በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተነሳሽነት ይኑርህ

ተነሳሽነት ይኑርህ

ለማንኛውም ነገር ተነሳሽነቱ እንዲኖርህ በቅድሚያ ጠቀሜታውን መገንዘብ ይኖርብሃል።

መማር ምን ጥቅም ያስገኛል? ትምህርት ጥበብ እንድታገኝ የሚረዳህ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ ጥላ ከለላ ነው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:12) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ለምሳሌ፣ በአንድ አደገኛ አካባቢ በእግር እየተጓዝክ ነው እንበል። ታዲያ በዚህ ወቅት ብቻህን ብትሆን ይሻልሃል? ወይስ አንድ አደጋ ቢፈጠር እንኳ ሊጠብቁህ ከሚችሉ ጓደኞችህ ጋር ብትሄድ ትመርጣለህ? መሠረታዊ የሆነ ጥሩ ትምህርት ቀሰምክ ማለትም ምንጊዜም ከአንተ የማይለዩ “ጓደኞች” አፈራህ ማለት ነው። እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦

  • የማሰብ ችሎታ፦ ትምህርት ቤት ገብተህ መማርህ መጽሐፍ ቅዱስ “ማስተዋልና የማመዛዘን ችሎታ” በማለት የሚጠራቸውን ባሕርያት እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። (ምሳሌ 3:21 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን) እነዚህን ችሎታዎች ማዳበርህ ደግሞ ሁልጊዜ የሌሎችን እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ የሚያጋጥሙህን ችግሮች ራስህ መፍታት እንድትችል ይረዳሃል።

  • ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች እንደ ትዕግሥትና ራስን መግዛት ያሉ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ይመክራል። (ገላትያ 5:22, 23) በትምህርት ቤት ከተለያዩ ልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ትልቅ ሰው ስትሆን በጣም የሚጠቅሙህን እነዚህን ባሕርያት ጨምሮ እንደ መቻቻል፣ ለሌሎች አክብሮት ማሳየትና መራራት የመሳሰሉ ግሩም ባሕርያትን እንድታዳብር ጥሩ አጋጣሚ ይከፍትልሃል።

  • ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ሥልጠና፦ ትምህርት ጥሩ የሥራ ባሕል ያለውን ጠቀሜታ እንድትገነዘብ የሚያደርግህ ሲሆን ይህ ደግሞ ሥራ ለማግኘትና ሥራውን እንደያዝክ ለመቀጠል ይረዳሃል። በተጨማሪም በዙሪያህ ስላለው ዓለም ብዙ ባወቅህ መጠን ስለ ማንነትህና ስለምታምንበት ነገር የተሻለ ግንዛቤ ይኖርሃል። (ምሳሌ 14:15) እንዲህ ዓይነት ጠንካራ እምነት ካለህ ደግሞ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ስለምታምንባቸው ነገሮች ለሌሎች ማስረዳት ትችላለህ።—1 ጴጥሮስ 3:15

ዋናው ነጥብ፦ ትምህርት እንዲህ ያለ ጠቀሜታ የሚያስገኝልህ ከሆነ ትምህርትን እንድትጠላ በሚያደርጉ ነገሮች ላይ ማብሰልሰልህ ምንም ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ ከላይ የተገለጹትን እንድትማር የሚገፋፉ ምክንያቶች በማሰብ ለመማር ተነሳሳ። መማር የሚያስገኛቸውን ሌሎች ጥቅሞችም ማሰብ ትችላለህ።

አሁኑኑ ለምን አትጀምርም? በግለሰብ ደረጃ ለመማር እንድትነሳሳ የሚያደርግህን ዋነኛ ምክንያት ለማሰብ ሞክር።