በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሚያስጨንቁ የዜና ዘገባዎችና ልጆቻችሁ

የሚያስጨንቁ የዜና ዘገባዎችና ልጆቻችሁ

“የ11 ዓመት ልጄ ዜና መከታተል አትወድም። ብዙ ጊዜ ያየችው ነገር በሕልሟ ይመጣባታል። አንድ ጊዜ የቤተሰቡን አባል ራስ ስለቆረጠ ሰው የሚናገር የዜና ዘገባ አይታ ነበር። የዚያን ቀን ማታ በሕልሟ ጭንቅላቷ ሲቆረጥ አየች።”—ክዊን

“ስድስት ዓመት የሆናት የባለቤቴ ወንድም ልጅ፣ በአንድ የአገሪቱ ክፍል ስለደረሰ አውሎ ነፋስ ዜና ላይ ተመለከተች። ከዚያ በኋላ ለበርካታ ሳምንታት በፍርሃት ትርበተበት ነበር። ስልክ ደውላ በእርግጥ አውሎ ነፋስ እየመጣ እንደሆነና መሞቷ እንደማይቀር ትነግረኝ ነበር።”—ፔዥ

የዜና ዘገባዎች በልጆቻችሁ ላይ ፍርሃት ያሳድራሉ? በአንድ ጥናት ላይ 40 በመቶ የሚሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ባዩት ዜና እንደተረበሹና በዚህም ምክንያት ተመሳሳይ ነገር በራሳቸው ወይም በቤተሰባቸው ላይ ይደርሳል ብለው እንደሰጉ ተናግረዋል።

ለምን? አንዱ ምክንያት፣ አብዛኛውን ጊዜ ልጆች የዜና ዘገባዎችን የሚረዱበት መንገድ ከትላልቅ ሰዎች ስለሚለይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ትናንሽ ልጆች በተደጋጋሚ የቀረበ አሳዛኝ ዜና ሲመለከቱ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለ ይመስላቸዋል።

ሁለተኛው ምክንያት፣ አንድ ልጅ የሚያስጨንቁ የዜና ዘገባዎች በየዕለቱ ሲቀርቡ መመልከቱ ስለ ዓለም ያለውን አመለካከት ሊያዛቡበት ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ የምንኖርበት ዘመን “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሆኖም ልጆች የሚረብሹ የዜና ዘገባዎችን አዘውትረው መከታተላቸው በፍርሃት እንዲሽመደመዱ ሊያደርጋቸው ይችላል። ካይዘር ፋምሊ ፋውንዴሽን የተባለ ተቋም “በቴሌቪዥን የሚቀርብ ዜና በብዛት የሚመለከቱ ልጆች ስለ ወንጀል መስፋፋት የተጋነነ ግንዛቤ ይኖራቸውና ዓለም ከእውነታው የከፋ አደገኛ ቦታ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ” በማለት ዘግቧል።

የሚያስጨንቁ የዜና ዘገባዎች በልጆችህ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ቀጥሎ ጥቂት ሐሳቦች ቀርበዋል።

ጥበቃ አድርጉላቸው።

የልጆቹን ዕድሜ፣ ብስለትና ስሜታዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዜና በመከታተል ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንደሚኖርባቸው ገደብ አውጡላቸው። በዚህ የመረጃ ዘመን ልጆች ወቅታዊ ሁኔታዎችን እንደሚሰሙ ጥርጥር የለውም። ትናንሽ ልጆች እንኳ ከምትገምቱት በላይ ብዙ ነገሮችን ሊያዩ ወይም ሊሰሙ ይችላሉ። ስለዚህ በልጆቻችሁ ላይ የፍርሃት ወይም የመረበሽ ምልክቶች ካያችሁ ጉዳዩን በትኩረት ተከታተሉ።

አስተምሯቸው።

ልጆቻችሁ በዕድሜ ከፍ እያሉ ሲሄዱ የዜና ዘገባዎችን አብሮ የመከታተሉን ጉዳይ ልታስቡበት ይገባል። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ዘገባዎቹን ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን ማስተማር ትችላላችሁ። ዜናው የያዘውን አዎንታዊ ጎን ለማጉላት ሞክሩ። ለምሳሌ በተፈጥሮ አደጋ ወቅት ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ ትኩረት ማድረግ ትችላላችሁ።

አረጋጓቸው።

አስጨናቂ የሆነ ዜና በሚቀርብበት ጊዜ ስለተከሰተው ነገር ልጆቻችሁ ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ጠይቋቸው። ማይክል የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ወንድ ልጃችን ነታንየል ዜና ላይ ስለተመለከተው ነገር ማብራሪያ የምንሰጠው ከመሆኑም ሌላ እንዲህ ያለው አሳዛኝ ነገር በእኛ ላይ እንዳይደርስ ስላደረግነው ጥንቃቄ ጊዜ ወስደን እናስረዳዋለን። አንድ ቀን ነታንየል አንድ ቤት በእሳት ጋይቶ አመድ ሲሆን በቴሌቪዥን በተላለፈ ዜና ላይ ሲመለከት የእኛም ቤት መቃጠሉ እንደማይቀር ስጋት አደረበት። እሱን ለማረጋጋት ስንል፣ ቤታችን ውስጥ የተተከሉትን የእሳት አደጋ የማስጠንቀቂያ መሣሪያዎች በሙሉ አሳየነው። ልጃችን መሣሪያዎቹ የት የት ቦታ ላይ እንዳሉና ለምን እዚያ እንደተተከሉ ያውቃል። ይህን ማድረጋችን እንዲረጋጋ አስችሎታል።”

ሚዛናዊ አመለካከት ያዙ።

ሰዎች አንድ ዓይነት ሁኔታ የመድረሱ አጋጣሚ ከፍተኛ ነው ብለው የሚያስቡት ለዚያ ሁኔታ ምሳሌ የሚሆኑ ክስተቶችን ማስታወስ በቻሉበት መጠን እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ለምሳሌ አንድ ልጅ ታፍኖ እንደተወሰደ በቅርብ ሰምታችሁ ከነበረ ልጃችሁ እንዲህ ላለው አደጋ የመጋለጡ አጋጣሚ ከፍተኛ እንደሆነ ሊሰማችሁ ይችላል። እርግጥ አደጋ ሊደርስ ይችላል ብሎ መጠንቀቁ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡ ዘገባዎች ፈጽሞ ሊደርሱብን የማይችሉ ክስተቶችን እንድንፈራ ሊያደርጉን እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።—ምሳሌ 22:3, 13

ወላጆች ለዜና ዘገባዎች ሚዛናዊ አመለካከት ከሌላቸው ከልክ በላይ ፍርሃት ሊያድርባቸው ይችላል። ልጆቻቸውም ተመሳሳይ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ለምሳሌ በ2005 አንድ የ11 ዓመት ልጅ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በዩታ ተራራዎች ላይ ሲጓዝ አቅጣጫ ስቶ ጠፋ። ጠላፊዎች አፍነው ይወስዱኛል ብሎ ስለፈራ እሱን ይፈልጉ ከነበሩ ሰዎች ለአራት ቀናት ተደብቆ ቆየ። ፍለጋ ላይ የተሰማሩት ሰዎች መጨረሻ ላይ ሲያገኙት ልጁ ተዳክሞና በእጅጉ ውኃ ተጠምቶ ነበር። ተጠልፎ የመወሰድ አደጋው ከ350,000 እጅ 1 ቢሆንም ልጁ ካደረበት ፍርሃት የተነሳ እርዳታ ከመቀበል ይልቅ ለረሃብ መዳረግን መርጦ ነበር።

“ዕድሜያቸው ከ3 እስከ 7 ዓመት የሚሆኑ ልጆች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችንና ያልታሰቡ አደጋዎችን በተመለከተ የሚቀርቡ ዜናዎች ይበልጥ ፍርሃት የሚያሳድሩባቸው ሲሆን ከ8 እስከ 12 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ደግሞ በጣም የሚፈሩት የወንጀልና የዓመፅ ዘገባዎችን ነው።”—ካይዘር ፋምሊ ፋውንዴሽን

ከዚህ ምን እንማራለን? እናንተም ሆናችሁ ልጆቻችሁ ለዜና ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ይኑራችሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ብዙ አደጋዎች አርዕስተ ዜና ሆነው የሚቀርቡት የተለመዱ ክስተቶች ስለሆኑ ሳይሆን ያልተለመዱ በመሆናቸው ነው።

ወንጀል፣ ዓመፅና የተፈጥሮ አደጋዎች በዚህ ዘመን በብዛት የሚያጋጥሙ አሳዛኝ ክስተቶች ሆነዋል። ይሁን እንጂ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ልጆቻችሁን ለመጠበቅ፣ ለማስተማር፣ ለማረጋጋትና ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ለመርዳት የምታደርጉት ጥረት ልጆቻችሁ አስጨናቂ የዜና ዘገባዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩባቸው ሊረዳቸው ይችላል።