በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተደራጀህ ሁን

የተደራጀህ ሁን

ትንሽ ጥረት አድርጎ መደራጀት በእጅጉ ይክሳል፤ ጊዜ ይቆጥባል፣ ውጥረትን ይቀንሳል እንዲሁም ጥሩ ውጤት ያስገኛል።

አንድ ነገር ለመግዛት ወደ አንድ መደብር ጎራ አልክ እንበል፤ ሆኖም በመደብሩ ውስጥ ሸቀጣ ሸቀጦቹ በሙሉ ሥርዓት በሌለው ሁኔታ በየቦታው ተዝረክርከዋል። የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ምን ያህል ጊዜ የሚፈጅብህ ይመስልሃል? ሸቀጣ ሸቀጦቹ ሳይዝረከረኩ በሥርዓት ቢቀመጡና መደርደሪያዎቹ ላይ የዕቃዎቹ ስም ቢለጠፍባቸው የምትፈልገውን ነገር በቀላሉ አታገኝም ነበር? ትምህርትህንም በተመለከተ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ፕሮግራም አውጣ፦

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ዛከሪ የተባለ የ18 ዓመት ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት ሳምንቱን ሙሉ ጓደኛዬ ቤት ስለከረምኩ ትምህርት ቤት የተሰጠኝን የቤት ሥራ ሙሉ በሙሉ ረስቼው የነበረ ከመሆኑም በላይ ቤት ውስጥ የማከናውናቸውን ሥራዎች ዘንግቼ ነበር። በመሆኑም ሰኞ ዕለት የቤት ሥራዬን ለመሥራት ጊዜ እንዲሰጡኝ አስተማሪዎቼን መለመን ግድ ሆኖብኝ ነበር። አሁን ግን የምሠራቸውን ነገሮች በዝርዝር መጻፌ መሥራት ያለብኝን ነገር እንዳስታውስ ይረዳኛል።”

ሴሌስቲን የምትባል በፓፑዋ ኒው ጊኒ የምትኖር አንዲት ወጣትም የምትሠራቸውን ነገሮች ዝርዝር መጻፏ ጠቅሟታል። በትምህርት ያሳለፈችውን ዘመን መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ ብላለች፦ “የቤት ሥራዬን፣ ፈተናዎቼንና የተጋበዝኩባቸውን ግብዣዎች ጨምሮ ለማደርጋቸው ነገሮች በሙሉ ፕሮግራም አወጣ ነበር። እንዲህ ማድረጌ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እንዳስቀድምና ማንኛውንም ነገር በጊዜው ማጠናቀቅ እንድችል ረድቶኛል።”

ጠቃሚ ምክር፦ የምትሠራቸውን ነገሮች ዝርዝር አነስተኛ በሆነ የማስታወሻ ደብተር ላይ ጻፍ ወይም በሞባይል ስልክህ አሊያም በሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ላይ መዝግብ።

ዛሬ ነገ አትበል፦

“በኋላ እሠራዋለሁ” ማለት ቀላል ነው። ይሁን እንጂ የምትሠራቸውን ነገሮች በተለይም የቤት ሥራህን በተቻለ መጠን ቶሎ መሥራትህ የተሻለ ነው።

ጠቃሚ ምክር፦ ቤት እንደደረስክ፣ ቴሌቪዥን ከመክፈትህ ወይም በሌላ ዓይነት መዝናኛ መካፈል ከመጀመርህ በፊት የቤት ሥራህን የመሥራት ልማድ ይኑርህ።

በቦርሳህ ውስጥ የሚያስፈልጉህን ነገሮች በሥርዓት ያዝ፦

ክፍል ውስጥ ከገባህ በኋላ ማስታወሻ ደብተርህን፣ እስክሪብቶህን ወይም መጽሐፍህን ስትፈልግ ያጣህበት ጊዜ አለ? እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳያጋጥምህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በማያንማር የሚኖር ኦንግ ሚዮ ሚያት የተባለ አንድ ወጣት “ሁልጊዜ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች በሙሉ ቦርሳዬ ውስጥ የምከተው አስቀድሜ ነው” በማለት ተናግሯል።

ጠቃሚ ምክር፦ በቦርሳህ ውስጥ የምትከታቸውን ነገሮች በቀላሉ ማግኘት እንድትችል በሥርዓት አስቀምጣቸው።

ዋናው ነጥብ፦ የተደራጀህ መሆንህ ዕቃዎችህን በመርሳት፣ ረፍዶብህ እየሮጥክ በመድረስና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሌሎች ነገሮች በቂ ጊዜ በማጣት ሊደርስብህ ከሚችለው ውጥረት ያድንሃል።

አሁኑኑ ለምን አትጀምርም? በሚገባ መደራጀት የሚጠይቅ አንድ ተግባር ወይም የሥራ መስክ ለማሰብ ሞክር። ከዚያም ማሻሻያ ልታደርግባቸው የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች በሚገባ ለማጤን እንዲረዳህ ከወላጅህ ወይም ከጓደኛህ ጋር ተማከር።