በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክል ወይስ ስህተት? መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጠናል

ትክክል ወይስ ስህተት? መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጠናል

ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ውሳኔ የምናደርገው በራሳችን ወይም በሌሎች ስሜት ላይ ብቻ ተመሥርተን ከሆነ ውሳኔያችን ጥሩ ውጤት ላያስገኝ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ይነግረናል። ሆኖም በዚህ ብቻ አይወሰንም። አስደሳችና አርኪ ሕይወት ለመምራት የሚረዳ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጠናል።

የአምላክ መመሪያ ያስፈልገናል

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ a አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው ራሳቸውን እንዲመሩ ሳይሆን ከእሱ መመሪያ እንዲያገኙ አድርጎ እንደሆነ ይናገራል። (ኤርምያስ 10:23) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን የሥነ ምግባር ደንቦች ያሰፈረልን ለዚህ ነው። እሱ የሰው ልጆችን ይወዳል፤ እንዲሁም በግምትና በሙከራ ውሳኔ ማድረግ ከሚያስከትለው መዘዝና ብስጭት ሊጠብቀን ይፈልጋል። (ዘዳግም 5:29፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እሱ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ለእኛ ከሁሉ የተሻለውን ምክር ለመስጠት የሚያስችል ጥበብና እውቀት አለው። (መዝሙር 100:3፤ 104:24) ያም ቢሆን አምላክ፣ ሰዎች በእሱ መሥፈርቶች እንዲመሩ ፈጽሞ አያስገድድም።

ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለአዳምና ለሔዋን እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28, 29፤ 2:8, 15) ከዚህም ሌላ ቀላል መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል፤ እነዚህን መመሪያዎች እንዲከተሉም ይጠብቅባቸው ነበር። ያም ቢሆን እነዚህን መመሪያዎች ለመከተል ወይም ላለመከተል እንዲመርጡ ፈቅዶላቸዋል። (ዘፍጥረት 2:9, 16, 17) የሚያሳዝነው፣ አዳምና ሔዋን በአምላክ መሥፈርቶች ከመመራት ይልቅ በራሳቸው መሥፈርት ለመመራት መረጡ። (ዘፍጥረት 3:6) ውጤቱስ ምን ሆነ? የሰው ልጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው በመወሰናቸው የተሻለ ሕይወት መምራት ችለዋል? በፍጹም። የአምላክን መሥፈርቶች ችላ ማለት ዘላቂ ሰላምና ደስታ እንደማያስገኝ ታሪክ ይመሠክራል።—መክብብ 8:9

አስተዳደጋችንና ባሕላችን ምንም ይሁን ምን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ይሰጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ “ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) እንዴት? እስቲ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ቃል” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?—1 ተሰሎንቄ 2:13 የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ማን ነው? የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን መመሪያ ይዟል

መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንት ዘመን አንስቶ ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ስለነበረው ግንኙነት በትክክል ይዘግባል። በውስጡ ያለው ሐሳብ በአምላክ ዓይን ትክክልና ስህተት እንዲሁም ጠቃሚና ጎጂ ስለሆነው ነገር እንድናውቅ ይረዳናል። (መዝሙር 19:7, 11) በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዱ ዘመን የማይሽራቸው ምክሮችን ይዟል።

ለአብነት ያህል በምሳሌ 13:20 ላይ የሚገኘውን ምክር ልብ በል፦ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል።” ይህ ምክር በጥንት ዘመን የነበረውን ያህል በዘመናችንም ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ባሉ ጠቃሚ ምክሮች የተሞላ ነው።—“ ዘመን የማይሽረው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር የሚሰጠው መመሪያ ዛሬም እንደሚሠራ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ቀጣዩ ርዕስ ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ እውነተኛ ታሪኮችን ይዟል።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18