በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጤንነትህን ጠብቅ

ጤንነትህን ጠብቅ

ጤንነትህን መንከባከብህ ትምህርት የመቀበል ችሎታን ብሎም ሕይወትህን ሊያሻሽልልህ ይችላል።

አምላክ የሰጠህን ሰውነት መንከባከብህ በጣም አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 139:14) ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ መኪና አለህ እንበል፤ ይሁን እንጂ አስፈላጊውን ጥገና አድርገህለት አታውቅም። በመሆኑም ውሎ አድሮ ይህ መኪና መበላሸቱ አይቀርም። በሰውነትህ ላይም ተመሳሳይ ነገር ሊደርስ ይችላል። ታዲያ ሰውነትህ የሚያስፈልገው ምን ዓይነት “ጥገና” ነው?

በቂ እረፍት፦

በቂ እንቅልፍ አለማግኘትህ ድክምክም ብለህ እንድትታይ፣ እንድትልፈሰፈስና ግራ እንድትጋባ ሊያደርግህ አልፎ ተርፎም ሊደብትህ ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ በቂ እረፍት ማግኘትህ የበለጠ ጉልበት ይሰጥሃል። በተጨማሪም እድገትህን ያፋጥንልሃል፣ የአንጎልህን አሠራር ያሻሽልልሃል፣ የሰውነትህን በሽታ የመከላከል አቅም ይጨምርልሃል፤ እንዲሁም ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል። ትንሽ ጥረት በማድረግ ብቻ ይህን ሁሉ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።

ጠቃሚ ምክር፦ ከተቻለ በእያንዳንዱ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት ለመተኛት ጥረት አድርግ።

የተመጣጠነ ምግብ፦

በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እድገታቸው ፈጣን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቹ ወንዶች በ10 እና በ17 ዓመት ዕድሜ መካከል የሰውነታቸው ክብደት በእጥፍ ይጨምራል። ሴቶች ልጆችም በከፍተኛ ፍጥነት ያድጋሉ። በማደግ ላይ ያለ ሰውነት ደግሞ በቂ ምግብና ኃይል ያስፈልገዋል። እንግዲያው ሰውነትህ የሚያስፈልገውን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ አድርግ።

ጠቃሚ ምክር፦ ቁርስ ሳትበላ መዋል የለብህም። ትምህርት ከመጀመርህ በፊት ‘ነዳጅ መሙላትህ’ በትኩረት የማዳመጥና የማስታወስ ችሎታህን ሊያሻሽልልህ ይችላል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦

መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለሰውነትህ ጠቃሚ ነው” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን) የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጡንቻዎችህንና አጥንቶችህን ሊያጠነክርልህ የሚችል ሲሆን ኃይልህን ከፍ ለማድረግ፣ ክብደትህን ለመቆጣጠር፣ የማሰብ ችሎታህን ለማሳደግ፣ የሰውነትህን በሽታ የመከላከል አቅም ለመጨመር፣ ውጥረትን ለመቀነስና ስሜትህን ለማነቃቃት ሊረዳህ ይችላል። እርግጥ ነው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አንተ የምትወዳቸውን እንቅስቃሴዎች ሊያካትት ስለሚችል አስደሳች ይሆንልሃል!

ዋናው ነጥብ፦ በቂ እንቅልፍ፣ የተመጣጠነ ምግብና መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ‘የሰውነትህ ሞተር’ መሥራቱን እንዲቀጥል ጥሩ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ይህ ደግሞ ትምህርት የመቀበል ችሎታህን ከፍ ያደርገዋል። *

አሁኑኑ ለምን አትጀምርም? በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምታደርግበት መደበኛ ፕሮግራም ይኑርህ። ለአንድ ወር ያህል የእንቅልፍና የአመጋገብ ልማድህን በማስታወሻ በማስፈር በምን ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ለማስተዋል ሞክር።

“ደክሞኝ እያለም እንኳ የእግር ጉዞ ማድረግ ስጀምር ጉልበቴ እየታደሰ ሲሄድ ይሰማኛል።”—ጄሰን፣ ኒውዚላንድ

“አምላክ ምግብን የሰጠን ለሰውነታችን ነዳጅ እንዲሆን በማሰብ እንደሆነ ይሰማኛል፤ ስለዚህ ወደ ሰውነቴ ማስገባት የምፈልገው ምርጥ የሆነውን ነዳጅ ነው!”—ጂል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“በሳምንት ሦስት ጊዜ እሮጣለሁ፤ በሳምንት ሁለት ጊዜ ደግሞ ብስክሌት እነዳለሁ ወይም በእግር እጓዛለሁ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጌ ተጨማሪ ጉልበት የሚሰጠኝ ከመሆኑም በላይ የሚሰማኝን ውጥረት ያቀልልኛል።”—ግሬስ፣ አውስትራሊያ

^ አን.9 ጤንነትህን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1 (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተመልከት።