መዝሙር 139:1-24

  • አምላክ አገልጋዮቹን በሚገባ ያውቃል

    • ከአምላክ መንፈስ ማምለጥ አይቻልም (7)

    • ‘ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ’ (14)

    • ‘ፅንስ እያለሁ ዓይኖችህ አዩኝ’ (16)

    • ‘በዘላለም መንገድ ምራኝ’ (24)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የዳዊት መዝሙር። ማህሌት። 139  ይሖዋ ሆይ፣ በሚገባ መርምረኸኛል፤ ደግሞም ታውቀኛለህ።+   አንተ ስቀመጥም ሆነ ስነሳ ታውቃለህ።+ ሐሳቤን ከሩቅ ታስተውላለህ።+   ስጓዝም ሆነ ስተኛ በሚገባ ታየኛለህ፤መንገዶቼን ሁሉ ታውቃለህ።+   ይሖዋ ሆይ፣ ገና ቃል ከአፌ ሳይወጣ፣እነሆ፣ አንተ ሁሉን ነገር አስቀድመህ በሚገባ ታውቃለህ።+   ከኋላም ከፊትም ከበብከኝ፤እጅህንም በላዬ ላይ ታደርጋለህ።   እንዲህ ያለው እውቀት እኔ ልረዳው ከምችለው በላይ ነው።* በጣም ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ልደርስበት አልችልም።*+   ከመንፈስህ ወዴት ላመልጥ እችላለሁ?ከፊትህስ ወዴት ልሸሽ እችላለሁ?+   ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፤በመቃብር* አልጋዬን ባነጥፍም እነሆ፣ አንተ በዚያ ትኖራለህ።+   እጅግ ርቆ በሚገኝ ባሕር አቅራቢያ ለመኖር፣በንጋት ክንፍ ብበር፣ 10  በዚያም እንኳ እጅህ ትመራኛለች፤ቀኝ እጅህም ትይዘኛለች።+ 11  “በእርግጥ ጨለማ ይሰውረኛል!” ብል፣ በዚያን ጊዜ በዙሪያዬ ያለው ሌሊት ብርሃን ይሆናል። 12  ጨለማው ለአንተ አይጨልምብህም፤ይልቁንም ሌሊቱ እንደ ቀን ብሩህ ይሆናል፤+ጨለማ ለአንተ እንደ ብርሃን ነው።+ 13  አንተ ኩላሊቴን ሠርተሃልና፤በእናቴ ማህፀን ውስጥ ጋርደህ አስቀመጥከኝ።*+ 14  በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ስለተፈጠርኩ+ አወድስሃለሁ። ሥራዎችህ አስደናቂ ናቸው፤+ይህን በሚገባ አውቃለሁ።* 15  በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣በማህፀን ውስጥ እያደግኩ በነበረበት ወቅት፣*አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም ነበር።+ 16  ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ፤አንዳቸውም ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው በፊት፣የተሠሩባቸውን ቀኖች በተመለከተ በዝርዝር ተጻፈ። 17  ሐሳቦችህ ለእኔ ምንኛ ውድ ናቸው!+ አምላክ ሆይ፣ ቁጥራቸው ምንኛ ብዙ ነው!+ 18  ልቆጥራቸው ብሞክር ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ።+ ከእንቅልፌ ስነቃም ገና ከአንተው ጋር ነኝ።*+ 19  አምላክ ሆይ፣ ምነው ክፉውን በገደልከው!+ በዚያን ጊዜ ጨካኞች* ከእኔ ይርቁ ነበር፤ 20  እነሱ በተንኮል ተነሳስተው በአንተ ላይ ክፉ ነገር* ይናገራሉ፤ስምህን በከንቱ የሚያነሱ ጠላቶችህ ናቸው።+ 21  ይሖዋ ሆይ፣ አንተን የሚጠሉትን እጠላ የለም?+በአንተ ላይ የሚያምፁትንስ እጸየፍ የለም?+ 22  እጅግ ጠላኋቸው፤+ለእኔ የለየላቸው ጠላቶች ሆነዋል። 23  አምላክ ሆይ፣ በሚገባ ፈትሸኝ፤ ልቤንም እወቅ።+ መርምረኝ፤ የሚያስጨንቁኝንም* ሐሳቦች እወቅ።+ 24  በውስጤ ጎጂ የሆነ ዝንባሌ ካለ እይ፤+በዘላለምም መንገድ ምራኝ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለእኔ እጅግ አስደናቂ ነው።”
ወይም “ከመረዳት አቅሜ በላይ ነው።”
ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“አበጃጅተህ ሠራኸኝ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴ ይህን በሚገባ ታውቃለች።”
ቃል በቃል “ጥልቅ በሆኑ የምድር ክፍሎች ውስጥ በተሸመንኩ ጊዜ።”
“ገና እየቆጠርኳቸው እገኛለሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የደም ዕዳ ያለባቸው ሰዎች።”
ወይም “የመሰላቸውን።”
ወይም “እረፍት የሚነሱኝንም።”