በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች ማድረግ የሚችሉት ነገር

ወላጆች ማድረግ የሚችሉት ነገር

“በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ተማሪዎች ታጭቀው ይማሩ ነበር! ክፍሉ አየር የሚያቀዘቅዝ መሣሪያ ስላልነበረው ሙቀቱ ትንፋሽ የሚያሳጣ ነበር።”—ሉዊስ፣ ቦሊቪያ

“በትምህርት ቤታችን ጥቂት አስተማሪዎች ብቻ ስለነበሩ ለእያንዳንዱ ተማሪ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት የሚሰጥ አልነበረም። ትምህርት ቤቱ ካርታዎች፣ የቤተ ሙከራ መሣሪያም ሆነ ቤተ መጻሕፍት አልነበሩትም።”—ዶከስ፣ ምያንማር

“አብዛኞቹ አስተማሪዎቼ የክፍሉን ተማሪዎች ለመቆጣጠር ይቸገሩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ተማሪዎች በጣም ስለሚረብሹ መማር በጣም አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር።”—ኒና፣ ደቡብ አፍሪካ

ከላይ የቀረቡት አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መማር በጣም አስቸጋሪ ነው። ታዲያ እንደ ወላጅ መጠን፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም እንኳ ልጆቻችሁ ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።

ልባዊ ተነሳሽነት ይኑራችሁ፦

አብዛኞቹ ችግሮች ከእናንተ አቅም በላይ ሊሆኑ ስለሚችሉ በችግሮቹ ላይ ከማተኮር ይልቅ ልታደርጉት በምትችሉት ነገር ላይ አተኩሩ። ልጃችሁ አንድ ትምህርት ከከበደው ወይም ብዙ የቤት ሥራ የሚሰጠው ከሆነ አንድ ላይ ሆናችሁ በመወያየት መፍትሔ ፈልጉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቤት ውስጥ ለጥናት ይበልጥ አመቺ የሆነ ቦታ ማዘጋጀት ትችላላችሁ? ልጃችሁ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ተግባሮቹን ለማከናወን የሚያስችለውን ፕሮግራም ለማውጣት እርዳታ ያስፈልገዋል? አስጠኚ ቢቀጠርለት ይበልጥ ይጠቀም ይሆን? ተጨማሪ የመፍትሔ ሐሳብ ለማግኘት የልጃችሁን የክፍል ኃላፊ ወይም ሌሎች አስተማሪዎች ማነጋገር ትችላላችሁ። እነዚህን ሰዎች እንደ ባላንጣ ሳይሆን እንደ አጋሮቻችሁ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው።

ልጃችሁ ከትምህርት በሚገኘው ጥቅም ላይ እንዲያተኩር አድርጉ፦

ልጃችሁ የሚማርበት ዓላማ፣ ሲያድግ ሁለገብ እውቀት ያለውና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንዲሆን ነው። ልጃችሁ የሚማረው እንዲሁ ሀብት ማካበት የሚቻልበትን መንገድ ለማወቅ መሆን የለበትም። ሆኖም በዚህ መስክ የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዙ ወጣቶች የሚማሩት ሀብት ለማግኘት ስለሚፈልጉ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ቁሳዊ ሀብትን በሚመለከት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ” ቢናገርም “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ” ሰዎች እውነተኛ ደስታ እንደማያገኙ በመግለጽ ያስጠነቅቃል።—መክብብ 7:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9

ልጃችሁ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ እንዲማር አድርጉ፦

ብዙ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎቻቸው አስቸጋሪዎች ሊሆኑ ቢችሉም ወላጆቻቸው ከልጆቹ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆኑበት ጊዜ እንዳለ አስተያየት ሰጥተዋል። አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው ችግር ሲገጥመው ወይም በፈተና ዝቅተኛ ውጤት ሲያመጣ ወዲያውኑ ጣልቃ ገብተው ያዙኝ ልቀቁኝ ይላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ታይም መጽሔት አንዲት የኮሌጅ ፕሮፌሰር አንዳንድ ተማሪዎቻቸውን አስመልክተው የሰነዘሩትን አስተያየት እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል፦ “አንዳንድ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ሲያመጡ ክፍል ውስጥ ትምህርት እየተካሄደ ባለበት ሰዓት ስሞታ ለመንገር ለወላጆቻቸው በሞባይል ስልክ ይደውላሉ፤ በዚህ ጊዜ ወላጆቻቸው ጣልቃ በመግባት ፕሮፌሰሯን ማነጋገር ስለሚፈልጉ እዚያው ክፍል ውስጥ ስልኩን ለፕሮፌሰሯ ይሰጧታል። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ብዙ ገንዘብ እየከፈሉ እንደሆነና ይህን ያህል ወጪ እያወጡ ልጆቻቸው ከኤ ያነሰ ውጤት ሊያገኙ እንደማይገባ የሚጠቁም አስተያየት ይሰነዝራሉ።”

እንዲህ ዓይነቶቹ ወላጆች ልጆቻቸውን እየጠቀሟቸው አይደለም። እንዲያውም ልጆቻቸውን “በመርዳት” ፋንታ ልጆቻቸው “ውሳኔ በማድረግ፣ በመሳሳትና የሠሩት ስህተት ያስከተለውን መዘዝ ተቋቁመው በማለፍ ረገድ ጥሩ ልምድ እንዳያገኙ” እንቅፋት እየፈጠሩባቸው እንደሆነ ፖሊ ያንግ አይዘንድራት የተባሉ ሴት ዘ ሰልፍ-ኤስቲም ትራፕ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ወላጆች የልጆቻቸውን ችግር ለመፍታት በሚል ሁልጊዜ ጣልቃ የሚገቡ ከሆነና በዚህ ሳቢያ ልጆቹ እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡ ከሆነ ወላጆቹ ልምድ እያካበቱ ይሄዳሉ፤ ልጆቹ ግን ምንም ዓይነት ልምድ ስለማይኖራቸው አንዳንድ ችግሮችን በራሳቸው ለመፍታት ሲሞክሩ ሳይሳካላቸው ይቀራል።”

ልጃችሁ እስከ ምን ደረጃ መማር እንዳለበት በምክንያታዊነት ወስኑ፦

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ትምህርት ልጃችሁ ሲያድግ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንዲሆን ሊረዳው ይችላል። (ዘፍጥረት 2:24) ይሁን እንጂ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ እስከ ምን ደረጃ መማር ያስፈልገዋል?

ልጃችሁ ጥሩ ኑሮ ለመኖር የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መከታተል እንዳለበት አድርጋችሁ አታስቡ። ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ሌሎች አማራጮች አሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ፣ ሙያ የተማሩ ሰዎች የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ከሚያገኙት ጋር የሚተካከል ገቢ ሊያገኙ ይችላሉ።

ዋናው ነጥብ፦ ትምህርት ቤቶች የራሳቸው የሆኑ ችግሮች ያሏቸው ሲሆን በዛሬው ጊዜ ልጆች ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ተሰምተው የማያውቁ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ይሁን እንጂ ልጃችሁ ከእናንተ በሚያገኘው ድጋፍ ታግዞ በትምህርቱ ሊሳካለት ይችላል! ታዲያ በቤተሰብ ሆናችሁ በዚህ መጽሔት ላይ ከገጽ 3 እስከ 7 ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ለምን አትወያዩባቸውም?