በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርዳታ ጠይቅ

እርዳታ ጠይቅ

የሌሎችን እርዳታ ማግኘት በትምህርት ላይ ሳለህ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ትልቅ ሰው ከሆንክ በኋላም በምታከናውናቸው ነገሮች ረገድ በጣም አስፈላጊ ነው።

በትምህርትህ ውጤታማ ለመሆን በምታደርገው ጥረት ማን ሊረዳህ ይችላል?

ቤተሰብ፦

በብራዚል የምትኖር ብሩነ የተባለች የ18 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የቤት ሥራዬን ለመሥራት እርዳታ ሲያስፈልገኝ አባቴ ትምህርቱን የሚያብራራልኝ ከመሆኑም ሌላ ሐሳቡ እንዲገባኝ የሚረዱ አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቀኝ ነበር። ይሁን እንጂ መልሱን ራሴ አስቤ እንዳገኝ ያደርጋል እንጂ አይነግረኝም።” *

ጠቃሚ ምክር፦ በመጀመሪያ እናትህ ወይም አባትህ አንተን የከበደህን ትምህርት ይማሩ በነበረበት ወቅት ምን ያህል ውጤታማ እንደነበሩ ለማወቅ ጠይቃቸው። ወላጆችህ በዚያ ትምህርት ጎበዞች ከነበሩ ሊረዱህ ይችላሉ።

አስተማሪዎች፦

አብዛኞቹ አስተማሪዎች፣ አንድ ተማሪ በትምህርቱ ውጤታማ ለመሆን ከልቡ እንደሚጥር ሲያውቁ ደስ ስለሚላቸው ለመርዳት ፈቃደኞች ይሆናሉ።

ጠቃሚ ምክር፦ አስተማሪህን “ይህ ትምህርት ቢከብደኝም ጥሩ ውጤት ማምጣት እፈልጋለሁ። ምን ትመክረኛለህ?” ብሎ መጠየቅ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።

አማካሪዎች፦

ምናልባትም እምነት የሚጣልባቸው የቤተሰብህ ወዳጆች ሊረዱህ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት እጥፍ ድርብ ጥቅም ሊኖረው ይችላል፤ አንደኛ፣ የሚያስፈልግህን እርዳታ ታገኛለህ። ሁለተኛ፣ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የሌሎችን እርዳታ የመጠየቅ ልማድ ታዳብራለህ፤ ይህ ልማድ ደግሞ ትልቅ ሰው ከሆንክ በኋላም ይጠቅምሃል። በአብዛኛው የሕይወት መስክ ስኬት ሊገኝ የሚችለው ለብቻ ሆኖ በመሥራት ሳይሆን በቡድን በሚደረግ ጥረት ነው።—ምሳሌ 15:22

ጠቃሚ ምክር፦ ማን ጥሩ አማካሪ ሊሆንህ እንደሚችል ወላጆችህን ጠይቃቸው።

ዋናው ነጥብ፦ የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ ስህተት አይደለም።

አሁኑኑ ለምን አትጀምርም? ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑህ የሚችሉና የምታከብራቸው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ስም ጻፍ። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል በትምህርትህ ሊረዳህ የሚችል ሰው ይኖር ይሆን?

^ አን.4 ታላቅ ወንድምህ ወይም እህትህ ሊረዱህ ይችሉ ይሆናል።