በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

ጥቁር የእሳት ጥንዚዛ ያሉት ጠቋሚዎች

ጥቁር የእሳት ጥንዚዛ ያሉት ጠቋሚዎች

ሰደድ እሳት ሲነሳ ብዙ እንስሳት ይሸሻሉ፤ ጥቁር የእሳት ጥንዚዛዎች (ብላክ ፋየር ቢትል) ግን በሰደድ እሳቱ ይማረካሉ። ለምን? ምክንያቱም የተቃጠሉት ዛፎች ለእነዚህ ነፍሳት እንቁላል ለመጣል ምቹ ሁኔታ ይፈጥሩላቸዋል። ከዚህም በላይ እሳቱ ጠላቶቻቸውን በሙሉ ስለሚያባርር ጥንዚዛዎቹ ያለ ምንም ስጋት እንደልባቸው መመገብ፣ መራባትና እንቁላል መጣል ይችላሉ። ለመሆኑ ጥቁር የእሳት ጥንዚዛዎች ቃጠሎ የተነሳበትን ቦታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የእሳት ጥንዚዛ፣ ከመካከለኛው እግሮቹ ቀጥሎ ባለው የአካል ክፍል ላይ ከሰደድ እሳት የሚወጣውን ጨረር (ኢንፍራሬድ ሬዲዬሽን) መለየት የሚችሉ ጠቋሚዎች (ፒት ኦርጋንስ) አሉት። ጨረሩ በጠቋሚ የሰውነት ክፍሉ ላይ ሲያርፍ ሙቀት እንዲፈጠር ያደርጋል፤ ከዚያም ጥንዚዛው ጨረሩን በመከተል ወደ እሳቱ ያመራል።

እነዚህ ጥንዚዛዎች እሳትን አነፍንፎ የሚያገኝ ሌላም መሣሪያ አላቸው። ጥንዚዛዎቹ የሚፈልጉት ዛፍ በሚቃጠልበት ጊዜ በአንቴናቸው ተጠቅመው በቃጠሎው ምክንያት አየር ውስጥ የሚለቀቁትን እጅግ አነስተኛ መጠን ያላቸው አንዳንድ ኬሚካሎች እንኳ ለይተው ማወቅ ይችላሉ። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ጥቁር የእሳት ጥንዚዛዎች “በጭስ ማነፍነፊያ” አንቴናቸው አማካኝነት በ800 ሜትር ርቀት እየተቃጠለ ያለን አንድ ዛፍ ማግኘት ይችላሉ። እነዚህ ጥንዚዛዎች ጠቋሚ የሰውነት ክፍላቸውንና ማነፍነፊያ አንቴናቸውን አቀናጅተው በመጠቀም ከ48 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ ርቀት ላይ የሚገኝን የደን ቃጠሎ ለይተው ማወቅና ቦታውን ማግኘት ይችላሉ።

ተመራማሪዎች ኢንፍራሬድ ጨረሮችንና ቃጠሎን የሚጠቁሙ መሣሪያዎችን አሻሽለው ለመሥራት በጥንዚዛው አካል ላይ የሚገኘውን ጠቋሚ የሰውነት ክፍልና አንቴና በማጥናት ላይ ናቸው። አብዛኞቹ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው የኢንፍራሬድ መጠቆሚያ መሣሪያዎች ማቀዝቀዣ ያስፈልጋቸዋል፤ ስለዚህ የሳይንስ ሊቃውንት ማቀዝቀዣ የማያስፈልገው መጠቆሚያ መሣሪያ ለመሥራት በጥንዚዛው ላይ ያለውን ንድፍ ማጥናታቸው ሊረዳቸው ይችላል። መሐንዲሶች፣ የጥንዚዛውን አንቴና ንድፍ በመቅዳት ቃጠሎ የተነሳበትን ቦታ የማወቅ ችሎታቸው ከፍተኛ የሆኑ እንዲሁም ከደን ቃጠሎ የሚወጡትን ንጥረ ነገሮች ከሌሎች ኬሚካሎች መለየት የሚችሉ ጠቋሚ መሣሪያዎችን ለመሥራት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

ተመራማሪዎች፣ ጥቁር የእሳት ጥንዚዛ እንቁላሏን የምትጥልበትን ቦታ ለመፈለግ በምትጠቀምበት ልዩ ዘዴ እጅግ ይደነቃሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የኮርነል ዩኒቨርሲቲ የጥንዚዛ ሊቅ የሆኑት ሪቻርድ ሆቤክ “እነዚህ ጥንዚዛዎች በዚህ መንገድ እንቁላል የመጣል ችሎታቸውን ያዳበሩት እንዴት ነው?” በማለት ጠይቀዋል። ከዚያም ‘ውስብስብና አስገራሚ የመለየት ችሎታ ስላላቸው ነፍሳት ያለን እውቀት በጣም ውስን ነው’ ብለዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ጥቁር የእሳት ጥንዚዛ፣ የደን ቃጠሎን አነፍንፎ የማግኘት ችሎታውን ያገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?