በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአመስጋኝነት ተቀበሉ​—በሙሉ ልባችሁ ስጡ

በአመስጋኝነት ተቀበሉ​—በሙሉ ልባችሁ ስጡ

በአመስጋኝነት ተቀበሉ​—በሙሉ ልባችሁ ስጡ

በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል። የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በሙሉ በጥልቅ እንደሚያስብ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ጴጥ. 5:7) ይሖዋ ለእኛ እንደሚያስብ ከሚያሳይባቸው መንገዶች አንዱ እሱን በታማኝነት ማገልገል እንድንችል የሚያስፈልጉንን ነገሮች በተለያየ መልኩ ማቅረቡ ነው። (ኢሳ. 48:17) በተለይ ደግሞ ከባድ ችግር በሚያጋጥመን ወቅት ይሖዋ እርዳታ እንድናገኝ ባደረጋቸው ዝግጅቶች እንድንጠቀም ይፈልጋል። የሙሴ ሕግ ይህንን እውነታ ያጎላል።

ይሖዋ ወላጅ የሌላቸው ልጆች፣ መበለቶች፣ መጻተኞችና “ድኾች” የሆኑ ሌሎች ሰዎች እርዳታ የሚያገኙበት ፍቅራዊ ዝግጅት በሙሴ ሕግ ውስጥ እንዲካተት አድርጎ ነበር። (ዘሌ. 19:9, 10፤ ዘዳ. 14:29) አምላክ ከአገልጋዮቹ መካከል አንዳንዶቹ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃል። (ያዕ. 1:27) ይሖዋ አንዳንዶች ለሌሎች እርዳታ እንዲሰጡ ሊያነሳሳቸው ይችላል፤ በመሆኑም ከአገልጋዮቹ መካከል ማናቸውም ቢሆኑ እንዲህ ያለውን ድጋፍ ለመቀበል ማቅማማት የለባቸውም። ያም ቢሆን ግን እርዳታ ስንቀበል ተገቢ አመለካከት ሊኖረን ይገባል።

በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ሕዝቦች መስጠት የሚችሉበት አጋጣሚም እንዳላቸው ይናገራል። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ስለተመለከታት “ድሃ መበለት” የሚናገረውን ዘገባ አስታውስ። (ሉቃስ 21:1-4) ይህች ሴት በሕጉ ውስጥ ይሖዋ ለመበለቶች ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት ልትጠቀም እንደምትችል ጥርጥር የለውም። ይህች መበለት ድሃ ብትሆንም የምትታወሰው እርዳታ በመቀበሏ ሳይሆን በመስጠቷ ነው። እንዲህ ያለ የሰጪነት መንፈስ ማሳየቷ ደስታ እንዳስገኘላት የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (ሥራ 20:35) ታዲያ “ሰጪ” መሆን እንዲሁም መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም የምትችለው እንዴት ነው?—ሉቃስ 6:38

‘ለይሖዋ ምን ልክፈለው?’

መዝሙራዊው “ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ . . . [“ለይሖዋ፣” NW] ምን ልክፈለው?” በማለት ጠይቋል። (መዝ. 116:12) ይሖዋ ለመዝሙራዊው የዋለለት ውለታ ምንድን ነው? ይህ የአምላክ አገልጋይ “ጭንቅና ሐዘን” ባጋጠመው ወቅት ይሖዋ ደግፎ አቁሞታል። እንዲሁም ‘ነፍሱን ከሞት አድኖለታል።’ በመሆኑም መዝሙራዊው፣ አንድ ነገር በማድረግ የይሖዋን ውለታ ‘መክፈል’ ፈልጓል። ታዲያ ምን ማድረግ ይችላል? ‘ስእለቴን ለይሖዋ እፈጽማለሁ’ በማለት ተናግሯል። (መዝ. 116:3, 4, 8, 10-14) ለይሖዋ የገባውን ቃል ለማክበርና አምላክ የሚጠብቅበትን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር።

አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። እንዴት? ይህን የምታደርገው ምንጊዜም ከአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወትህን በመምራት ነው። ስለዚህ የይሖዋ አምልኮ በሕይወትህ ውስጥ ምንጊዜም ትልቁን ቦታ እንዲይዝ እንዲሁም በምታደርገው ነገር ሁሉ የአምላክ መንፈስ እንዲመራህ መፍቀድ ይኖርብሃል። (መክ. 12:13፤ ገላ. 5:16-18) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ላደረገልህ ነገር ሁሉ መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ልትከፍለው አትችልም። ይሁንና ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል የምትችለውን ሁሉ ማድረግህ የይሖዋን ‘ልብ ደስ ያሰኘዋል።’ (ምሳሌ 27:11) በዚህ መንገድ ይሖዋን ማስደሰት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

ለጉባኤው ደኅንነት የበኩላችሁን አስተዋጽኦ አበርክቱ

የክርስቲያን ጉባኤ በብዙ መንገዶች ጠቅሞሃል ቢባል እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም። ይሖዋ በጉባኤው በኩል የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦልናል። ከተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ከመንፈሳዊ ጨለማ ነፃ ያወጣህን እውነት ያገኘኸው ከጉባኤው ነው። (ዮሐ. 8:32) “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው የጉባኤና ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ገነት በሆነች ምድር ላይ ሥቃይና መከራ ሳይኖር ለዘላለም ለመኖር የሚያስችልህን እውቀት አግኝተሃል። (ማቴ. 24:45-47) በአምላክ ጉባኤ በኩል ያገኘሃቸውንና ወደፊትም የምታገኛቸውን ጥቅሞች መቼም ቢሆን ቆጥረህ መጨረስ አትችልም። ታዲያ አንተስ በምላሹ ለጉባኤው ምን መስጠት ትችላለህ?

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአካል ክፍሎች ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት እርስ በርስ ተስማምተው እየተገጣጠሙና እያንዳንዱ የአካል ክፍል እንደ አቅሙ በሚያከናውነው የሥራ ድርሻ መሠረት እርስ በርስ ተደጋግፈው እየሠሩ፣ አካሉ እንዲያድግና በፍቅር ራሱን እንዲያንጽ ያደርጉታል።” (ኤፌ. 4:15, 16) ይህ ጥቅስ በዋነኝነት የሚሠራው በቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ክርስቲያኖች በሙሉ መሠረታዊ ሥርዓቱን ተግባራዊ ሊያደርጉት ይችላሉ። በእርግጥም እያንዳንዱ የጉባኤው አባል ለጉባኤው ደኅንነትና እድገት አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል። ይህን ማድረግ የሚቻለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

ይህን ማድረግ የምንችለው ምንጊዜም ሌሎችን ለማበረታታትና ለማነጽ ጥረት በማድረግ ነው። (ሮም 14:19) በተጨማሪም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉ የአምላክን መንፈስ ፍሬ በማፍራት “አካሉ እንዲያድግ” አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። (ገላ. 5:22, 23) ከዚህም ባሻገር “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም ነገር [ለማድረግ]” የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለግ እንችላለን። (ገላ. 6:10፤ ዕብ. 13:16) ወንድም እህት፣ ወጣት አረጋዊ ሳይል ሁሉም የጉባኤው አባላት ‘አካሉ በፍቅር ራሱን እንዲያንጽ’ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ችሎታችንን፣ ኃይላችንን እንዲሁም ቁሳዊ ንብረታችንን ጉባኤው የሚያከናውነውን ሕይወት አድን ሥራ ለመደገፍ ልናውለው እንችላለን። ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 10:8) እንግዲያው በጣም አስፈላጊ በሆነው የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ አድርግ። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በዚህ ሥራ እንዳትካፈል አቅምህን የሚገድብብህ ነገር አለ? ኢየሱስ የገለጻትን ድሃ መበለት አስታውስ። ይህቺ መበለት የሰጠችው ነገር በጣም ትንሽ ነበር። ያም ቢሆን ኢየሱስ ከሌሎቹ ሁሉ የበለጠ እንደሰጠች ተናግሯል። ድሃዋ መበለት አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ ሰጥታለች።—2 ቆሮ. 8:1-5, 12

እርዳታ ስትቀበሉ ተገቢ አመለካከት ይኑራችሁ

አንዳንድ ጊዜ ከጉባኤው እርዳታ መቀበል ያስፈልግህ ይሆናል። ይህ ሥርዓት የሚያስከትልብህን ጫና ለመቋቋም በምትታገልበት ወቅት ጉባኤው የሚሰጥህን ማንኛውንም እርዳታ ለመቀበል ፈጽሞ አታቅማማ። ይሖዋ ‘ጉባኤውን እንዲጠብቁ’ ይኸውም መከራና ችግር ሲያጋጥምህ እንዲረዱህ ብቃት ያላቸውና አሳቢ የሆኑ ወንዶችን ሰጥቷል። (ሥራ 20:28) ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች የጉባኤው አባላት ችግሮች በሚያጋጥሙህ ጊዜ ሊያጽናኑህ፣ ሊደግፉህና መንፈሳዊ ጥበቃ ሊያደርጉልህ ይፈልጋሉ።—ገላ. 6:2፤ 1 ተሰ. 5:14

ይሁን እንጂ የሚያስፈልግህን እርዳታ በምትቀበልበት ጊዜ ተገቢ አመለካከት ሊኖርህ እንደሚገባ አትዘንጋ። ምንጊዜም ቢሆን ለተሰጠህ እርዳታ አድናቆት ይኑርህ። የእምነት ባልንጀሮችህ የሚያደርጉልህን እንዲህ ያለውን እርዳታ የአምላክ ጸጋ መግለጫ እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። (1 ጴጥ. 4:10) እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እኛ ክርስቲያኖች ለሚሰጣቸው ነገር ምንም ዓይነት አድናቆት እንደሌላቸው በዓለም ላይ እንዳሉ በርካታ ሰዎች መሆን አንፈልግም።

ሚዛናዊና ምክንያታዊ ሁኑ

ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጢሞቴዎስን በተመለከተ “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም” ብሎ ነበር። ጳውሎስ አክሎም “ሌሎቹ ሁሉ የክርስቶስ ኢየሱስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉ” ብሏል። (ፊልጵ. 2:20, 21) ጳውሎስ የጠቀሰውን ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በአእምሯችን በመያዝ እኛስ በዛሬው ጊዜ ‘ስለ ራሳችን ፍላጎት’ ከልክ በላይ ከማሰብ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?

ያጋጠሙንን ችግሮች ለመወጣት እንድንችል የጉባኤው አባላት ጊዜያቸውንና ትኩረታቸውን እንዲሰጡን በምንጠይቅበት ወቅት ከእነሱ ብዙ መጠበቅ የለብንም። ለምን? እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ አስብ፦ ድንገተኛ ችግር ቢያጋጥመንና አንድ ወንድም ችግራችንን ለመወጣት እንድንችል ቁሳዊ እርዳታ ቢያደርግልን ይህን ወንድም ከልባችን እንደምናመሰግነው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ቁሳዊ እርዳታ ሊሰጠን እንደሚገባ በመጠበቅ ወንድምን እንዲረዳን እንጠይቀዋለን? እንደዚህ እንደማናደርግ ግልጽ ነው። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ፣ አፍቃሪ የሆኑት ወንድሞቻችን እኛን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁዎች ቢሆኑም ጊዜያቸውን እንዲሰጡን በምንጠብቅበት ወቅት ሚዛናዊና ምክንያታዊ መሆን ይኖርብናል። ደግሞም የእምነት ባልንጀሮቻችን፣ የገጠመንን አስቸጋሪ ሁኔታ እንድንወጣ የሚያደርጉልንን ማንኛውንም እርዳታ በፈቃደኝነት እንዲያደርጉት እንፈልጋለን።

ክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ አንተን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁዎችና ፈቃደኞች እንደሆኑ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ያም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ የምትፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ማሟላት አይችሉ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ይሖዋ ለመዝሙራዊው እንዳደረገው ሁሉ አንተንም ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥምህ እንደሚደግፍህ አትጠራጠር።—መዝ. 116:1, 2፤ ፊልጵ. 4:10-13

እንግዲያው፣ በተለይ መከራና ችግር በሚያጋጥምህ ወቅት ይሖዋ አንተን ለመርዳት ያደረገውን ማንኛውንም ዝግጅት ለመቀበል አታቅማማ፤ እንዲሁም ለተደረገልህ ነገር አመስጋኝ ሁን። (መዝ. 55:22) ይሖዋ የሚደረግልህን እርዳታ እንድትቀበል ይፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ‘በደስታ እንድትሰጥ’ ይፈልጋል። ስለዚህ እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ አቅምህ የሚፈቅድልህን ሁሉ ለማድረግ ‘ከልብህ’ ጥረት አድርግ። (2 ቆሮ. 9:6, 7) በዚህ መንገድ በአመስጋኝነት መቀበልና በሙሉ ልብህ መስጠት ትችላለህ።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ ለይሖዋ ምን ልክፈለው?’—መዝ. 116:12

▪ ‘ለሁሉም ሰዎች መልካም ነገር ለማድረግ’ የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ፈልግ

▪ ሌሎችን ለማበረታታትና ለማነጽ ጥረት አድርግ

▪ ሁኔታዎችህ በፈቀዱልህ መጠን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ አድርግ