በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ከአሁኑ መዘጋጀት ትችላለህ

በቅርቡ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖረን ሕይወት

በቅርቡ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖረን ሕይወት

አምላክ ምድርን የፈጠረው፣ ጻድቅ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩባት ነው። (መዝሙር 37:29) አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት አዳምንና ሔዋንን ኤደን ገነት ውስጥ አስቀመጣቸው፤ ከዚያም እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው ምድርን እንዲያለሙና እንዲንከባከቡ ኃላፊነት ሰጣቸው።—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15

አሁን በምድር ላይ ያለው ሁኔታ መጀመሪያ ላይ አምላክ ለሰው ልጆች ካሰበው ፈጽሞ የተለየ ነው። የአምላክ ሐሳብ ግን አልተቀየረም። ታዲያ የሰው ልጆች እሱ መጀመሪያ ላይ ያሰበው ዓይነት ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያደርገው እንዴት ነው? ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ እንደተመለከትነው፣ አምላክ ምድርን አያጠፋትም። ከዚህ ይልቅ ታማኝ የሆኑ ሰዎች መኖሪያ እንድትሆን ያደርጋል። አምላክ የገባው ቃል ሲፈጸም በምድር ላይ የሚኖረው ሁኔታ ምን ይመስላል?

መላውን ምድር የሚያስተዳድር አንድ መንግሥት

በቅርቡ በሰማይ የተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር ይጀምራል። ያን ጊዜ ምድራችን ሰዎች በፍቅር ተስማምተው የሚኖሩባት አስደሳች ቦታ ትሆናለች፤ ሁሉም ሰው አስደሳችና አርኪ ሥራ ይኖረዋል። አምላክ፣ ምድርን እንዲያስተዳድር የሾመው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ዛሬ ካሉ ብዙ መሪዎች በተቃራኒ፣ ኢየሱስ ምንጊዜም ተገዢዎቹን የሚጠቅም ነገር ያደርጋል። አገዛዙ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ይሆናል፤ ደግ፣ መሐሪና ፍትሐዊ ንጉሥ ይሆናል።—ኢሳይያስ 11:4

ዓለም አቀፍ አንድነት

ያኔ ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በድንበር ወይም በዘር የተከፋፈሉ አይሆኑም። መላው የሰው ዘር አንድ ሕዝብ ይሆናል። (ራእይ 7:9, 10) ሁሉም ሰው አምላክንና ሰዎችን የሚወድ ይሆናል። ሁሉም በሰላምና በኅብረት በመሥራት የአምላክን የመጀመሪያ ዓላማ ይፈጽማሉ፤ የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ፣ የሰው ልጆች መኖሪያቸውን ምድርን እየተንከባከቡ እንዲኖሩ ነው።—መዝሙር 115:16

ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ መኖር

የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚያስተዳድርበት ወቅት፣ ፈጣሪ የምድርን አየር ንብረት ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል፤ ስለዚህ ያን ጊዜ የተፈጥሮ አደጋዎች አይኖሩም። (መዝሙር 24:1, 2) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አንድን አስፈሪ ማዕበል በቀላሉ ጸጥ አሰኝቷል፤ ይህም አምላክ ለእሱ የሰጠው ኃይል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ያሳያል። (ማርቆስ 4:39, 41) ክርስቶስ ምድርን በሚያስተዳድርበት ወቅት የተፈጥሮ አደጋዎች ይከሰታሉ ብለን የምንሰጋበት ምንም ምክንያት አይኖርም። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት፣ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር እንዲታረቅ ያደርጋል።—ሆሴዕ 2:18

የተሟላ ጤና እና የተትረፈረፈ ምግብ

ሁሉም ሰው የተሟላ ጤና ይኖረዋል። የሚታመም፣ የሚያረጅ ወይም የሚሞት ሰው አይኖርም። (ኢሳይያስ 35:5, 6) የምንኖርበት አካባቢ፣ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንደኖሩባት እንደ ኤደን ገነት ውብና ንጹሕ ይሆናል። በኤደን ገነት እንደነበረው ሁሉ መጪው አዲስ ዓለም ውስጥም መሬቱ ፍሬያማ ይሆናል፤ ስለዚህ ሁሉም የምድር ነዋሪዎች በቂ ምግብ ይኖራቸዋል። (ዘፍጥረት 2:9) አምላክ ይንከባከበው እንደነበረው እንደ ጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ፣ ገነት ውስጥ የሚኖር ሁሉም ሰው ‘ምግቡን እስኪጠግብ ድረስ ይበላል።’—ዘሌዋውያን 26:4, 5

እውነተኛ ሰላምና ደህንነት

የአምላክ መንግሥት መላዋን ምድር በሚያስተዳድርበት ወቅት ሰላም ይሰፍናል፤ ያኔ ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ አንዳቸው ለሌላው ደግና አሳቢ ይሆናሉ። ጦርነት አይኖርም፤ ሥልጣኑን ያላግባብ የሚጠቀም ሰው አይኖርም፤ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚደረግ ሽኩቻም አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ተስፋ ይሰጣል፦ “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”—ሚክያስ 4:3, 4

ምቹ መኖሪያ ቤትና አስደሳች ሥራ

ሁሉም ቤተሰብ፣ ‘ካሁን ካሁን እፈናቀላለሁ’ የሚል ስጋት ሳያድርበት በራሱ ቤት ተረጋግቶ ይኖራል፤ እንዲሁም ሁላችንም የምንወደውን ሥራ መሥራት እንችላለን። አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ‘በከንቱ እንደማይለፉ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ኢሳይያስ 65:21-23

የላቀ የትምህርት ፕሮግራም

መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 11:9) ያን ጊዜ ምድር ላይ የሚኖረው ማኅበረሰብ፣ ማለቂያ ከሌለው የፈጣሪ ጥበብ ብዙ ይማራል፤ ውብ ስለሆኑት የእሱ ፍጥረታትም ብዙ የምንማረው ነገር ይኖራል። ሰዎች እውቀታቸውን የጦር መሣሪያ ለመሥራት ወይም ሌሎች ሰዎችን ለመጉዳት አይጠቀሙበትም። (ኢሳይያስ 2:4) ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ በሰላም የሚኖሩበትንና ምድርን የሚንከባከቡበትን መንገድ ይማራሉ።—መዝሙር 37:11

የዘላለም ሕይወት

አምላክ እያንዳንዱን ቀን ተደስተን እንድንኖር ይፈልጋል፤ ምድርን ለሰው ልጆች ተስማሚ አድርጎ የሠራት ለዚህ ነው። የእሱ ዓላማ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። (መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 45:18) አምላክ ይህን ዓላማውን ለመፈጸም ሲል “ሞትን ለዘላለም ይውጣል” ወይም ያስወግዳል። (ኢሳይያስ 25:8) መጽሐፍ ቅዱስ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (ራእይ 21:4) አምላክ ለሁሉም ሰዎች ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል፤ አምላክ ይህን ክፉ ዓለም ሲያጠፋ የሚያድናቸው ሰዎችም ሆኑ መጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት የሚያስነሳቸው ብዙ ሰዎች ይህን አጋጣሚ ያገኛሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

አሁንም እንኳ፣ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖረው ሕይወት እየተዘጋጁ ነው። እነዚህ ሰዎች ፍጹም ባይሆኑም እንኳ አምላክ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈቅድላቸው ዓይነት ሰዎች ለመሆን ጥረት እያደረጉ ነው። ይህን እያደረጉ ያሉት እንዴት ነው? ስለ ይሖዋ አምላክና እሱ ስለላከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በመማር ነው።—ዮሐንስ 17:3

ከዓለም ፍጻሜ ለመትረፍና በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብህ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ትፈልጋለህ? አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምርህ ጠይቅ፤ ያለምንም ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምርሃል።