በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ

ወላጆች ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ

ወላጆች ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ

“የሥነ ልቦና ጠበብት አንድን ልጅ ጥሩ አድርጎ ማሳደግ የሚቻልበትን ዘዴ ለማግኘት ለዓመታት ሲያደርጉት የነበረውን ጥናት አሁን ሊያቆሙ ይችላሉ፤ የሚያቆሙት ግን ዘዴውን ስላገኙት ሳይሆን ከናካቴው ስለሌለ ነው።” ይህ ሐሳብ ስለ ልጅ አስተዳደግ የወጣን አንድ መጽሐፍ በተመለከተ ታይም መጽሔት ያሰፈረው አስተያየት ነው። መጽሐፉ በልጆች የሥነ ምግባር አቋም ላይ በዋነኝነት ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እኩዮቻቸው እንጂ ወላጆቻቸው አይደሉም የሚል የመከራከሪያ ነጥብ አቅርቧል።

የእኩዮች ተጽዕኖ ከፍተኛ ኃይል እንዳለው የሚካድ አይደለም። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) ዊልያም ብራውን የተባሉ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ለሚገኝ አንድ ወጣት የአምላክን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ቢኖር ሌሎችን መስሎ የመገኘት ጉዳይ ነው። . . . ለወጣቶች ከእኩዮቻቸው የተለዩ መሆን ከሞት የከፋ ነው” ብለዋል። በዚህ ሩጫ በበዛበት ዓለም ውስጥ በብዛት እንደሚታየው ወላጆች ቤተሰባቸው ሞቅ ያለ ግንኙነት የሰፈነበትና አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ከተሳናቸው ወይም ከልጆቻቸው ጋር በቂ ጊዜ ማሳለፍ ካልቻሉ የእኩዮች ተጽዕኖ በልጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲያደርስ አጋጣሚውን እያመቻቹ ሊሆን ይችላል።

ከዚህም በላይ አሁን ባለንበት “በመጨረሻው ዘመን” ቤተሰብ አደጋ ላይ ወድቋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው ሰዎች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ለገንዘብ፣ ለተድላና ለግል ጥቅማቸው ነው። ታዲያ ልጆች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው” ሲሆኑ መመልከት ሊያስደንቀን ይገባል?—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3

በዚህ ጥቅስ ላይ “ፍቅር” የሚለው ቃል ቤተሰባዊ ፍቅርን ያመለክታል። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ፣ ልጆች ደግሞ ከወላጆቻቸው ጋር ጠንካራ ስሜታዊ ትስስር እንዲኖራቸው የሚያደርግ ተፈጥሯዊ ማሰሪያ ነው። ይሁን እንጂ ወላጆች ተፈጥሯዊ ፍቅር ሲጎድላቸው ልጆቻቸው ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ሌላ አቅጣጫ በተለይ ደግሞ ወደ እኩዮቻቸው ዞር ይላሉ። በዚህ ጊዜ የእነርሱን ሥነ ምግባራዊ አቋምና አስተሳሰብ ሊኮርጁ ይችላሉ። ይሁንና ወላጆች የቤተሰባቸውን ሕይወት ለመምራት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚጠቀሙ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ሊያስወግዱ ይችላሉ።—ምሳሌ 3:5, 6

ቤተሰብ—መለኮታዊ ተቋም

አምላክ አዳምንና ሔዋንን ባልና ሚስት አድርጎ ካጣመራቸው በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው። በዚህ መንገድ አባትን፣ እናትንና ልጆችን ያቀፈው የቤተሰብ ተቋም ወደ ሕልውና መጣ። (ዘፍጥረት 1:28፤ 5:3, 4፤ ኤፌሶን 3:14, 15) ይሖዋ፣ ሰዎች ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ለመርዳት መሠረታዊ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ የሚያስችላቸውን ተፈጥሯዊ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ሆኖም ሰዎች ከእንስሳት በተለየ መልኩ ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ ሌላ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ይሖዋ በጽሑፍ የሰፈሩ መመሪያዎችን አዘጋጅቶላቸዋል። ከእነዚህም መሃል ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ እንዲሁም ልጆችን በአግባቡ ስለ መገሠጽ የሚናገሩ መመሪያዎችን እናገኛለን።—ምሳሌ 4:1-4

አምላክ አባቶችን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።” (ዘዳግም 6:6, 7፤ ምሳሌ 1:8, 9) ወላጆች ከሁሉም አስቀድመው የአምላክን ሕግ በልባቸው መያዝ እንደነበረባቸው ልብ በል። እንዲህ ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ሰው የሚሰጠው ትምህርት ሌሎችን እንዲያንቀሳቅስ ከተፈለገ በቃል ብቻ ከመናገር ይልቅ ከልቡ ተነሳስቶ በተግባር እንደሚፈጽመው ማሳየት ይገባዋል። ወላጆችም የልጆቻቸውን ልብ መንካት የሚችሉት እነርሱ ራሳቸው ከልባቸው ካስተማሯቸው ብቻ ነው። ከልባቸው የሚያስተምሩ ወላጆች ለልጆቻቸው ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም ልጆች ከቃል ይልቅ ተግባርን ይመለከታሉ።—ሮሜ 2:21

ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ገና ከሕፃንነታቸው አንስተው “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” እንዲያስተምሯቸው ተነግሯቸዋል። (ኤፌሶን 6:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15) ገና ከሕፃንነታቸው? አዎን! አንዲት እናት “አንዳንድ ጊዜ እኛ ወላጆች ልጆቻችን ያላቸውን ችሎታ ዝቅ አድርገን እንመለከታለን። ልጆች ሊዳብር የሚችል ችሎታ አላቸው። እኛ ወላጆች ደግሞ ልንጠቀምበት ይገባል” በማለት ጽፋለች። አዎን፣ ልጆች መማር የሚወዱ ሲሆን ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ካስተማሯቸው ደግሞ ማፍቀርንም ይማራሉ። እንደነዚህ ያሉት ልጆች ወላጆቻቸው ባወጡላቸው ገደቦች ጥበቃ ስለሚያገኙ ደኅንነት ይሰማቸዋል። ስለዚህ የተሳካላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው አፍቃሪ ጓደኞች ለመሆን ይጥራሉ፤ ሁልጊዜ ያጫውቷቸዋል፤ ትዕግሥተኛ ሆኖም ጥብቅ አስተማሪ ይሆናሉ። እንዲሁም ልጆቻቸው ጥሩ ሆነው እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን ሁኔታ ያመቻቻሉ። a

ለልጆቻችሁ ጥበቃ አድርጉላቸው

በጀርመን የሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በአሳቢነት ተነሳስቶ ለወላጆች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ውድ ወላጆች ልጆቻችሁን የማሳደጉን ሥራ ለቴሌቪዥን ወይም ለመጥፎ ጓደኞች አሳልፋችሁ ከመስጠት ይልቅ የልጆቻችሁን ባሕርይ በመቅረጽ ረገድ የራሳችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ልናሳስባችሁ እንወዳለን።”

አንድ ሰው ልጁን ለቴሌቪዥን ወይም ለመጥፎ ጓደኞች አሳልፎ ሰጥቷል ሲባል የዓለም መንፈስ በልጁ አስተዳደግ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት ፈቅዷል ማለት ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 2:1, 2) የአምላክን መንፈስ በቀጥታ የሚጻረረው ይህ የዓለም መንፈስ ‘የምድር፣ የሥጋና የአጋንንት’ የሆነውን አስተሳሰብ እንደ ኃይለኛ ነፋስ ጠራርጎ በመውሰድ ተሞክሮ ወይም ብስለት በጎደላቸው ልጆች ልብና አእምሮ ውስጥ ይዘራል። (ያዕቆብ 3:15) አረም ሰብልን እንደሚያወድም ሁሉ ጎጂ የሆኑት እነዚህ አስተሳሰቦች ውሎ አድሮ ልብን ማበላሸታቸው አይቀርም። ኢየሱስ በልብ ላይ የተዘራ ሐሳብ የሚያስከትለውን ውጤት አስመልክቶ ቀጥሎ ያለውን ምሳሌ ተናግሯል:- “መልካም ሰው በልቡ ከሞላው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሞላው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።” (ሉቃስ 6:45) በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና” በማለት ያስጠነቅቀናል።—ምሳሌ 4:23

እርግጥ ልጆች የልጅነት ጠባይ እንደሚያሳዩ አይካድም፤ እንዲያውም አንዳንዶች አስቸጋሪ ብሎም ዓመጸኛ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዘፍጥረት 8:21) በዚህ ጊዜ ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቅለታል” ይላል። (ምሳሌ 22:15) አንዳንዶች ይህን የጭካኔ ተግባር አድርገው በመቁጠር ጊዜ እንዳለፈበት ይናገራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃል መናገርንም ሆነ መደብደብን ይቃወማል። ይሁንና “በትር” የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ ቃል በቃል ሊሠራ ይችላል፤ ይህም አንድ ወላጅ ለልጁ ዘላቂ ደኅንነት በማሰብ በፍቅር ጠበቅ ያለ ተግሣጽ የመስጠት ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ነው።—ዕብራውያን 12:7-11

ከልጆቻችሁ ጋር ተዝናኑ

ልጆች በተገቢው ሁኔታ እንዲያድጉ ከተፈለገ መጫወትም ሆነ መዝናናት እንዳለባቸው ማንም ያውቃል። ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች በተቻለ መጠን ከልጆቻቸው ጋር በመዝናናት አጋጣሚውን ወላጅና ልጅን የሚያስተሳስረውን ሰንሰለት ይበልጥ ለማጠናከር ይጠቀሙበታል። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸው ጤናማ መዝናኛ እንዲመርጡ ከመርዳት በተጨማሪ ከእነርሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስታቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል።

የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ አባት ብዙ ጊዜ ከሥራ ሲመለስ ከልጁ ጋር ኳስ እንደሚጫወት ተናግሯል። አንዲት እናት ደግሞ እንደ ቼዝና ዳማ ያሉ ጨዋታዎችን ከልጆቿ ጋር መጫወት ያስደስታት እንደነበር ታስታውሳለች። አንዲት ሴት፣ ልጅ እያለች መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ብስክሌት እየነዱ ይዝናኑ እንደነበር ተናግራለች። ከላይ የተጠቀሱት ልጆች በሙሉ አሁን ትልልቅ ሰዎች ሆነዋል፤ ይሁንና ለወላጆቻቸውም ሆነ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር አሁንም ድረስ ጠንካራ ከመሆኑም ባሻገር ወደፊትም ይበልጥ እየጠነከረ እንደሚሄድ አያጠራጥርም።

በቃልም ይሁን በተግባር ልጆቻቸውን እንደሚወዱ የሚያሳዩ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚያስደስታቸው ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ዘላቂ የሆነ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የአንድ ክፍል ተመራቂዎች መካከል አብዛኞቹ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግባቸው እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው የወላጆቻቸው ምሳሌነትና ማበረታቻ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ለልጆቹ እንዴት ያለ ግሩም ውርስ ነው! ወላጆቻቸውም ቢሆኑ በእጅጉ ተባርከዋል! ልጆች ሁሉ ሲያድጉ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት ይችላሉ ማለት ባይሆንም ሁሉም ልጆች የቅርብ ጓደኛና ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኗቸው አምላክን የሚፈሩ ወላጆች መጠቀማቸው እንዲሁም ወላጆቻቸውን ማክበራቸው አይቀርም።—ምሳሌ 22:6፤ ኤፌሶን 6:2, 3

ነጠላ ወላጆች ስኬታማ መሆን ይችላሉ

በዛሬው ጊዜ በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ልጆች አሉ። ያለ ትዳር ጓደኛ ድጋፍ ልጆችን ማሳደግ ይበልጥ ተፈታታኝ ቢሆንም እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወላጆች ስኬታማ መሆን ይችላሉ። እነዚህ ወላጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰችው የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳዊት ክርስቲያን ከኤውንቄ ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ። ኤውንቄ ባለቤቷ የማያምን ሰው በመሆኑ ከእርሱ የምታገኘው ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ድጋፍ እንዳልነበረ እሙን ነው። ይሁንና ጢሞቴዎስን በማስተማር ረገድ አርዓያ ትሆነናለች። ኤውንቄ ከእናቷ ከሎይድ ጋር ሆና ከሕፃንነቱ አንስታ በጢሞቴዎስ ላይ ያሳደረችው በጎ ተጽዕኖ ከአንዳንድ እኩዮቹ አሉታዊ ተጽዕኖ የበለጠ ኃይል እንዳለው አስመስክራለች።—የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:15

በዛሬው ጊዜም የማያምን ወይም ነጠላ ወላጅ ባለበት ቤት የሚኖሩ ብዙ ልጆች ወጣቱ ጢሞቴዎስ የነበሩትን ግሩም ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነው የ22 ዓመቱ ራያን ከታላቅ እህቱና ወንድሙ ጋር ያደገው በነጠላ ወላጅ ነው። ራያን የአራት ዓመት ልጅ ሳለ የአልኮል ሱሰኛ የነበረው አባታቸው ቤተሰቡን ትቶ ሄደ። ራያን “እማዬ ቤተሰቡ ሁሉ ይሖዋን ማምለኩን እንዳይተው ቆርጣ ነበር። ደግሞም በሙሉ ልቧ ከውሳኔዋ ጋር ተስማምታ ትኖር ነበር” በማለት ሁኔታውን አስታውሶ ተናግሯል።

ራያን በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ለምሳሌ ያህል፣ እናቴ በጎ ተጽዕኖ ከማያሳድሩብን ልጆች ጋር እንዳንወዳጅ ትከታተለን ነበር። ከጉባኤ ውጪም ሆነ በጉባኤ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ጓደኛ ብሎ ከሚጠራቸው ልጆች ጋር እንድንገጥም በፍጹም አትፈቅድልንም። ከዚህም በላይ ለሰብዓዊ ትምህርት ሊኖረን የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት ቀርጻብናለች።” የነራያን እናት ከሥራ ብዛት የተነሳ ብዙ ጊዜ የሚደክማት ቢሆንም ይህ ሁኔታ ለልጆቿ በአሳቢነት አንዳንድ ነገሮችን ከማድረግ አላገዳትም። ራያን እንዲህ ብሏል:- “እናታችን ሁልጊዜ ከእኛ ጋር የመሆን ፍላጎት ያላት ከመሆኑም በላይ ቀርባ ታጫውተናለች። እንዲሁም ትዕግሥተኛ ሆኖም ጥብቅ አስተማሪ ነበረች። ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖረን የተቻላትን ያህል ትጥር ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በእርሷ ዘንድ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም።”

ራያን የልጅነት ጊዜውን መለስ ብሎ ሲያስበው በእርሱም ሆነ በታላቅ ወንድሙና እህቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር ረገድ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ በዋነኝነት የምትጠቀሰው አምላክንም ሆነ ልጆቿን ከልቧ የምትወደው እናቱ መሆኗን ተገንዝቧል። ስለዚህ እናንተ ክርስቲያን ወላጆች የትዳር ጓደኛ ይኑራችሁም አይኑራችሁ ወይም የትዳር ጓደኛችሁ አማኝም ይሁን አይሁን ልጆቻችሁን ለማስተማር ጥረት በምታደርጉበት ጊዜ ተስፋ መቁረጥም ሆነ ጊዜያዊ መሰናክል እንዲያሸንፋችሁ አትፍቀዱ። አንዳንድ ልጆች ልክ እንደ ኮብላዩ ልጅ ከእውነት የሚወጡበት ጊዜ ይኖራል። ይሁንና ይህ ዓለም ምን ያህል አርቴፊሻልና ርኅራኄ የጎደለው መሆኑን ሲመለከቱ ይመለሱ ይሆናል። አዎን፣ “ጻድቅ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራል፤ ከእርሱም በኋላ የሚከተሉት ልጆቹ ቡሩካን ናቸው።”—ምሳሌ 20:7፤ 23:24, 25፤ ሉቃስ 15:11-24

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በእነዚህ ነጥቦች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 55-59 ተመልከት።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

በአምላክ የተመረጡት የኢየሱስ ወላጆች

ይሖዋ፣ ልጁ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ወደ ምድር ሲልከው የኢየሱስን ወላጆች የመረጠው በጥንቃቄ ነበር። የሚገርመው ነገር ባልና ሚስቱ መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ተራ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስን ከማቀማጠል ይልቅ የአምላክን ቃል አስጠንተውታል፤ እንዲሁም ጠንክሮ መሥራትና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን ያላቸውን ዋጋማነት እንዲገነዘብ ረድተውታል። (ምሳሌ 29:21፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27) ዮሴፍ ለኢየሱስ የአናጢነት ሙያ አስተምሮታል። በተጨማሪም ዮሴፍና ማርያም በኋላ ላይ የወለዷቸውን ቢያንስ ስድስት ልጆች ሲያሳድጉ የበኩር ልጃቸው ኢየሱስ እንዲያግዛቸው እንዳደረጉ ምንም ጥያቄ የለውም።—ማርቆስ 6:3

የዮሴፍ ቤተሰብ የማለፍ በዓልን ለማክበር በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ለሚያደርገው ጉዞ ሽር ጉድ ሲል በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት፤ ዘመናዊ መጓጓዣ በሌለበት በዚያ ዘመን ኢየሩሳሌም ደርሰው ለመመለስ 200 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠይቅባቸው ነበር። ዘጠኝ አሊያም ከዚያ በላይ ቁጥር ያለው ይህ ቤተሰብ ለጉዞው ጥሩ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት የታወቀ ነው። (ሉቃስ 2:39, 41) ዮሴፍና ማርያም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥሟቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ለሚያደርጉት ጉዞ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጡ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምናልባትም እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ስላለፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ለልጆቻቸው ለማስተማር ተጠቅመውበት ይሆናል።

ኢየሱስ በልጅነቱ ወላጆቹን ‘ይታዘዝላቸው የነበረ’ ሲሆን ‘በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ’ ነበር። (ሉቃስ 2:51, 52) በእርግጥም ዮሴፍና ማርያም፣ አደራ ሊጣልባቸው የሚገቡ ሰዎች መሆናቸውን አስመስክረዋል። በዛሬው ጊዜ ላሉ ወላጆች ግሩም ምሳሌ ትተዋል!—መዝሙር 127:3