ናት። (ገላ. 4:26, 31) በአብርሃም ቃል ኪዳን ላይ በተሰጠው ተስፋ መሠረት የሴቲቱ ዘር ለሰው ልጆች በረከት ያመጣል።

12 የአብርሃም ቃል ኪዳን በሰማይ መንግሥት እንደሚቋቋም ሕጋዊ ዋስትና ሆኗል፤ እንዲሁም ንጉሡና ተባባሪ ገዢዎቹ ይህን መንግሥት እንዲወርሱ መንገድ ከፍቷል። (ዕብ. 6:13-18) ይህ ቃል ኪዳን ጸንቶ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ዘፍጥረት 17:7 ‘የዘላለም ኪዳን’ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ቃል ኪዳን፣ መሲሐዊው መንግሥት የአምላክን ጠላቶች እስኪያጠፋና የምድር ሕዝቦች በሙሉ እስኪባረኩ ድረስ ጸንቶ ይቆያል። (1 ቆሮ. 15:23-26) በዚያ ወቅት በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ዘላለማዊ በረከት ያገኛሉ። አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን፣ ይሖዋ ጻድቅ የሆኑ የሰው ልጆች ‘ምድርን እንዲሞሏት’ ያለው ዓላማ መፈጸሙ እንደማይቀር ያረጋግጣል።—ዘፍ. 1:28

መንግሥቱ ዘላለማዊ እንደሚሆን የሚያረጋግጥ ቃል ኪዳን

13, 14. የዳዊት ቃል ኪዳን የመሲሑን አገዛዝ በተመለከተ ምን ያረጋግጥልናል?

13 የኤደኑ ተስፋ እና የአብርሃም ቃል ኪዳን አንድ ዓቢይ ቁም ነገር ያጎላሉ፤ ይኸውም በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት የተገለጸው የይሖዋ ሉዓላዊነት ወይም አገዛዙ ምንጊዜም በጽድቅ መሥፈርቶቹ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያሳያሉ። (መዝ. 89:14) መሲሐዊው መንግሥት ምግባረ ብልሹ በመሆኑ ምክንያት መወገድ ሊያስፈልገው ይችላል? ይህ ፈጽሞ እንደማይሆን የሚያሳይ ሌላ ሕጋዊ ቃል ኪዳን አለ።

14 የዳዊትን ቃል ኪዳን ይኸውም ይሖዋ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት የገባለትን ቃል እንመልከት። (2 ሳሙኤል 7:12, 16ን አንብብ።) ይሖዋ ከዳዊት ጋር ይህን ቃል ኪዳን ያደረገው ዳዊት በኢየሩሳሌም ንጉሥ በነበረበት ወቅት ሲሆን መሲሑ በእሱ ዘር በኩል እንደሚመጣ ቃል ገብቶለታል። (ሉቃስ 1:30-33) በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ ዘሩ የሚመጣበትን መስመር ይበልጥ ግልጽ አደረገ፤ በተጨማሪም የዳዊት ወራሽ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ ለመሆን “የሚገባው ባለ መብት” ይሆናል።  (ሕዝ. 21:25-27) በኢየሱስ አማካኝነት የዳዊት ንግሥና “ለዘላለም የጸና ይሆናል።” በእርግጥም የዳዊት ዘር “ለዘላለም፣ ዙፋኑም . . . እንደ ፀሓይ ጸንቶ ይኖራል።” (መዝ. 89:34-37) አዎን፣ የመሲሑ አገዛዝ መቼም ቢሆን ምግባረ ብልሹ አይሆንም፤ ያከናወናቸው ነገሮችም ቢሆኑ ዘላለማዊ ይሆናሉ!

የክህነት አገልግሎት እንዲኖር የሚያደርግ ቃል ኪዳን

15-17. እንደ መልከጼዴቅ ባለው የክህነት ቃል ኪዳን መሠረት ዘሩ ምን ተጨማሪ ኃላፊነት ይኖረዋል? ለምንስ?

15 የአብርሃም ቃል ኪዳንና የዳዊት ቃል ኪዳን የሴቲቱ ዘር ንጉሥ እንደሚሆን በግልጽ የሚያሳዩ ቢሆንም ይህ ብቻ ለሰው ዘሮች በሙሉ በረከት ለማምጣት በቂ አይሆንም። የሰው ዘሮች የተሟላ በረከት እንዲያገኙ ከኃጢአታቸው ነፃ ወጥተው ከይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ጋር አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ዘሩ የክህነት አገልግሎትም መስጠት አለበት። ጠቢብ የሆነው ፈጣሪ ይህን ለማስፈጸም ሲል እንደ መልከጼዴቅ ያለ የክህነት ቃል ኪዳን በመግባት ሌላ ሕጋዊ ዝግጅት አድርጓል።

16 ይሖዋ፣ ሁለት ዓላማዎች ያሉት ቃል ኪዳን ከኢየሱስ ጋር እንደሚገባ በንጉሥ ዳዊት በኩል ተናግሯል፦ አንደኛው ዓላማ ኢየሱስ በጠላቶቹ መካከል እስኪገዛ ድረስ በአምላክ ‘ቀኝ መቀመጡ’ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት . . . ለዘላለም ካህን” መሆኑ ነው። (መዝሙር 110:1, 2, 4ን አንብብ።) “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት” የተባለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአብርሃም ዘሮች ተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የሳሌም ንጉሥ የሆነው መልከጼዴቅ “የልዑሉ አምላክ ካህን” ሆኖ ያገለግል ነበር። (ዕብ. 7:1-3) መልከጼዴቅ እንዲህ እንዲያደርግ በቀጥታ የሾመው ይሖዋ ነው። ንጉሥና ካህን ሆኖ እንዳገለገለ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው ሰው እሱ ብቻ ነው። በተጨማሪም ከእሱ በፊትም ሆነ ከእሱ በኋላ እንዲህ ያለ ቦታ የነበረው ሰው መኖሩ ስላልተገለጸ “ለዘላለም ካህን” ሊባል ይችላል።

17 ኢየሱስ ካህን ሆኖ የተሾመው ከይሖዋ ጋር በገባው በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት ነው፤ እንዲሁም “በመልከጼዴቅ ሥርዓት መሠረት . . . ለዘላለም ካህን” ይሆናል። (ዕብ. 5:4-6) ይህ በግልጽ እንደሚያሳየው ይሖዋ፣ ለምድርና ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ለማድረግ ሲል በመሲሐዊው መንግሥት እንደሚጠቀም ሕጋዊ ማረጋገጫ ሰጥቷል።

መንግሥቱ በሕጋዊ ቃል ኪዳኖች ላይ የተመሠረተ ነው

18, 19. (ሀ) እስካሁን የተመለከትናቸው ቃል ኪዳኖች ስለ መንግሥቱ ምን ያስገነዝቡናል? (ለ) የትኛው ጥያቄ ይነሳል?

18 ቀደም ሲል ያየናቸው ቃል ኪዳኖች ከመሲሐዊው መንግሥት ጋር የሚያያዙት እንዴት እንደሆነና መንግሥቱ በሕጋዊ ውሎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተገንዝበናል። በኤደን የተሰጠው ተስፋ ይሖዋ፣ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ በሴቲቱ ዘር አማካኝነት እንደሚፈጽም ያረጋግጣል። ይህ ዘር ማን ነው? የትኞቹን ሥራዎችስ ያከናውናል? የአብርሃም ቃል ኪዳን ለዚህ መልስ ሰጥቶናል።

19 የዳዊት ቃል ኪዳን ደግሞ የዘሩ ዋነኛ ክፍል የሚመጣበትን የዘር ሐረግ በግልጽ ያሳያል፤ በተጨማሪም ይህ ቃል ኪዳን፣ ዘሩ በምድር ላይ የመግዛት መብት እንዲኖረውና መንግሥቱ የሚያከናውናቸው ነገሮች ለዘላለም ጸንተው መቀጠል እንዲችሉ ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መልከጼዴቅ ያለው የክህነት ቃል ኪዳን፣ ዘሩ ካህን ሆኖ ማገልገል እንዲችል መሠረት ሆኗል። ኢየሱስ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና የሚያደርሰው ግን ብቻውን አይደለም። ነገሥታትና ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ የተሾሙ ሌሎችም አሉ። ይህ ኃላፊነት የሚሰጣቸው እነማን ናቸው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።